Sunday, July 23, 2017

የግብሩ አመጽ – የፍጻሜው ጦርነት

July 23,2017
ክንፉ አሰፋ
የአስቸኳይ (የአፈና) ግዜ  አዋጁ ገና አልተነሳም። በአዲሱ የግብር ትመና ሳብያ ከዳር እስከዳር የተነሳው ሕዝባዊ አድማ እና አመጽ ግን አዋጁን ውድቅ ያደረገው ይመስላል። አንድ ስርዓት ራሱ ያወጣው ህግ በህዝብ ሲሻርበት - ያኔ ነው ያበቃለት!
        ከቶውን "የአለምን  ኢኮኖሚ እየመራች ያለች ሃገር" የበጀት ሸክሟን ለምን በህዝብ ላይ መጣል እንዳለባት ግልጽ አልሆነም። እውነታው ከነዚህ ሁለት እይታዎች ውጭ አይሆንም።  ይነፋ የነበረው የእድገት ቀረርቶ እና ይነገር የነበር ሁለት ዲጅት እድገት ቁጥር ሁሉ ውሸት ነበር፣  ወይንም ደግሞ የሃገሪቱ ሃብት በጥቂቶች እየተዘረፈ ነው።
        ጆሮን ያሰለቸው የ"እድገት እና ትራንስፎርሜሽኑ" ዘፈን ቀዝቀዝ ማለት ሲጀምር የ "ደብል ድጅቱ" የፈጠራ ተረት እንደ በረዶ እየነጻ መሄዱ አልቀረም። እድገቱ የህዝቡን  ህይወት አልለወጠም። ተጀምሮ ከሚቋረጥ ህንጻ እና መንገድ ውጭ ትራንስፎርሜሽኑም በተግባር አልታየም።  ይልቁንም ተሸፍኖ የነበረው ችግር አሁን ፈጥጦ ወጥቶ በህዝብ ጫንቃ ላይ ጉብ ሊል ዳዳው፣ ገበሬውን መሬት በመንጠቅ፣ ነጋዴው ላይ ደግሞ ሚዛናዊ ባልሆነ የገቢ ግምት - ከፍተኛ ግብር በመጫን።   ምላሹንም እንደምናየው ነው።  አድማ፡ ህዝባዊ አመጽ፣... ተቃውሞ!
        በዘንድሮው የበጀት አመት የህወሃት መንግስት 320 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን አብስሮን ነበር።  ይህ በጀት የ100 ቢሊዮን ብር  (1/3ኛ) የበጀት ጉድልት ነበረበት። ይህ የ100 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ከብድር እና እርዳታ ይሸፈናል ተብሎ  ነበር የተጠበቀው። የ11 በመቶው እድገት ተረት - ተረት  ውስጥ የእርዳታው እና የብድሩ መጠን ተገልጾ አያውቅም። ሃገሪቱ በደፈናው እያደገች ነው አሉን። በፈጣን እድገት የአለምን ኢኮኖሚ የምትመራ ሃገር ተባለ።  ፈረንጆቹም አመኑ።
        እርዳታን  እንደ ስትራቴጂ የቀመሩት የህወሃት ጠበብቶች፣ ፈረንጆች ፊታቸውን ማዞር እንደማይሳናቸው እንኳን አላሰቡትም። በሶማሊያ ውስጥ የነሱን ቆሻሻ ጦርነት ስለተረከቡ ብቻ ጉዳዩን እንደ ይገባኛል መብት (for granted) አዩት። የሶማልያ ጉዳይ፣ የአልሻባብ ፖለቲካ ዲስኩር፣ የጸረ-ሽብር እንቶፈንቶ አሁን የለም። አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ዜጎችን በአዋጅ እና በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አፍኖ የያዘው ስርዓት ጋር በረጅሙ እንደማይዘልቁ ግልጽ ነው። ታዲያ ከቻይናው የእድሜ-ልክ የእዳ ቁልል ውጭ የታሰበው የውጭ ገቢ ጠፋ። ማጠፍያው አጠረ። ለሰራዊቱና ለደህንነቱም ደሞዝ መከፈል አለበት።  ...ቀሪው ገንዘብ ከግብር እና ከሃገር ውስጥ የሚሰበሰብ ገንዘብ ብቻ ነው።
        እናም እዳው ሕዝብ  ላይ ተቆለለ። የቀን ገቢ በግምት እየታየ ተጫነ። በገቢና ወጪ ሳይሆን፣  በህዝብ ላይ በግምት ግብር ሲጫን በታሪክ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። አዲሱ የግብር ትመና በንግዱ ህብረተሰብድ ከባድ ቁጣ ቀስቅሷል። ከጫፍ እስከጫፍ የተነሳው የሥራ ማቆም አድማ የት ላይ እንደሚቆም አይታወቅም። በአስቸኳይ ግዜ በምትተዳደር ሃገር የተነሳው ይህ አድማ ቀድሞ የተጀመረው የመብት እና የነጻነት ትግል ቅጣይ ይመስላል። ቀድሞ የተነሳው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።  የህወሃት የአፈና ሰንሰለትም እንደቀጠለ ነው። ዛሬ ነጋዴው ህብረተሰብ የሰለባው ባለሳምንት ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሰረታዊ ችግር ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የግብር ፖሊሲ አይደለም። ችግሩ ስርዓቱ ራሱ ነው። ዛሬ የንግድ ቤቶች ቢዘጉ ሌላ የንግድ ቤቶችን የመክፈት አቅም ያላቸው የህወሃት ሰዎች በደስታ መፈንጠዛቸው አይቀርም። ...አሜካላው ሳይነሳ መፍትሄ አይታሰብም።
        ዋናው ነገር ወዲህ ነው። ግብር ለመክፈልም እኮ የህዝብ ውክልና ያለው ስርዓት መኖር ግድ ይላል። የሀዝቡን ይሁንታ ያላገኘ መንግስት፣ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ግብር የማስከፈል መብት የለውም፣ ሕዝቡም ላልወከለው መንግስት ግብር ለመክፈል አይገደድም።    
        እ.ኤ.አ. በ1750ቹ እና 1760ቹ አስራ ሶስቱ የአሜሪካ ቅኝ ግዛቶች ይዘውት የተነሱት መፈክርን ያስተውሏል። "No Taxation Without Representation" ይላል። "ውክልና ከሌለ ግብር አይኖርም" እንደማለት ነው።  አሜሪካኖች በዚያ የነጻነት ትግላቸው ወቅት አቋማቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙበት መሪ ቃል ነበር።  አመሪካውያኑ ይህንን መፈክር ይዘው በማመጽ የብሪትሽን ኤምፓየር እንዳናፈጡት የታሪክ ማህደር ያወሳናል።
         ህወሃት የህዝብ ይሁንታም የለው፣ መረጃም የለው። ሃይለማርያም ደሳለኝ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ለይ ወጥተው እንዲህ አሉ። ስራችንን የምንሰራው፣ ውሳኔም የምንወስነው መረጃ ሳንይዝ እንዲሁ በግምት ነው። "መረጃ የሚጠናከርበት ስርዓት የለም።" አሉ።  እኚህ ሰው አንዳንዴ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ  እውነትን ይለቁልናል። ንግግራቸው እኝህ ሰው ነጻ ያለመሆናቸውን ይጠቁመናል።   ሃገሪቱ ነጻ መውጣት ካለባት በመጀመርያ ነጻነትን ማወጅ ያለበቸው እሳቸው ናቸው። እውነት ነው።  ህወሃት እየመራ ያለው በግምት እና በጥይት ነው።
        የሃይለማርያም ንግግር አጉልቶ የሚያሳየን ነገር አለ። ስርዓቱ ችግር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን፣ ስርዓቱ ራሱ ችግር መሆኑን ግልጽ ያደርግልናል።
        ትግራይ "ክልል" ፕሬዝዳንት እና የመቐሌ ከንቲባ ላይ ከሰሞኑ የተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ የሚሰብቀን ነገር ይኖራል። ከሰሞኑ በመቀሌ ስታድዮም የገባው ህዝብ በዝግጅቱላይ በተገኙ የህወሓት አመራሮችን "ሌባ ሌባ ሌባ .. ሃሳዊ (ውሸታም) መሲህ ሲሉ ተደምጠዋል። እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ራሱ ተወክያለው ያለውን አመራር "ሌባ ሌባ " ካለ ምን ቀረ?... እንደኔ ግምት የቀረ የለም። ሃገር እየተመራች ያለችው መረጃ በሌላቸው፣ ራዕይ በሌላቸውና የህዝብ ይሁንታ ባላገኙ ሌቦች ነው።
        ከትግራይ ውጭ ያለውም ሕዝብ እንዲህ ነው የሚለው። "ወያኔ ሌባ ነው! ለሌባ ግብር አንከፍልም!"  
        "ኢትዮጵያንና ህዝቧን በጉልበት አፍኖ ለያዘ ዘራፊ ቡድን አንገብርም!!" ብለዋል ጊንጪዎች። ይህ የግብር አመጽ የፍጻሜው ጦርነት ይሆን? እድሜ ከሰጠን እናየዋለን።
        ለዛሬ በዚህ ላብቃ በመጪው ጽሁፌ ስለ "ኳስ እና ፖለቲካ" የምለው አለኝ።

No comments:

Post a Comment