Augest 2,2016
ኢሳት ዜና ፣ — በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢትዮጵያ መንግስት ከስልጣን እንዲወገድ የሚጠይቅ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እሁድ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል ሲሉ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘገቡ። ቢቢሲ እና ኣዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሰልፉን ከዘገቡት ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ነዋሪነታቸው በከተማዋ እና አካባቢዋ የሆነ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የተለያዩ መፈክሮችን በማስተጋባት በሃገሪቱ ኢፍትሃዊነት መንገሱን በተቃውሞ ሲያሰሙ መዋላቸውን አፍሪካ ኒውስ የተሰኘ መጽሄት አስነብቧል።
ተገቢ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል በሃገሪቱ መንገሱን እና የመንግስት አፈናና ቁጥጥር መባባሱን በቁጣ ሲገልጹ የዋሉት ሰልፈኞች ሰልፉ እንዳይካሄድ የተላለፈን ውሳኔ በመጣስ አደባባ መውጣታቸውን መጽሄዱ ሰልፈኞቹን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል።
በመንግስት ላይ ያላቸውን የተለያዩ ተቃውሞዎች የገለጹት የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለ25 አመት በስልጣን ላይ የቆየው የመንግስት ከስልጣን እንዲወገድ ጥያቄ ማቅረባቸውንም አለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለው ይኸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆምና የአማራው ክልል ታሪካዊ የድንበር ወሰን እንዲከበር ጥያቄ ማቅረቡንም አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ዘግቧል።
በጎንደር ከተማ ዕሁድ ሲካሄድ የዋለው ይኸው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በክልሉና በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ መሆኑንም የዜና አውታሩ በዘገባው አስፍሯል።
የብሪታኒያው የማሰራጫ ኮርፖሬሽን (BBC) በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ባቀረበው ሰፊ ዘገባው አስነብቧል።
በክልሉ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን ያወሳው የዜና አውታሩ፣ በሰልፉ የታደሙ ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተመሳሳይ ችግሮችንና በእስር ላይ ተዳርገው የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችን ጉዳት በማንሳት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ በቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
ኢንዲያን ኤክስፕረስ የተሰኘ የህንድ ጋዜጣ በበኩሉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ጎንደር ከተማ በአይነቱ ልዩና ታላቅ የሆነ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ዘግቧል።
በተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የታደሙ ነዋሪዎች ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች ያሉ በርካታ ሰዎች በእግርና በተሽከርካሪ በመሆን ከዋዜማው ጀምሮ ወደጎንደር ከተማ መግባት መጀመራቸውንንና የተቃውሞ ትዕይንቱን እንደተቀላቀሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
“ወያኔ ከእንግዲህ አይገዛንም” ፣ “ወልቃይት አማራ ነው”፣ “በኦሮሚያ ክልል ያለው ግድያ ይቁም” ፣ “በመብታችን አንደራደርም” የሚሉ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ የነበሩት ሰልፈኞች መንግስት በህዝቡ ላይ የሚያደርገውን አፈና እንዲያበቃ አሳስበዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እሁድ ማለዳ በተለያዩ የከተማዋ ዋና ዋና ስፍራዎች ቀድመው በመገኘት የተቃውሞ ሰልፉን ለማደናቀፍ ጥረት ቢያደርጉም ህዝቡ አካባቢውን በሙሉ ተቆጣጥሮ መዋሉን እማኞች አክለው አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment