June 29,2016
“ሪፎርም [ተሃድሶ] በገዥዉም በተቃዋሚዉም የግድ ያስፈልጋል"
ከጥቂት ቀናት በፊት “ሀገር አለኝ!! ወገን አለኝ!!” በማለት በፌስቡክ ገጹ ላይ ይህንን የለጠፈው የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ሃብታሙ አያሌው በጠና ታምሞ በኮማ ውስጥ ይገኛል፡፡
“እዉነት እዉነት እላችሁአለሁ ስቃይና መከራ የምቀበልላት ብቻ ሳትሆን የምሞትላት ሀገር አለችኝ!!
“ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለዉ” ከሚል ጀግና ህዝብ ተወልጄ በእስካሁኑ ስቃይ ጉልበቴ አይዝልም። እንድበረታ ዛሬም ከጎኔ ላልተለያችሁ ቃሌ ይሄ ነዉ። አመሰግናለሁ” ነበር ያለው!
“ዘጠኝ ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለዉ” ከሚል ጀግና ህዝብ ተወልጄ በእስካሁኑ ስቃይ ጉልበቴ አይዝልም። እንድበረታ ዛሬም ከጎኔ ላልተለያችሁ ቃሌ ይሄ ነዉ። አመሰግናለሁ” ነበር ያለው!
የትግል አጋሩ ዳንኤል ሺበሺ (Daniel Shibeshi) በጥቂት ሰዓታት በፊት በፌስቡክ ገጹ ላይ ከላይ የሚታየውን የሃብታሙን ፎቶ አድርጎ ያሰራጨው ጽሁፍ እንዲህ ይላል፤
“በሀብታሙ አያሌው ጤና መታወክ፣ እየተረባበሻችሁ ላላችሁ ሁሉ በያላችሁበት ሆናችሁ ፀሎታችሁን ቀጥሉበት። አሁንም በኮማ ውስጥ ነው ያለው። ለውጥ አልታየም። ከትንፋሽ ውጭ ሌላ እንቅስቃሴ የለም። ቤተሰብ በሙሉ ተረባብሿል። ነገር ሁሉ ግራ ገብቶኛል። ወገን ሆይ በክፉዎች እጅ ወድቀናል!!! ከሌሊቱ 8ሰዓት።”
በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በነበረው የጎላ ተሳትፎ በህወሃት ዓይን ውስጥ የገባው ወጣቱ ፖለቲከኛ ሃብታሙ በህወሃት “አሸባሪ” ተብሎ ተፈርጆ በእስርቤት ሲማቅቅ በቆየበት ጊዜ ከደረሰበት ግፍና ስቃይ የተነሳ ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከፍተኛ ችግር ደርሶባቸው በሃይለኛ ህመምና ስቃይ ውስጥ ሲማቅቅ ቆይቷል፡፡ በአገር ውስጥ መታከም የማይችል በመሆኑ ወደ ውጪ ሄዶ እንዲታከም ከሃኪሞች ቢነገረውም የህወሃት ሹመኛ የሆነው “ወንጀለኛ ዳኛ” ከአለቆቹ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሃብታሙ ወደ ውጪ እንዳይወጣ ከልክሏል፡፡
አሁንም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ቁርጠኛ እንደሆነ የሚናገረው ሃብታሙ ከጥቂት ቀናት በፊት ከጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጋር በአዲስ ገፅ መፅሔት ያደረገው ቃለምልልስ ከዚህ በታች ይገኛል፡፡
ጥያቄ፡- የግንቦት 20 ፍሬን በተመለከተ የምታምንበትን ገልጸሃል፡፡ የተቃውሞ ፓርቲ ትግልም በውጣ ወረድ የታጀበ ነው፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ራሱ በገደል አፋፍ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ለሀገርና ለህዝብ የሚጣፍጥ ፍሬ ለማፍራት ምን መደረግ አለበት?
ሐብታሙ አያሌው፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ፤ በንጉሱም፣ በደርግም የነበሩ ችግሮች ኢህአዴግ ከ25 አመታት በሁአላም እንዲቀጥላቸዉ መፍቀድ አይገባም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ዋናውና መሰረታዊዉ ጥያቄ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ለነገ የሚባሉ አይደሉም። ፈጣን ምላሽ ይጠይቃሉ። ኢህአዴግ እነዚህን መሰረታዊ የህዝብ መብቶች ለማክበር ዝግጁ እንዳልሆነና አቅሙም እንደሌለዉ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ግልፅ የሆነ ይመስላል።
የምትፈልገውን ነገር የማግኘት፣ የመምረጥ፣ በህይወት የመኖር፡ የመናገር፡ የመፃፍ…የመሳሰሉት መሰረታዊ መብቶች በተጣሱበት ምንም አይነት ጣፋጭ ፍሬ ሊገኝ አይችልም። ኢህአዴግ ስልጣን ለማስጠበቅ ብቻ የሚከተለዉ በልማት ስም የህዝብን መብት የማፈን ስርዓት ሊያፈርሰን ካልሆነ በቀር ሊሰራን አይችልም።
ጣፋጭ ፍሬ ለማግኘት ከሁሉ መቅደም ያለበት ሰብዓዊ ልማት ነው፡፡ ከልማቱ ጋር ተያይዞ ከድህነት የመውጣት ጥያቄ ይመጣል፡፡ መጀመሪያ ህሊና… ህሊና ከሆድ መቅደም አለበት፡፡ የህሊና ነጻነት የሚባል ነገር አለ፡፡ ኢህአዴግ ያልገባዉ ወይም እንዲገባዉ ያልፈለገው ይህ ነዉ ። የምን ጊዜዉም መከራከሪያዉ ሆድን በማስቀደም ላይ ነው፡፡ ‹‹ልማት ይቀድማል›› ይለናል፡፡ የህሊና ጥያቄዎች ሳይመለሱ ሆድ መቅደም የለበትም፡፡ የስርዓቱ ሰዎች የገዛ ህዝባቸውን እየዘረፉ በረሃብ የሚቆሉት እና የሚያፍኑት እኮ ለዚህ ነዉ እነሱ ጋር የህሊና ጥያቄ የሚባል ነገር የለም ። በአፋቸዉ ዴሞክራሲና ልማት ተነጣጥለው አይታዩም ይሉሃል በተግባር ግን ከዚህ የተለዩ ናቸዉ መብት የጠየቀን ያስራሉ ያሰድዳሉ ይገላሉ፡፡ ኢህአዴግ ከባድ የቁርጠኝነትና የማስፈጸም ችግር ያለበት ድርጅት ነዉ፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ነገሮች ሲሻሻሉና ትንሽ ዕድል ሲያገኙ አልታዩም ከአመት አመት ወደ ባሰ ጨለማ እያመራን ነዉ። ኢህአዴግ ለመነጋገር እና ለሪፎርም መዘጋጀት አለበት ተቃዋሚዉም እንደዛዉ አለዚያ መጨረሻችን የፈራነው እንደ ሀገር መፍረስ ይመጣል። መነጋገር መደማመጥ የሁሉ መፍትሄ ነዉ ነገር ግን ተስፋ የሚያሳጣዉ ኢህአዴግ በየጊዜው እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ የማይመጣ ድርጅት መሆኑን ነዉ።
ጥያቄ፡- እንዴት?
ሐብታሙ አያሌው፡- ለማስታወስ ያህል፣ በ83 እና 84 ዓ.ም ልጅ ነበርኩ፤ ምንም አላስታውስም፡፡ ግን አንብቤ እና ጠይቄ ከተረዳሁት፣ መሬት ላይ የነበረውም ነገር እንደሚያሳየው ከ83-87 ዓ.ም ድረስ የሚዲያው ነጻነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ነበር ይባላል፡፡ የፈለከውን መናገር ትችላለህ፣ የፈለከውን መጻፍ ትችላለህ፣ ኢህአዴግ ለማፈንና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልት አልዘረጋም ዴሞክራሲን ለማስመሰል ወይም ለመሞከር ይፈልግ ነበር፡፡
ጥቂት ቆይቶ ግን ወደ ተፈጥሮአዊ የድርጅቱ ባህሪ ተመለሰ። ስለዚህ ወደ አፈናው ሲሄድ፡ ምሁራኖቹን መጀመሪያ በጠላትነት መፈረጅ፣ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ያለውን ነገር ማጽዳት፣ ሚዲያዎችን በሙሉ መቆጣጠር፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ወይም ሲቪል ማኅበራትን በመንግሥት ደጋፊዎች በመሙላት መቆጣጠር፣ የሃይማኖት ተቋማትን መቆጣጠር . . . ፖለቲካውን አረጋግቶ ለመምራት ሁሉንም ተቋማት ‹‹በእኔ ቁጥጥር ሥር ማድረግ አለብኝ›› ወደሚል ተግባር ሄደ፡፡ መሆን የነበረበት ግን ይህ ሳይሆን ተቃራኒው ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትን በካድሬ መቆጣጠር ሳይሆን መፍትሄዉ ገለልተኛ ሆነዉ እንዲጠናከሩ ማድረግ ነበር። መንግሥት ሊሔድና ሊመጣ ይችላል፣ ሲስተሙ ግን መቆም ነበረበት፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ያተኮረው ሲስተም ላይ ሳይሆን የቁጥጥር ዘዴ ግንባታ ላይ ነው፡፡
እምነት የሚጣልበት ተቋም ተገንብቶ ቢሆን ኖሮ ላለፉት 25 ዓመታት ምርጫ ቦርድ አያከራክርም ነበር፡፡ ዛሬም የዴሞክራሲ ጥያቄ ሀገሪቷን ያልሆነ ችግር ውስጥ አይከታትም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋም ቢገነባ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያወጣው ውጤትና በሚነግረን ነገር ላይ ልዩነት አይፈጠርም፡፡ የሚዲያ ተቋሙ (በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለው) አንድን ፓርቲ ከማገልገል ይልቅ ሀገራዊ ሚናውን ሊወጣ የሚችል ነጻ የሚዲያ ተቋም እንዲሆን ማድረግ ቢቻል ይሄ ሁሉ ሀገራዊ ቀዉስ አይፈጠርም ነበር፡፡
ጥያቄ፡- እነዚህ ነገሮች በሌሉበት የምታደርገው ምንድን ነው?
ሐብታሙ አያሌው፡- በኢህአዴግ ፕሮግራም ላይ ነጻ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚል አለ፡፡ በነጻ ገበያ እኩል መወዳደር ሚቻልበት ዕድል ግን የለም፡፡ ይልቁንስ እንደምናየውና እንደምንሰማው የመከላከያው ክፍል ተቆጣጥሮታል፡፡ እርግጥ ነው፣ አንድ መከላከያ ሀገርን ከመጠበቅ ባሻገር በልማት ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ ነገር ግን፣ አጠቃላይ የግሉን ሴክተር በሙሉ ከውድድር በሚያወጣ መልኩ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ መከላከያ መሰባሰቡ ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ይዘን ተከራክረናል፡፡ የግል ዘርፉ ነው መንግስትን መቆጣጠር ያለበት፡፡ መንግስት በገበያ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ውስን መሆን አለበት፡፡ መንግስት ኢኮኖሚውንና የፖለቲካ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ አንባገነን ለመሆን ሰፊ ዕድል ይሰጣል፡፡ በዚህም የግለሰቦች ሚና ከፍተኛ ይሆናል፡፡ አየህ ኢህአዴግ በሁሉም ነገር ቁልቁል ሂዶአል የምልህ ለዚህ ነዉ ። በጥቅሉ አንድ ፓርቲ ይወለዳል ያድጋል ይሞይሞታል አሁን ኢህአዴግ በዚህ ሂደት አልፎ እድገቱን ጨርሷል።
ጥያቄ፡- ስለዚህ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
ሐብታሙ አያሌው፡- ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ ሪፎርም ሳያደርግ፣ የዴሞክራሲ አብዩት ሳያመጣ፣ በዴሞክራሲ መንገድ ለውጥ ሳያመጣ፣ በልማቱ ጉዳይ፣ በሰብዓዊ መብት ለውጥ ሳያመጣ እስካሁን በመጣበት መንገድ ለመቀጠል የሚችልበት ዕድል የለም፡፡ ይልቁንስ ወደበለጠ ቀውስ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ሪፎርም የማምጣት ዕድሉን መጠቀም አለበት፡፡ እንደውም አንድ አባባል መጠቀም እፈልጋለሁ፡፡ ኢህአዴግን በተቃዋሚ ጎራ ላይ ወድቀን ነው የጠበቅነው፡፡ ወድቀን ጠብቀን፣ ለምን ደረሱብን እያልን ነው፡፡ ወድቀን ባንጠብቃቸው አይደርሱብንም ነበር፤ ለዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ባነሳ፣ አንዱ የተቃዎሚዎች ጎራ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት ሆኖ የቀጠለበት በማይረባ ምክንያቶች፤ የግል ጉዳዩን ለማሳካት የተሰባሰበ ስብስብ፣ ከግል ከፍተኛ ፍላጎት መዝለል ያልቻለ ስብስብ በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ሲባል የሚከፋው ሰው ይኖራል፤ ግን የሆነ ሰው ይከፈዋል ብዬ አስተያየት ከመስጠት ወደኋላ አልልም፡፡ አንድነት ፓርቲ በእኔ ዘመን ሊቀ-መንበር ያደረገው ኢንጂነር ግዛቸውን ነበር፤ ኢንጂነር ግዛቸው ከኃላፊነት ሲነሳ ‹‹እኔ ከሄድኩ ፓርቲው ብትንትኑ ይውጣ›› ብሎ አንድነትን በትኖ ሄዷል፡፡ ኢንጂነር ግዛቸው አንድነትን በማፍረስ ከኢህአዴግ የሚለይበትን አንድም ምክንያት የሚጠቅስ ሰው አላገኝም፡፡ ኢህአዴግ አንድነትን ለማፍረስ የሰራውን ያህል ኢንጂነር ግዛቸውም ሰርቷል፡፡ እነትዕግስቱስ አንድነትን ለማፍረስ የተጫወቱት ሚና ከኢህአዴግ የሚለየው በምንድን ነው?! ኢህአዴግ መጥቶ አንድነትን ባያፈርሰው ኖሮ ግዛቸው፣ ትዕግስቱና ሰፊው የሚባሉ ሰዎችን ይዘን ነበር የምንቀጥለው፡፡ ያ ስብስብ በርካታ ችግሮች የነበሩበት ስብስብ ነበር፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚነጠረው የፈተና ቀን ሲመጣ አብዛኛው ተበታትኖ ድራሹ ጠፋ፡፡
በእርግጥ ይህንን ለማድረግ የታወቀ ኢህአዴግ ባህሪ አለ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይፈጠር ፍላጎት አለው፡፡ አንድነትን ማፍረስም ለነገ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ምክንያቱም አንድነት ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በደንብ የገባቸውና የተረዱ ምርጥ ምርጥ ኃይሎች ነበሩ፡፡ እኔም ወደአንድነት ስገባ እነዚህን ሰዎች አይቼ ነው፡፡ እነዚህን ጥቂት እርሾ የሆኑ ሰዎችን ይዞ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ውስጥ የኢህአዴግን ሁኔታ ተቋቁሞ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ውስብስብ የሆነው የተቃዋሚው ችግር በቀላሉ የሚለቀን አልሆነም፡፡ በፖለቲካ አቋማቸውና እውቀታቸው አንድም ጥያቄ የማይነሳባቸውን እከሌ እከሌ ብሎ ማንሳት ይቻላል፡፡
እኔና ዳንኤል ወደ እስር ቤት ስንገባ ከአንድነት ፓርቲ በጣም ተስፋ የጣልኩባቸው ምርጥ ምርጥ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ተክሌ በቀለን የመሰለ ፖለቲከኛ፣ በላይ ፍቃዱን የመሰለ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ በቂ እውቀት ያለው ሰዉ፡ ግርማ ሰይፉን የመሰለ ወሳኝ፡ አስራት አብርሃ፡ አስራት ጣሴ፡ ፀጋዬ አላምረዉ … ነበልባል የሆኑት ወጣቶች እንደነ ዳግም፡ እስማኤል ዳዉድ፡ ስንታየሁ ቸኮል፡ ዳዊት ሰሎሞን፡ ያሬድ አማረ፡ አለነ ማህፀንቱን የመሳሰሉ በርካታ ትንታግ ወጣቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እድል ቢያገኙ፣ እንደ ኢህአዴግ በር ዘግቶ የሚያፍን ድርጅት ባይሆን ኖሮ የተሻለ ደረጃ የሚደረስበት እድል ነበረ፡፡ መጨረሻ ላይ እኮ እነ አስራት አብርሃ፣ አናንያ ሶሪ፡ ስለሺ ሀጎስ መሃመድ አሊ፡ ሌሎችም በርካታ ሰዎች ተስፋዎች ወደ አንድነት መጥተው ነበር፡፡ እኛም ከታሰርን በኋላ ፓርቲው ሊቀጥል የሚችልበት ሰፊ እድል ነበር፡፡ በላይ ፍቃዱ ተክሌ በቀለ ግርማ ሰይፉ እውቀትና ክህሎታቸዉን ተጠቅመዉ ምርጥ አመራር እየሰጡ ለዉጥ የሚያመጡበ ብሩህ ዕድል ነበረ፤ ነገርግን ይህንን ኢህአዴግ ጠምዝዞ አክሽፎታል፡፡
የኢህአዴግ አንድነትን ማፍረሱ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ አንድነትን አፍርሶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ዳግም ጨለማውን የበለጠ አበረታው፡፡ እኛን አሰረ፤ አንድነትን አፈረሰ፡፡ ዉጤቱ ሺህ እልህኛ ወጣቶችን ፈጠረ እንጂ ትግሉን አልቀለበሰዉም፡፡ አንድነት ‹‹በርታ›› ሊባልና ሊደገፍ የሚገባው ድርጅት ነበር፡፡ ድክመቶችን እንዲያርም እድል ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ አየህ ኢህአዴግ ፈፅሞ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ብቁም ምቹም እንዳልሆነ ሁሉ የተቃዋሚ ጎራው ስብስብም ባለብዙ ችግር ነዉ፡ ከብዙ ሆድ አደሮች ጋር ተጃምለን ለጉዳት ተጋልጠናል እናም መፍትሄዉ ሰከን ብሎ ወደራስ ማየት ራስን መገምገም ነዉ ።
ከሁሉ በፊት ሀገር እናስቀድም ሪፎርም በገዥዉም በተቃዋሚዉም የግድ ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
በመጨረሻም እኔ ባሁኑ ወቅት በከባድ የጤና ችግር ዉስጥ እንዳለሁ የምታየው ነዉ። የሀገሬ ጉዳይ ቢያሳስበኝም በደረሰብኝ ግፍ ስቃዬን እንዳዳምጥ ተገድጃለሁ። እናም ከብዙ ከሀዲዎች መካከል የነጠሩ የቀድሞ የአንድነት ሃይሎች እንደ ትላንቱ ዛሬም ስላልተለዩኝ አመሰግናለሁ። ተክሌ፡ በላይ፡ ግርማ፡ ስዩም፡ አስራት ጣሴ፡ አስራት አብርሃ፡ ገበየሁ፡ እስማኤል፡ ሰባህ፡ ፋሲካ፡ እዩኤል፡ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ፡ ናትናኤል ፈለቀ፡ ዮናታን ወልዴ፡ ታታሪዉ ጠያቂዬ ተፈሪ፡ ወዳጄ ማይክ መልዐከ … ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።
ከሁሉ በላይ ጠበቃ አመሃ መኮንን ከግፍ እስር ብቻ ሳይሆን ዛሬም ሂወቴን ለማዳን እያደረክ ላለህዉ ሁሉ ከቤተሰቤ ጋር ምስጋና እናቀርባለን። ኤልያስ እንደ ወንድም አልተለየህኝም ምስጋና ይድረስህ፡ በስም ያልተጠቀሳችሁ በሀገር ዉስጥ እና ዉጭ ያላችሁ ሁሉ አመስግኛለሁ።
ሰላም ለሀገራችን ይሁን!
(ምንጭ:Elias Gebru Godana ፌስቡክ)
No comments:
Post a Comment