Friday, March 11, 2016

ህወሃት – 9 ስደተኞችን ደብዳቤ ጽፎ ከአሜሪካ ወሰዳቸው

March 11,2016
“ከህወሃት በላይ በራሳችን አዝኛለሁ” ኦባንግ ሜቶ
miami
ከተለያዩ አገራት አሜሪካ ገብተው የስደት ማመልከቻ ያስገቡ 9 ኢትዮጵያውያንን ህወሃት ተረከቦ ወደ አገር ቤት እንደወሰዳቸው ታወቀ። አንዱ ራሱን ለማጥፋት ሞከሮ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ቢሄድም የጤናው ሁኔታ አልታወቀም። ድርጊቱን አስመልክቶ አቶ ኦባንግ ሜቶ “ከህወሃት ተግባር በላይ በራሳችን አዝኛለሁ” ሲሉ ወጣቶቹን ለማዳን ያደረጉት ጥረት መረጃው ዘግይቶ ስለደረሳቸው አለመሳካቱን አመለከቱ።
“ለቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ እንኳን ነግሬያቸው አላውቅም” ሲል የተናገረውን ወጣት ጨምሮ ህወሃት የተረከባቸው ኢትዮጵያዊያን ወግኖች አሜሪካ ለመድረስ እስከ 14 ወራት ፈጅቶባቸዋል። በብራዚል፣ በኮሎምቢያ ጫካ አቋርጠው፣ በፓናማ ወንዝ ተሻግረው፣ በሜክሲኮ አድርገው በአጠቃላይ እስከ 16 የሚደርሱ አገራትን አልፈው በተለያዩ መንገዶቸ አሜሪካ ደርሰው ጥገኝነት የጠየቁት ወገኖች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ ከስድስት ወር በላይ በፍሎሪዳ ጠቅላይ ቅዛት ማያሚ እስር ቤት መቆየታቸውን ለአቶ ኦባንግ በአስራ አንደኛው ሰዓት የላኩት “የድረሱልን” ደብዳቤ ያስረዳል። መረጃቸው እንደሚያመለክተው ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡት ወገኖች በፍሎሪዳ እስርቤት ከአንድ ወር እስከ አመት ተኩል ድረስ በእስር ቆይተዋል፡፡
አቶ ግርማ ብሩ የሚመሩት የህወሃት የአሜሪካ ቢሮ ስደተኞቹ ቢመለሱ ምንም አይሆኑም፣ ምንም አይደርስባቸውም፣ ሰላማዊ ኑሮ መኖር ይችላሉ፣ ወዘተ በማለት በጻፈው ደብዳቤና አዘጋጅቶ በሰጠው የመጓጓዣ ሰነድ አማካይነት ወጣቶቹ ተላልፈው ሊሰጡት ችሏል።
ህወሃት በኤርትራዊነት መታወቂያ የራሱን ወገኖች ለስደት በምዕራባውያን አገራት እየላከ ኢትዮጵያውያንን ሲያሰልል፤ በባህርና በበረሃ ተንገላተው አሜሪካ የገቡትን ምስኪን ዜጎች ላይ የወሰደው ርምጃ “ዲያስፖራውን የመበቀያ አንዱ አካል ነው” ተብሏል።
“ኑሮዬ ሳይስተካከል ለቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ እንኳን አላሳውቅሁም። እናትና አባቴ ልሙት፣ ልኑር አያውቁም፤ ከተለየኋቸው ጊዜ ጀምሮ ስልክ ሳልደውል አራት አመት ከ11 ወራት አልፈውኛል” ሲል ለአቶ ኦባንግ የድረሱልኝ ጥሪ ካሰሙት ወጣቶች አንደኛው ተናግሯል፡፡ ዘጠኙ በአንድነት ተላልፈው ከመሰጠታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ነበር አቶ ኦባንግ ደብዳቤያቸው የደረሳቸውና ጉዳዩን የሰሙት።
“እንደሰማሁ” አሉ አቶ ኦባንግ “ወዲያውኑ ስደተኞቹን የሚወክል ጠበቃ ያዝኩ። የወጣቶቹ ከስድስት ወር በላይ መታሰር ከህግ አንጻር አግባብ ባለመሆኑና ስደተኞቹ ሊመለሱ እንደማይገባ ለማውቃቸው እንደራሴዎችና ሴናተሮች በማስረዳት የእስር ውሳኔ ላስተላለፉት ዳኛ ደብዳቤ ሊላክ የሰዓታት ዕድሜ ሲቀር መርዶውን ሰማሁ” ብለዋል፡፡
ለወትሮው ረጋ ብለው በመናገር የሚታወቁት ኦባንግ “ለአንድ ቀን ተቀደምን” ሲሉ በቁጣ ነበር ስሜታቸውን የገለጹት። የጎልጉል የአሜሪካ ዘጋቢ ያነጋገራቸው አቶ ኦባንግ ቁጣቸውን ሊደብቁ በማይችሉበት ሁኔታ “ከህወሃት በላይ በራሳችን አዘንኩ” ብለዋል። “ለምን?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “በተመሳሳይ መንገድ ተሰድደው፣ ታስረው፣ ዛሬ በመልካም ሁኔታ ላይ ያሉ ወገኖች የ5 ሺህ ዶላር ዋስ ሆነው ልጆቹን ማስፈታት ይችሉ ነበር ። ዳሩ ምን ያደርጋል ሁላችንም መነሻችንን እንረሳለን” ሲሉ ጉዳዩን አስቀድመው የሚያውቁ ወገኖች ላሳዩት ቸልተኛነት ወቀሳ ሰንዝረዋል።
“አቶ ግርማስ ቢሆኑ” አሉ አቶ ኦባንግ “ይህን ደብዳቤ እንዴት ይጽፋሉ? ወይም ሲጻፍ እንዴት ዝም ይላሉ? የጉዞ ሰነዱ ተሰርቶ እንዲላክስ ለምን ይፈቅዳሉ? ምንም ቢሆን እርሳቸው ሳያውቁ የሆነ ነገር የለም፤ ኅሊና ካላቸው በጣም ሊያፍሩበት ይገባቸዋል፤ እርሳቸውም ሆኑ አብረዋቸው የሚሰሩት ራሳቸውን በእነዚህ ልጆች ጫማ አስገብተው ማየት ይገባቸው ነበር፤ እነርሱ አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ እዚሁ ከነቤተሰቦቻቸው ጥገኝነት ጠይቀው ኑሯቸውን ይቀጥላሉ፤ በአየር፣ በምድር፣ በወንዝ በስንት ስቃይና መከራ እዚህ የደረሱትን ልጆች ግን ደህና አገር እንዳለው የጉዞ ሰነድ ልከው ባዶ እጃቸውን ወደመጡበት እንዲመለሱ ያደርጋሉ፤ ይህ ወራዳና አጸያፊ ተግባር ነው፤ አገሪቱን ወይ በትክክል አያስተዳድሩ ወይ አገሩን ለቅቀው የሚወጡትን የፈለጉበት እንዳይኖሩ በሩ ይዘጋሉ፤ ኅሊና አለኝ ለሚል ሰው ይህ እጅግ አሳፋሪ ነው” ሲሉ ይወቅሷቸዋል።
ከስደተኞቹ መካከል አንዱ ወጣት በአገር ውስጥ የሚካሄደው ሰቆቃ ያስመረረው ከመሆኑ የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመለስ በአሜሪካ እስርቤት ለመሞት እንደሚመኝ መናገሩን አቶ ኦባንግ ጠቁመዋል፡፡ “በረሃና ወንዝ ስናቋርጥ በርካታ ወንድምና እህቶቻችንን አጥተናል፤ ማንም ስለ እነርሱ ግድ ያለው የለም፤ ታዲያ ለምን ለኛ ግድ ያላቸው ለመምሰል ይሞክራሉ” በማለት እንዳወራላቸው አቶ ኦባንግ ጠቅሰዋል፡፡
አገር ቤት ስራ አለመኖሩን፣ ችጋር፣ ረሃብና ድርቅ ዜጎችን እየጠበሰ መሆኑንን፣ እስርና ግድያ፣ አፈና ባለበት ሁኔታ እነዚህን ምስኪኖች ሰብስቦ መውሰድ ህወሃት ዲያስፖራውን ከመበቀል ያለፈ ትርጉም እንደሌለው በመግለጽ ዜጎች ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአሜሪካ እንደራሴዎች ምክርቤት አባላት ደብዳቤ ለመጻፍ ቃል ገብተው፣ ጠበቃ ተገኝቶ ወጣቶቹን ለማስፈታት የሚያስችል ርምጃ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት በተፈጸመው ድርጊት ክፉኛ ማዘናቸውን የጠቆሙት ኦባንግ ሜቶ አሁንም እስር ላይ ያሉትን ለማስፈታት ጥረታቸውን እንደሚገፉበት ተናግረዋል። ከእንግዲህ ጉዳዩ የህወሃት ወይም በዋሽንግተን ዲሲ ያስቀመጠው ጽ/ቤቱ አይደለም፤ ጉዳዩ የራሳችን ነው የሚሉት “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ “ህወሃት የጉዞ ሰነድ እያዘጋጀ የራሱ ጽ/ቤት ባደረገው ኤምባሲው አማካኝነት እየሰጠ ስደተኞች ላይ የሚፈጽመው ይህ ተግባር የሚቆምበት ሁኔታ ከእንደራሴዎች ጋር በመነጋገር ተጽዕኖ የማድረግ ሥራ” ካሁኑ መጀመሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ኦባንግ ስደተኛ ወገኖች ባሉበት ሁሉ ፈጥነው በመድረስና አለኝታ በመሆን የሚታወቁ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ዜጎች የአደባባይ ምስክርነት በ“ቃላቸው” ብቻ የሚሰጧቸው ሰው መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም።

No comments:

Post a Comment