ሥልጣንን በጠመንጃ አፈሙዝ ተቆጣጥሮ ያለው የወያኔ አገዛዝ ካለመታከት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተአምር ሊመስል በሚችል መንገድ እያሳደኩ ነው እያለ ሲዋሽ አመታት ተቆጥረዋል። በተለይ ምዕራባዊያንን ሲያታልልበት የነበረው የዲሞክራሲ ጭንብል በምርጫ 97 ከተገፈፈበት ወዲህ ላለፉት አስር አመታት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ እጅ እጅ እስኪለን ድረስ በባዶ ሜዳ ስለ ልማትና የዕድገት ሲነግረን ሰነበቷል።
ወያኔ በጉልበት በሚያስተዳድራት ኢትዮጵያ የልማትና የእድገት ፕሮፓጋንዳ ስለ ሰበአዊ መብትና ስለዲሞክራሲ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማፈኛና አፍ ለማዘጊያነት በማገልገል ላይ ይገኛል ። አለማቀፍ የሰባአዊ መብት ተቋማት ስለሰበአዊ መብት ጥሰት ለሚያቀርቡት አቤቱታ ሁሉ የሚሰጠው መልስ “ኢኮኖሚውን እያሳደግን ነው” የሚል ነው። ኢኮኖሚ ማደግ አለማደጉን ትርጉም የሚኖረው ከህዝብ የእለተ ተእለት ኑሮ ጋር ሲያያዝ መሆኑ ሁሉ ትርጉም አጥቷል። ራበኝ የሚለው ሰው ሁሉ ጠገብኩ ማለቱ ነው ተብሎም ይተረጎማል።
የውሸት ነገር ውሎ አድሮም ቢሆን መጋለጡ አይቀርምና ይኼው በቅርቡ የተከሰተው ድርቅ የወያኔን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ክንብንብ ገፎታል። አለም በሙሉ አስር አመት ሙሉ በሁለት አሃዝ ሲያድግ የነበረ ኢኮኖሚ ባለበት ሃገር ውስጥ አንዲት የድርቅ አመት ካለርሃብና ልመና እንዴት መሻገር አቃተው የሚል ጥያቄ በሰፊው በማንሳት ላይ ነው። ወያኔ ለዚህ ጥያቄ መልስ የለውም። በአለም ዙሪያ ያለው ተመክሮ ሁሉ የሚያሳየው ወያኔ አድጌበታለሁ ብሎ ሲለፍፍ ከኖረው አሃዝ በታች በግማሽ ያደጉ ሃገሮች እንኳ አንድም ጊዜ አንድ የድርቅ ዘመን መሻገር አቅቶአቸው ሲንገዳገዱና መንግሥታቸው ለልመና ሲሄድ አለመታየቱን ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ የሚያወራውን ያህል ያልሆነ ቢሆንም በአንዳንድ ከተሞች አካባቢ የሚታየው እድገት የተገኘው ከውጭ መንግስታት የገንዘብ ብድር፣ በአለም አቀፍ ተቋማት እርዳታ፣ ስደተኛው ኢትዮጵያዊ በገፍ በሚልከው ገንዘብና ወያኔ ከድሃውና ከነጋዴው ከዝርፊያ ባላነሰ ሁኔታ በሚሰበሰበው ግብርና መዋጮ የተገኘ እንጂ ወያኔ ባስፋፋው ኢንዱስትሪና ልማት እንዲሁም ሀገር ውስጥ በፈጠረው ሀብት አለመሆኑ የሚታወቅ ነው።
የወያኔ ሹማምንትና አገልጋዮች ሀብት በሀብት መሆናቸውን እንደ እድገት ካልቆጠርን በስተቀር ህዝባችን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮውን እንኳን መደጎም አልቻለም ።በዝርፊያ ገንዘብ ሹማምንቱና የወያኔ ባለምዋሎች የገነቡትን ፎቅ የሀገር ልማት ነው ካላልን በስተቀር እውነተኛና የህዝብ ህይወት ከመሰረቱ የሚቀይር ልማት አገር ውስጥ አለመካሄዱ ትንሽ ገለጥ ሲያደርጉት የሚታይ ሃቅ ነው። አንድ የድርቅ ወቅት መሻገር አቅቶት ብዙ ሚሊዮኖችን ከረሃብና እልቂት መታደግ ያልቻለ ኢኮኖሚ አስር አመት ሙሉ በሁለት አሃዝ አድጓል ብሎ የሚያምን ሰው ሊኖር አይችልም።
የወያኔ የኢኮኖሚ አሃዝ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” ከሚለው የሀገራችን ግፈኛ አባባል ብዙም አይለይም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለህዝብ በሚጠቅም መንገድ የማደጉ ጉዳይ በመጀመሪያ ፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርአት መገንባትንና ዴሞክራሲ ማስፈንን ይጠይቃል።
በመሆኑም የዛሬው የወያኔ ኢኮኖሚ የዝርፊያ ኢኮኖሚ እንጂ ህዝባዊ ሽታ የለውም። የኢትዮጵያን ህዝብ እዚህና እዚያ በሚብለጨለጩ ያውም በአብዛኛው በብድርና እርዳታ በተገኙ ልማት ተብዬ ነገሮች ለረዥም ጊዜ ማታለል አይቻልም።
ወያኔ በሚሰጠው አሃዝ የሚያድግ ማንኛውም ሀገር የውጭ ስደተኞችን ያስተናግድ እንደሆን እንጂ ወጣቶች ሞትና ህይወትን አማራጭ አድርገው አይሰደዱበትም። ባለ ሁለት አሃዝ አዳጊ ኢኮኖሚ በየትም ሀገር የስደተኞች ምንጭ ሆኖ ታይቶ አይታወቅም በዘረኛው ወያኔ ተገዢዋ ኢትዮጵያ ካልሆነ በስተቀር።
አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትንሳኤ ከዘራፊው የወያኔ ሥርዐት መወገድ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑን ያምናል! ስለዚህም ህዝባችን ወያኔን ለማስወገድ የተጀመረውን ትግል በነቂስ ለመቀላቀል ዛሬውኑ እንዲነሳና ከጎናችን እንዲሰለፍ የማያቋርጥ ጥሪውን ደግሞ ደጋግሞ ያስተላልፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment