August 26,2015
በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች በየክልሉ በተቋቋሙ እስር ቤቶች ዉስጥ ክስ ሳይመሰረትባቸዉ እንደሚታሰሩና፤ ግርፋት ሰቆቃና ድብደባ እንደሚደርስባቸዉ አልፎ ተርፎም እንደሚገደሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰወረ አይደለም።
በኢትዮጵያ የህግ አስፈፃሚ አካላት የሆኑት ፖሊሰ፤ ፍርድ ቤቶችና ወህኒ ቤቶች ኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ሙሉ በሙሉ ከመዉደቃቸዉ ሌላ የአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት እንኳ ሊያዝዛቸዉ እንደማይችል በተለያየ ወቅት ተመስክሯል።
የፖሊስ ጣቢያዎች፤ የአስተዳደር ጽ/ቤቶች፤ወታደራዊ ካምፖች፡ ህጋዊ እስር ቤቶች፡ ሚስጢራዊ ስዉር እስር ቤቶች፡ በሀገረ ማርያም፤ ሁርሶ፤ ዴዴሳ፤ አጋርፋ፤ ዝዋይ፤ ጦላይ፤ቃሊቲ፤ማእከላዊ፤ በየክልል ወህኒ ቤቶችና በተለይ በአዲስ አበባ ዘመናዊ ቪላዎች በመከራየት በእስር ቤትነት ከመጠቀሙም በላይ በእስረኞች ላይ ሰቆቃ፤ ግርፋትና ድብደባ መፈፀሚያ በማድረግ እንደሚገለገልባቸዉ ይታወቃል።
የአለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ድንጋጌም ሆነ ህወሀት/ኢህአዴግ ያፀደቀዉ የአገሪቱ ህገ መንግሰት በማንም ሰዉ ላይ ሰቆቃ፡ ግርፋትና ድብደባ እንዲሁም ጭካኔ የተመላበት ኢ-ሰብኣዊ ድርጊትም ሆነ ስብዕናን የሚያዋርድ ተግባር ሊፈፅምበት እንደማይገባ ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ ይህ በእስራት ወቅትና ከእስራት ዉጭ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች፤ የደህንነት፤ የፖሊስ፤ የድርጅቱ ካድሬዎችና ወታደሮች አማካይነት በመላዉ የአገሪቱ ክልሎች በዜጎች ላይ የሚፈፀም የየቀኑ ተግባር ነዉ። ይህን በመፈፀም ማእከላዊ የምርመራ ድርጅት በመባል የሚታወቀዉ እስር ቤትና የደህንነት ተቋም የናዚ ጀርመን ይጠቀምባቸዉ ከነበሩት የማጎሪያ ካምፖች ያልተናነሰ እንደሆነ ይነገራል።
ዜጎች በኤሌክትሪክ ገመድና በሌሎችም ነገሮች በመጠቀም እጆቻቸዉ በሰንሰለትና በካቴና ታስረዉ ግድግዳ ላይ በተመቱ ምስማርና ችካሎች እንዳይንቀሳቀሱ ተወጥረዉ፤ የዉስጥ እግራቸዉንና መላ አካላቸዉን በጠቅላላ አዕምሯቸዉን እስኪስቱ ድረስ መደብደባቸውና የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ሱዳን፤ የመን፤ ኬንያ፤ ሶማሊያና ጅቡቲ ድረስ ድንበር ዘልቀዉ በመግባት የሚፈልጓቸዉን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አፍነዉ መዉሰዳቸዉና ሊያመጧቸዉ ያልተሳካላቸዉን እንደሚገድሉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ ያዉቀዋል።
የመንግስት የፀጥታ አስከባሪዎች ሌሎች ታጣቂዎች በቀን በአደባባይ የመንግስትን የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚቃወሙ ናቸዉ በሚሏቸዉ ላይ ግድያ እስከመፈፀም ያልተገደበ መብት አላቸዉ፤ በእያንዳንዱ የገበሬ ማህበር ቤት እየዞሩ ኢህአዴግን መምረጥ እንዳለባቸዉና ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን ምንም አይነት የመንግስት አቅርቦት እንደማያገኙ፤ ቤተሰቡ የመስራትም ሆነ የመማር እድል እንደማይኖረዉ በግልፅ የተነገረበት ሁኔታ እንደነበርና ኢህአዴግን ያልደገፉ ድሃ ገበሬዎች ማዳበሪያና ሌሎች የእርሻ ግብኣት ድጋፎች እንዳይደረግላቸዉ መከልከላቸዉን የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች አጋልጠዋል።
ኢህአዴግ የፖለቲካ አላማዉን ለማስፈፀም ላለፉት 24 አመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ በደህንነትና በወታደራዊ ተቋሞቹ አማካይነት የአገሪቱን ፖለቲካ በግሉ ለመቆጣጠር፤ በጎሳና በዘር ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም በማካሄድ፡ በፖለቲካና በሲቪክ ማህበራት ድርጅቶችና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈፅማቸዉ የነበሩትና ዛሬም የሚፈፅማቸዉ የሽብር ተግባሮች ለመሆናቸዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያዉቃል።
እናም የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሰት “በሽብርተኝነት” “የአገርን ሰላም በማደፍረስ” “ህገ መንግስታዊዉን ስርአት በመናድ ” “በዘር ማጥፋት” “በአገር መክዳት” ወዘተ… የሚሉትን የወንጀል ክሶች የሚጠቀምበት ለምን አላማ እንደሆነ ግልፅ በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሳይበረከክ በኢህ አዴግ ስርዓትና ተቋማቱ ላይ የጀመረውን ተቃውሞውን በማጠናከር ማስቀጠል ይግባል።
No comments:
Post a Comment