Saturday, July 25, 2015

ኦባማ፡ “በንግግር (ወሬ) A፣ በተግባር D” ኦባንግ ሜቶ

July 25,2015
“በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑብን”
obang voa4

ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ውጤት ቢሰጥ በእስካሁኑ የአፍሪካ ፖሊሲያቸው በንግግር (በወሬ) ደረጃ A በተግባር ግን D እንደሚሰጧቸው ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ፡፡ አፍሪካውያንም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ምዕራባውያን ዕንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠቡ አስረዱ፡፡
በአሜሪካ ድምጽ የStraight Talk Africa አዘጋጅ ሻካ ሳሊ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የአፍሪካ ጉብኝት በተመለከተ ከሁለት ቀናት በፊት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ሦስት አፍሪካውያንን ተጋብዘው ነበር፡፡ ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሴራሊዮኑ ፕሮፌሰር አብዱል ካሪም ባንጉራ፣ የአፍሪካ ስደተኞች ስብስብ ኃላፊ ጋናዊው ኒ አኩቴ እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው ኦባንግ ሜቶ ነበሩ፡፡
በእስካሁኑ የአፍሪካ ፖሊሲያቸው ለፕሬዚዳንቱ ምን ውጤት ትሰጣላችሁ በማለት ሻካ ላቀረበው ጥያቄ ዶ/ር አብዱል D እሰጣቸዋለሁ፡፡ ይህም በተለይ ከአፍሪካ ጋር ስላለላቸው ግንኙነትና እንዴት የአፍሪካ ፖሊሲያቸው ውጤት አልባ እንደሆነ በመመልከት ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ያሉበትም ምክንያት በርካታ ሰዎችን በመጠየቅ ባደረጉት ጥናትና ምርምር እንደሆነ ሆኖም አሜሪካ ከኩባ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት በማለዘብደረጃ የተጫወቱ ሚና ከዚህ የወረደ ነጥብ እንዳያገኙ እንደረዳቸው ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡
ጋናዊው  አኩቴ ግን ለኦባማ A እንደማይሰጡ ከተናገሩ በኋላ በዝርዝር ሳይጠቅሱ ፕሬዚዳንቱ ላከናወኑት ተግባራት ግን ተመጣጣኝ ነጥብ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የትኛውም ነጥብ ይህ ነጥብ ወይም ደረጃ ለምንድነው የሚሰጣቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢና አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡obang voa2
ኢትዮጵያዊው ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ውጤት ስጡ ቢባሉ “በንግግር (በወሬ) A በተግባር ግን D” እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ ከዓመታት በፊት ጋናን በጎበኙ ወቅት “አፍሪካ የሚያስፈልጋት ጠንካራ መሪዎች ሳይሆን ጠንካራ ተቋማት” ነው ማለታቸውን ከጠቀሱ በኋላ “በአሁኑ ወቅት በአገሬ ያለው አገዛዝ በምርጫ መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ” የሚል መሆኑን አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተቋማት መቀጨጭ ወይም መምከን ምን ደረጃ እንደደረሰ ሲያስረዱም “በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት፣ ለሴቶች መብት፣ ለህጻናት መብት፣ ለዕርቅ፣  መሥራት ሕግን እንደ መጣስ ተቆጥሮ” ለእስር እንደሚዳርግ አስረድተዋል፡፡ አሜሪካ የተመሠረተችባቸው እነዚህ እሴቶች በኢትዮጵያ ዋጋ የሌላቸው መሆኑን ሲገልጹ ዋንኛው ምክንያት ጠንካራ ተቋማት በኢትዮጵያ እንዳይኖሩ አገዛዙ የመያዶች ሕግ በመባል የሚታወቀውን በማወጅ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖርና ሊቃወሙት የሚችሉትን ሁሉ በሕገወጥነት በመፈረጁ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከዚህ ሌላ በአገራቸው ጠንካራ ተቋም እንዳይመሠረት ዕንቅፋት የሚሆን የጸረ አሸባሪነት ሕግ በሥራ ላይ መዋሉን “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት በተመለከተ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ዋናው ዓላማ የአሸባሪነት ጉዳይ ተብሎ መጠቀሱ ኦባማ ለአፍሪካ ያላቸውን አመለካከት ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህም ማለት ማንኛውም የአፍሪካ መሪ ሕዝቡን እያሸበረ የአሜሪካንን ጥቅም እስካስከበረ ድረስ የዜጎች መብት መረገጥ ነገር ለአሜሪካም ሆነ ለምዕራባውያን ከጉዳይ እንደማይቆጥሩት የጋራ ንቅናቄው መሪ ኦባንግ አስረድተዋል፡፡ “ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ ጠንካራ ተቋማት መመሥረት የሚችሉ ብሩህ ኅሊና ያላቸው ጦማሪያንና ጋዜጠኞችና የነጻነት ድምጾች በአሸባሪነት ተፈርጀው በእስር የሚማቅቁት” በማለት ኦባማ በንግግር ደረጃ ለጠንካራ “ተቋማት መመሥረት ቢያወሩም በተግባር ግን የከሰሩ ናቸው፤ (የአፍሪካ ኅብረትን ሰብስበው ሲያናግሩም) የሚናገሩት ከጠንካራ መሪዎች ጋር ነው” ብለዋል፡፡
ኦባንግ ቀጠሉ “ዛሬ ኢትዮጵያ የምትተዳደረው በአፓርታይድ ዓይነት ዘረኛ አገዛዝ ነው፤ (ወደ አዘጋጁ ሻካ ሳሊ በመጠቆም) ለምሳሌ እኔና አንተ እዚህ አሜሪካ አገር በመጀመሪያ ሰዎች ነን፤ ወንድማማች ነን እንጂ ኢትዮጵያዊ ወይም ዑጋንዳዊ ተባብለን በዘርና በአካባቢ የተለያየን አይደለም፤ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ይህ አይደለም፤ አንዲያውም በቅርቡ ከአሜሪካ የኔብራስካ ጠቅላይ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የሄደች አንዲት እህት መታወቂያ ካርድ ለማውጣት ስታመለክት ዘርሽ (ብሔርሽ) ምንድነው ተብላ ስትጠየቅ የሁለት ቅልቅል በመሆኗ ይህ ነው ብላ መናገር እንደማትችል፤ ኢትዮጵያዊ መሆኗን ብታስረዳም የግድ እንደሆነ ከኃላፊዎች ሲነገራት በማመልከቻው ቅጽ ላይ አማራ + ኦሮሞ = ______ በማለት እናንተው ሙሉት በሚል ክፍት አድርጋ ትታዋለች፤ (በኢትዮጵያ ሰው ከመሆንህ በፊት ዘርህ ይቀድማል) የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት የሚባለው ከደርግ ለመታገል በረሃ ወረደ፤ ደርግ ከተወገደ በኋላ ኢህአዴግ በማለት ራሱን የቀየረ በመምሰል አሁንም (ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም) እየገዛ ይገኛል፤ ዛሬ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በህወሃት ቁጥጥር ሥር ውሎ ዜጎች ይበረበራሉ፤ ሚሊታሪው፣ ኢኮኖሚው፣ ደኅንነቱ፣ በሙሉ በህወሃት ቁጥጥር ሥር ነው፤ በመሆኑም ኦማባ እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ የተከተሉት ፖሊሲ ይህንኑ የሚደግፍና ከሕዝቡ ያልወገነ ነው” በማለት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡
ጠያቂው ሻካ ሳሊ “እርስዎ ከበርካታ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎችና ከፍተኛ የፖለቲካ ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው ይገናኛሉ፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ንግግር ወቅት እነዚህ ባለሥልጣናት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ስላላት አቋም በተመለከተ ምንድነው የሚሉት” በማለት ለኦባንግ ላቀረቡላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በየጊዜው የሚሉት በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም ነው፤ እኔ የማስረዳቸው ደግሞ አገዛዙ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር በስልት እንዴት እንዳደረገ ነው፤ ኢንተርኔቱን ተቆጣጥረውታል፤ ከሃያ ዓመታት በላይ መንግሥት የሌላት ሶማሊያ በኢትንተርኔት አጠቃቀም ኢትዮጵያን ትበልጣለች፤ በየጊዜው የሚነሱ የነጻነት ድምጾች ታፍነዋል፤ ታስረዋል፤ ኢትዮጵያውያን በውጪ መደራጀት ይችላሉ ሆኖም በአገር ውስጥ (ህወሃት) ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር አድርጓል” በማለት በየጊዜው ለሚያገኟቸው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደሚያስረዱ ጠቁመዋል፡፡
ፕ/ር አብዱል በተራቸው በሙያቸው ባደረጉት ጥናት ኦባማ ለአፍሪካ እጅግም የበጀ ወይም በዋንኘነት የሚጠቀስ ተግባር አለመፈጸማቸው ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አብዱል ማመጣጠን እንዳለባቸው አዘጋጁ ሻካ ሳሊ በመጥቀስ ለአብነት ያህል በራሳቸው በፕ/ሩ የትውልድ አገር ሴራሊዮን የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ በመከላከል ኦባማ ያደረጉት አስተዋጽዖ ታላቅ እንደሆነ የሴራሊዮኑ ፕሬዚዳንት መናገራቸውን፣ እንዲሁም በላይቤሪያ ኦባማ የፈጸሙት ተግባር ተጠቃሽ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ሰርሊፍ የመሰከሩ መሆኑን ከዚህም ባሻገር ወጣት አፍሪካውያንን ወደ አሜሪካ እየመጡ እንዲማሩ በማድረግ ለአህጉሪቱ የወደፊት ራዕይ የሚበጅ Young Africans Leadership Initiative (YALI) ፕሮግራም መመሥረታቸው ሊጠቀስ እንደሚገባው በቃለምልልሱ ወቅት አውስቷል፡፡
ፕ/ር አብዱል ከበፊቱ ጠንከር ባለ ሁኔታ እንዲያውም ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬኒያም ሆነ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት የደመቀ አከባበርም ሆነ ዳንስና ጭፈራ እንደማያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ ለሥራ የመጡ ከሆነ ያላቸውን ጊዜ ሁሉ ምን መደረግ እንዳለበት በዝርዝርና ነጥብ በነጥብ ከአፍሪካውያን ጋር ጊዜያቸውን በሙሉ ማዋል ይገባቸዋል፡፡ ጊዜው የጭፈራና የዳንስ ሳይሆን የሥራና ተግባራዊ ለውጥ የሚታቀድበት ሊሆን እንደሚገባ ፕ/ር አብዱል አስረድተዋል፡፡
obang voa5“ፕሬዚዳንት ኦባማ ይህንን ፕሮግራም ቢመለከቱ ለእርሳቸው የሚነግሩት መልዕክት ምንድነው? ካሜራውን እየተመለከቱ መልዕክት አስተላልፉ” በማለት ሻካ ለኦባንግ ሜቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ጥቁሩ ሰው “ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ስለሚቀጥለው ሌጋሲዎ የሚያስቡ ከሆነ እና መታወስ፣ መታሰብ የሚፈልጉ ከሆነ ሲታወሱ ሊኖሩበት የሚችልበት አንዱ መንገድ ለአምባገነኖች በሠሩት ተግባር ሳይሆን ለሕዝብ በሚያከናውኑት ሥራ ነው፤ የአፍሪካ ኀብረት 50ዓመታት እለፎታል በአኅጉሪቷ (ፖለቲካ) ላይ ያመጣው ይህ ነው የሚባል ለውጥ የለም፤ ስለዚህ በሕዝብ ላይ ኢንቨስት ያድርጉ፤ (ከሕዝብ ጋር ይቁሙ)፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማነቆ የሆኑት የጸረ አሸባሪነት ሕግ እና የመያዶች ሕግ እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሻሩ ማድረግ ይችላሉና በዚህ ላይ ይሥሩ፤ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አሜሪካ እንዳደረገችው በኢትዮጵያም የሲቪክ ማኅበረሰቦች (መያዶች) በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና ሕዝብን በማንቃት ረገድ ተግባራቸውን እንዲወጡ እርስዎም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ይቁሙ” በማለት በቀጥታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሲቀጥሉም “የኢኮኖሚ ዕድገት አለ ይባላል፤ የሚታይ እንቅስቃሴ አለ፤ መንገድ ይሠራል፤ ፎቅም ይገነባል፤ ሆኖም የኢኮኖሚን ዕድገት በፎቅና መንገድ ሥራ መለካት አይቻልም፤ ኢኮኖሚው በእርግጥ እያደገ እየተመደገ የሄደ ከሆነ ለምንድነው ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ቀይባህርን አቋርጠው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚሰደዱት፤ ከአጠቃላዩ ሕዝብ 6 በመቶ በማይበልጥ አናሳ ብሔረተኞች ቁጥጥር ስር ስለሆነ አድጓል የሚባለው ኦኮኖሚ ይህ ነው የሚባል ለውጥ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ሊያመጣ አልቻለም” በማለት ኦባንግ ሜቶ በመላው ዓለም ፕሮግራሙን ለሚከታተሉ የአገራቸውን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም የጋራ ንቅናቄው ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ “አፍሪካውያንም ሆነ ኢትዮጵያውያን ኦባማን ወይም አሜሪካንን ወይም ምዕራባውያንን ነጻ እንዲያወጡን እየለመንን አይደለም፤ ራሳችንን እንዴት ነጻ እንደምናወጣ እናውቃለን፤ ነገር ግን (ከአምባገነኖች ጋር በማበር) በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑብን” በማለት ግልጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

No comments:

Post a Comment