June 9, 2015
አዲስ (ከሲልቨር ስፕሪንግ)
ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ቀናዒነት ስላለኝ በቅርብ እርቀት እከታተላለሁ ። ከአባላቱም ጋር በስደት የቅርብ ወዳጅነት መስርቼ ከልብ ትርታቸው ጋ የእኔን አዛምጄ ፣ በአዘኑበት አዝኜ ፣ ሲደሰቱ ተደስቼ ለማንኛውም ጥሪያቸው በግምባር ቀደምትነት ምላሽ በመስጠት በሁሉም ቦታ ታድሜ እነሆ ዘመናት ተቆጠሩ።
እማውቀው – እኔ ከብዙዎቹ አንዱ እንደሆንኩ ነው ። የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ በቁጭት አክብሮትና አድናቆትን እንደተጐናፀፈ ከትውልድ ትውልድ እያንፀባረቀ ቢመጣም ፤ የኋላ ኋላ ዕጣ ፋንታው ግን መበተን ፣ መሰደድ ፣ ያለ ፍርድ ለዘመናት መታሰርና ፣ ለሞት ፍርድ ተላልፎ መሰጠት ሆነ ። ይህም እንኳ ሳያግደው ዝናው በጠላቶቹም ጭምር ሳይቀር ከዳር እስከዳር እንደናኘ ዛሬም አለ።
ታድያ ዛሬ የዚህን ታላቅ ወታደራዊ ተቋም ታሪክ በመፅሃፍ ተፅፎ ማየት በህይወት ላሉት ክብር ፣ ለሰፊው ህዝብ ማስታወሻ ፣ ለመጪውም ትውልድ መማሪያ መሆኑ የማንኛውም ቅን ዜጋ ህልም ነው ፤ ለአባላቱና ለቤተሰቦቻቸውም ደግሞ ኩራትና እፎይታ ነው።
ለዚህም ነበር ይህንን ታላቅ አላማ ሰንቀው ለተንቀሳቀሱ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንጋፋ አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፍ የተሰጠው ። ድጋፍ በገንዘብ ፣ ድጋፍ በማቴሪያል ፣ ድጋፍ በሞራል …. ወዘተ።
የታሪክ መፅሃፉን እውን ለማድረግ ለዘመናት ሲዳክሩ የነበሩት ፣ በአየር ኃይሉ ውስጥ ቀደምትነት ያላቸው የተከበሩ ፣ ስመጥርና ገናና የመሆናቸውን ያክል ፤ አጨራረሱ ላይ ግን በፊት አውራሪነት በኢትዮጵያችን እየተለመደ የመጣው የገዢው ስርዓት ተዋላጆች ዋነኛ ባለቤት እየሆኑ የብዙሃኑን ቀና ግምት ወደ ትዝብት ፣ ሃዘንና ጥርጣሬ የወሰደ አልነበረም ብሎ መደምደም አይቻልም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የመፅሃፉ ይዘት በምን መልኩ ይቀርብ ይሆን የሚለው ከአገር ቤት እስከ ዲያስፖራው የቀድሞው አባላቱ መካከል የተለያየ ሃሳብ ከየአቅጣጫው ተነስቶ በመግባባትም ፣ ባለመግባባትም እንደተናጠ ነበር መፅሃፉ ከመደብር ሳይሆን በውስጥ አወቆች እዚህ ደጃችን የደረሰው።
ስለዚህ የጥያቄውና የውይይቱ መሰረተ ሃሳብ ለምን የአየር ኃይሉ የታሪክ መፅሃፍ ተፃፈ የሚል አይመስለኝም ። በፍፁም አደለምም ። የተወሰኑ ግለሰቦች ግን ለምን የአየር ኃይል ታሪክ ተፃፈ የሚል ጥያቄ እንደተነሳ አስመስለው ለማቅረብ ሲታገሉ በቅርብ አስተውያቸዋለሁ ። ጥያቄው ለምን መፅሃፉን ወደ ጠላት ጉያ ከተቱት (ምክንያቱም የአየር ኃይልን ቁስልና ጥቃት ለመግለፅ አመቺ ቀጠና ስላልመረጡ) ነው እንጂ ለምን ታሪኩ ተፃፈ አይደለም ብዬም ደጋግሜ አስረድቻቸውም ይህንን ይዘሉታል ። ስለዚህ ሆን ተብሎ የሚሰራ ነገር አለ ማለት ነው።
እንደ ግለሰብ ማንኛውም ሰው ፖለቲካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ወዘተ አመለካከቶች ሊኖሩት ይችላል ። ይህም ሊከበርለትና ሊበረታታም ይገባል ። ሆኖም ግን የዚህ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ አካሎች የኢትዮጵያ አየር ኃልይ አባላት ናቸው ። ባለቤቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ። እንግዲያውስ በዚህ መፅሃፍ ዝግጅት ዙርያ የተለያየ ሃሳብ ቢነሳ ሊደመጥና ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ትኩረት ተሰጥቶት በሃሳብ ተፋጭቶም ነጥሮ ሊወጣ ይገባዋል ፤ ለመፅሃፉም ግብዓት አስተዋፅዖው ቀላል አይሆንም ፤ የታሪኩንም ሙልዓዊነት ሲያዳብረው ተዓማኒነቱንም ከፍተኛ ያደርገዋል ። ይህንንም ስል እንዲያው መቋጠሪያ በሌለው ውዝግብ ውስጥ ገብቶ መቧቸሩ አስፈላጊ ያለመሆኑን እየተረዳሁ ቢያንስ ግልፀኝነትና ታማኝነት በተሞላበት ሁኔታ በተደራጀ መልኩ (በየአካባቢው) በቡድን ኰፒውን የማየትና ሃሳብ የመለዋወጥ ዕድሉ ሊኖር በተገባ ነበር ። አለፍም ሲል በእድሜም ሆነ በልምድ የተከበሩ የሰራዊቱ አባላት እንደዚህ አይነቱን የግራ ቀኝ የሃሳብ ፍጭት ሃላፊነት ወስደው ማወያየትና ሁሉንም በተቀራረበ ግንዛቤ ሸክፎ በአንድነት እንዲጓዝ ማድረግ ታሪክ የጣለባቸው ትልቅ ሃላፊነት መሆን በተገባው ነበር።
ለመሆኑ ችግሩ ምንድነው ? ለምንስ ወደ አላስፈላጊ ጭቅጭቅ በሚል መሸፈኛ እነዚህ ከስርዓቱ ጋር ወስደው ያጣበቁን ሰዎች የፈለጉትን ለማድረግ በር የሚከፍት አካሄድ ተመረጠ ? ትላልቅ የሚባሉት ሰዎችስ ሃላፊነት በሚሰማው መልኩ መሃል ገብተው ማወያየትና መዳኘት ለምን ወኔ ከዳቸው ? ይህ ሃላፊነት ተወስዶ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ዛሬ ላይ ለተነሳው የክህደት ጥያቄ ባልተጋለጠን ነበር።
አገራችን ኢትዮጵያ በረዥም ዘመን ታሪኳ ውስጥ አሁን እንዳለችበት ጊዜ ችግር ገጥሟት አያውቅም ። ለእናት አገራቸው ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በሙያቸው እያገለገሉ ሲዋደቁ የነበሩ ፣ ጊዜው በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታነፁ ፣ በአፍሪካ ግምባር ቀደሙን አየር ኃይል የአኩሪ ገደል ባለቤት ያደረጉ ፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ ለኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ጥንስስና መሰረት የጣሉ ፣ ለተለያዩ ሲቪል ተቋማትና አምራች ድርጅቶች አመራር መፍለቂያ የሆኑ ፣ በጤና ፣ በስፖርት የአገሪቷን ስም በዓለም እንዲናኝ ያደረጉ ወዘተ ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ሲዋረዱና እንዲሸማቀቁ ሲደረግ በዓይናችን እንድናይ የተገደድንበት ዘመን ላይ ነን ያለነው።
በኢትዮጵያ የአብዮት ዘመንም ተነሳ ተራመድ ብለው በግንባር ቀደምትነት የህዝብን የለውጥ ፍላጐት በመምራት የህዝብ ዕምባ ጠባቂ በመሆን ያገለገሉ ፤ ረዥሙ የእርስ በርስ ጦርነትም ማብቂያ ይበጅለት ብለው በግንቦት 8፣ 1981 ብርቅዬና ውድ አመራሮቻቸውን የገበሩ ፤ ለእናት አገሩ ዘብ በመቆሙና በማገልገሉ ጀግኖቹ አባላቱ ተዋርደው ፣ ታስረው ፣ ተሰደው ፣ ተገልለውና ተሸማቀው እንዲኖሩ የተደረገበት ። የሞት ፍርድ እንኳ ሳይቀር የተበየነበት ዘመን ነው።
ዛሬም እንኳ ይህቺን ፅሁፍ እየጫጫርኩ ባለሁበት አጋጣሚ የግንቦት 20 ድል እየተከበረ ስለ ጨፍጫፊው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሲያላዝኑ ይሰማል ። ሌላው ቢቀር በአንድ ወቅት አየር ኃይሉን እንዲጐበኙ ለተደረጉት አርቲስቶች እንዳሉት የሞተ ፣ የተማረከ ፣ የተንኰታኰተና የተሽመደመደ አየር ኃይል እንደተረከቡና ዛሬ ግን እነሱ አየር ኃይሉን ከፍተኛ ደረጃ እንዳደረሱ ሲገልፁ መስማት ምንኛ ያማል ? እነዚህ የመፅሃፉ አዘጋጆች እንደዚህ አይነቱ የመንግስት ዘለፋ ሊሞቃቸውም ሆነ ሊበርዳቸውም እንዳልቻለ ማስተዋል ገረሜታን መፍጠሩ አልቀረም።
ታድያ ዛሬ መነሻው በተድበሰበሰ ሁኔታ ተጀቡኖ ፣ በአሳዳጆቹ ዳንኪራ ቤት (ሸራተን) በተሰጠ የችሮታ ድግስ የተጀመረው የመፅሃፍ ዝግጅት ፣ የሌላውን ሃሳብ ባለማዳመጥ በድንገት የምረቃው ዜና አሁንም በአሳዳጆቹ አጋፋሪነት መሰማቱ ከፍተኛ ሃዘንና ድንጋጤ ቢፈጥር ምን ይገርማል ? ክህደትስ ነው ቢባል ምን ያጠራጥራል?
ደግሞስ የመፅሃፉ አወጣጥና አካሄድ አላግባብ በማን አለብኝነት ብሎ መተቸት ከመፅሃፉ ይዘት ጋር ምን ያገናኘዋል ? አዎ ወደ አይቀሬው የመፅሃፉ ይዘት ወደድንም ጠላንም እንገባለን! አወጣጡ ግን የተሽመደመደ ፣ በክህደት የተሞላ ፣ ለአፍራሾቹ በበቂ ሁኔታ ምላሽ ሊሰጥ የማይችል መሆኑን በድፍረት እናገራለሁ ። ወደፊት በመፅሃፉ ባህሪና ይዘት ላይ ብዙ ለማለት እንድችል ከወዲሁ ይህንን ሳልጠቁም ማለፍ ስላልፈለኩ ነው።
No comments:
Post a Comment