June29,2015
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ እስር ላይ ቆይተው ሰኔ 15/2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት እንዲፈቱ ተወስኖላቸው ሰኔ 16/2007 ዓ.ም ከእስር ቤት ሲወጡ እንደገና በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት ወንይሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤትሄልየም አካለወርቅ ዛሬ ሰኔ 22/2007 ልደታ ፍርድ ቤት 11ኛ ምድብ ችሎት ቀርበው ቀደም ሲል ‹‹ሁከትና ብጥብጥ አስነስተዋል›› በሚል በተከሰሱበትና ከእስር በተለቀቁበት ክስ ላይ ይግባኝ ተጠየቀባቸው፡፡
አቃቤ ህግ እነ ወይንሸት የዋስትና መብታቸውን ተነጥቀው ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቀ ቢሆንም ዳኛዋ ‹‹በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ ከእስር የተፈቱ በመሆናቸው ዋስትና ሊከለከሉ አይገባም፡፡›› ብለዋል፡፡ ዳኛዋ እነ ወይንሸት እንደተለቀቁ እንጅ በእስር ላይ መሆናቸውን እንደማያውቁ ገልጸው 3 ወር ተፈርዶበት ቂሊንጦ የሚገኘው ማስተዋል ፈቃዱ ባለመቅረቡ፣ ከእሱ ጋር ረቡዕ ሰኔ 24/2007 ዓ.ም ቀርበው ክርክር እንዲጀምሩ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡ ሰኞ ሰኔ 29/2007 ዓ.ም ውሳኔ እንደሚሰጡም አሳውቀዋል፡፡
ሰኔ 15/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ኤርሚያስ ፀጋዬ በነፃ፣ እንዲሁም ወይንሸት ሞላና ዳንኤል ተስፋዬ ሁለት ወር እስር ተወስኖባቸው ሁለት ወር በመታሰራቸው እንዲፈቱ ተፈርዶላቸው ከእስር ሲለቀቁ እስር ቤት በር ላይ በፖሊስ ተይዘው ወደ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ መዛወራቸው ይታወቃል፡፡ ወይንሸት፣ ኤርሚያስና ዳንኤል ሰኔ 19/2007 ዓ.ም በቄራ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ‹‹ከእስ እንዲለቀቁ በተወሰነላቸው ወቅት ምስክሮችና የምስክሮቹ ጓደኞች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ አድርሰውብኛል›› የሚል አዲስ ክስ አቅርቦባቸው 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ፡፡ በዚህ አዲስ ክስ ላይ የፖሊስን ምስክር ለመስማት ነገ ሰኔ 23/2007 ቄራ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
No comments:
Post a Comment