Wednesday, May 6, 2015

የኢህአዴግ መሰረተ ልማት ግንባታ ለፖለቲካ ፍጆታ እንጂ ለህዝብ ጥቅም ሲውል አልታየም!!

May 6,2015

amh editorail
በማንኛውም አገር የመሰረተ ልማት ግንባታ ወሳኝ ነው። ነገር ግን የሚሰሩት ግንባታዎች ለፖለቲካዊ ጥቅምና ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ተብሎ የሚሰሩና የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ የማይለውጡ ከሆኑ ግን መሰረተ ልማት ብሎ ከመጥራት ይልቅ የሙስና እና የብልሹ አሰራር መሰረተ ተብሎ ቢገለፅ ይቀላል።
የአንድ አገር መሰረተ ልማት የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ እድገት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ፤ በህዝቡ ውስጥ ያለው የኑሮ ሁኔታ ልዩነት የሚያጠብና ሁሉም ዜጎች እኩል ሆነው ለመኖር የሚያስችል መሆን ይኖርበታል።
ባሁኑ ግዜ በኢህአዴግ አመራር አገራችን እየተካሄደ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ። የሁሉንም ከተሞች እድገት በእኩል የማሳደግ ፋላጎት ሳይሆን ለአንዳንድ ከተሞች ብቻ ልዩ ትኩረት የሚያደርግና በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት ግብታዊ በሆነ መንገድ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስገኘት ብቻ ተብሎ የሚካሄድ የግንባታ ስራ በመሆኑ እስካሁን ድረስ አመርቂ የሆነ ውጤት ማምጣት አልቻለም።
በሌላ በኩል ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው የመሰረተ ልማት ሁኔታ። የህዝቡ ብዛት ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ማደረግ ነው፣ የሚገነባው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከህዝቡ ብዛት የሚመጣጠን ካልሆነ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ግንባታዎች በረጅም ግዜ ታይተው የሚሰሩና የሚፈጸሙ ካልሆኑ የህብረተሰቡን ፍላጎት ሟሟላትም አይችሉም። በተለይ ያገራችን ህዝብ ከ 20 እና 30 ዓመት በኋላ በእጥፍ ማደግ እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት የሚካሄድ የልማት ሁኔታ ከሌለና ከግዜው ጋር እድገት እያረጋገጠ የሚጓዝ መሰረተ ልማት መሆን ካልቻለ ችግሩ አደገኛ ነው የሚሆነው።
ከዚህ በመነሳት የኢህአዴግ ስርዓት በተለይ በከተሞቻችን ውስጥ የመኖሪያ ቤት ግንባታና የመንገድ ስራዎችን በተመለከተ ከተሰሩ በኋላ አስፈላጊውን አገልግሎት ሳይሰጡ ስለሚበላሹ የከተሞቹ ዘመናዊነት መበላሸታቸውን ሳይበቃ ያለ በቂ ጥናትና ክትትል የተሰሩትን መሰረተ ልማቶች እንደገና ለመጠገን እጅግ በርካታ ወጪ ስለሚደረግላቸው ለሌላ ግንባታ መሆን የሚገባውን ያገር ሃብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲባክን ማየት የተለመደ አሰራር ሆኗል።
ከተሞቻችን ማደግ ከሚገባቸውን እድገትና ስልጣኔ አኳያ ሲታይ ምንም እንኳን እጅግ በርካታ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም በቂ ዝግጅት ተሰጥቶት በሰለጠነና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መሰራት ሲገባቸው ለከተሞቹ ቀጣይ እድገት ግምት በማያስገባና በሚያበላሽ መንገድ እየተካሄደ በመሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታው ለወደፊቱ ትልቅ ጉዳት ማስከተል እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም።
ለማጠቃለል የኢህአዴግ ስርዓት የሚያካሂደው የመሰረተ ልማት ግንባታ ባለሙያዎች የተደገፉ ባለመሆናቸውና። ሁሉም የግንባታ ስራዎች በቂ ሞያ በሌላቸው የስርዓቱ አገልጋዮች እየተመራ በመሆኑ አጥጋቢ ውጤት ማግኘት አልተቻለም እየታየ ያለው የግንባታ ሁኔታም ቢሆን የህዝቡና የአገሪቱን ጥቅም ለማስከበር ታስቦ ሳይሆን የስርዓቱን ፖለቲካዊ ስልጣን ለማቆየት ታስቦ እየተካሄደ ያለ መሆኑንና በህዝቡም ላይ የመጣ አንዳችም ለውጥ እንደሌለ ማወቅ ያስፈልጋል።
ዴምህት

No comments: