Sunday, May 17, 2015

" ኢህአዴግ ጠመንጃና ምርጫ ቦርድን እንደ ምርኩዝ ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ "

May 17,2015
ዶ/ር መረራ ጉዲና
Minilik Salsawi's photo.
በየቦታው ትንንሽ ጦርነት የሚመስሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ የኛ ቅስቀሳ በተሳካ ቁጥር የእነሱ ብስጭት ይግል ነበር፡፡ ካድሬው ለሆዱ፣ መንግስት ለስልጣኑ በሚገባ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይሄ አመላካች ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ካድሬው ሽጉጥ ታጥቆ፣ ጠመንጃ ይዞ እገባለሁ አትገባም የሚል ግብግብ እስከመፈጠር ደርሷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መኪናዎቻችን እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው ተወዳዳሪ እጩዎቻችን ሳይቀሩ ተደብድበዋል፡፡ በአባላቶቻችን ላይ እስር፣ ድብደባና ወከባ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: በዘንድሮ ምርጫም ኦሮምያ ላይ እናሸንፋለን ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡
በኦሮሚያ ብዙ አካባቢዎች ሰፋፊ ህዝባዊ ስብሰባዎችን አካሂደናል፡፡ ባኮ፣ አምቦ፣ ጀልዱ፣ ጊንጪ የመሳሰሉት አካባቢዎች እኔ የተገኘሁባቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ በየስብሰባው ከ60ሺህ በላይ የሚገመት ህዝብ ነው ድጋፉን ሲገልፅልን የነበረው፡፡ በተለይ የወጣቱ ድጋፍ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ “ከዚህ በኋላ የፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዝ ይብቃን” የሚሉ ህብረ ዝማሬዎችን እያሰማ ነው ህዝቡ በየስብሰባው ላይ ሲታደም የነበረው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲታዩ ቅስቀሳው ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ኦህዴድ፣ በዚህ መልኩ ወጣቱ ለኛ ድጋፍ ይሰጣል ብሎ የገመተ አይመስለንም። አሁን ታዲያ የድንጋጤ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሃረርጌ፣ በባሌ እና በሸዋ አካባቢዎች አባሎቻችንን ማሰር፣ መደብደብና ማዋከብ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የቅስቀሳ መኪናዎቻችንን መስተዋቶች በድንጋይ የመስበር፣ መኪኖችን በቡና ቤቶች አካባቢ ማሳደር እንዳንችል የማድረግ ሁኔታዎች በስፋት ተስተውለዋል፡፡ ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡
በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖችና አካባቢዎች ተመሳሳይ የሆነ አቀባበል ከህዝቡ አግኝተናል፡፡ በአጠቃላይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይ እና በአዲስ አበባ በምርጫው እንወዳደራለን፡፡ በሁሉም ላይ ቦታ ሰፊ አቀባበል ያገኘን ቢሆንም በተለይ ኦሮሚያ ላይ ኢህአዴግ ምርጫውን ካላጭበረበረ በቀር የሚያሸንፍበት መንገድ የለውም፡፡ እኛ ሁለት ነገር ነው የምንጠብቀው፡፡ አንደኛ ኢህአዴግ ካላጭበረበረ በቀር ኦሮሚያ ላይ አያሸንፈንም፣ ሁለተኛ ደግሞ ፖለቲካውን በሚገባ እንዳሸነፍን አሳይተናል፡፡ ሰፊ ድጋፍ እንዳለን አስመስክረናል፡፡ በየትኛውም ሚዛን ከኦህዴድ እንደምንሻል አሳይተናል፡፡ በዚህ ተደናግጠው እኔ በምወዳደርበት አካባቢ ኦህዴዶች ህዝቡን በሬ አርደው ማብላት ሁሉ ጀምረዋል፡፡ የክልሉ ካድሬዎች አሁን አምቦ ከትመዋል፡፡ ሥራ ላይ ናቸው ማለት ነው፡፡ ኦህዴድና ህዝቡ ከተለያየ ቆይቷል፡፡ ያው በኢህአዴግ ጃንጥላና ጠመንጃ ስር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ እነሱም እንደማያሸንፉ ያውቃሉ። እኛ በ97 እኮ አሳይተናቸዋል፡፡ በወቅቱ እነ አባዱላን ያሸነፉት እኮ የ6ኛ እና 7ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ኦህዴድ በኦሮሚያ ሊሸነፍ እንደሚችል በ97 ምርጫ ነው ያረጋገጥነው፡፡ ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡
“መድረክ” አብላጫ ድምፅ ካገኘ ጥምር መንግስት ይመሰርታል:: እኛ በፕሮግራማችን ላይ በግልፅ አስቀምጠናል። በሽግግሩ ጊዜ ጥምር መንግስት ያስፈልጋል ብለናል። ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድና ለመሳሰሉት ዲሞክራሲያዊ ሂደቶች መልክ ማስያዣ ይሆን ዘንድ የብሄራዊ አንድነት መንግስት ያስፈልጋል፡፡ ከማን ጋር ይመስረት የሚለው በድርድር የሚከናወን ይሆናል፤ ነገር ግን አግላይ ፖለቲካ ውስጥ አንገባም፡፡አንድ ፓርቲ ሌላውን አግልሎ ኢትዮጵያን መንግስተ ሰማያት ያደርሳል የሚሉ ካሉ ወይ የፖለቲካ ሳይንስ ያልገባቸው ወይም እስከቻልን ድረስ በፈላጭ ቆራጭነት ረግጠን እንግዛ የሚሉ ናቸው፡፡ በተረፈ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ለማምጣት መታለፍ ያለበት አንዱ ሂደት የብሄራዊ አንድነት መንግስት ማቋቋም ነው። ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡
በአጭሩ የኢትዮጵያ መንግስት ደጋግሞ እንዲያስብበት የምመክረው ምርጫውን እንዳያጭበረብር ነው፤ ውጤቱ የፈለገ ይሁን፡፡ ምርጫን አጭበርብሮ አሸንፌያለሁ የማለት ጊዜ ማብቃቱን ማወቅ አለበት። ያንን ካላደረገ ሃገሪቷንና ህዝቦቿን ለበለጠ ተስፋ መቁረጥ ነው የሚዳርገው፤ ይሄ በተግባር እየታየ ነው። ወጣቱ ከቀይ ባህር እስከ ሜዲትራኒያን ድረስ የባህር ሲሳይ የሚሆነውና በረሃ ውስጥ እንደዚያ የሚታረደው፣ ደቡብ አፍሪካ እንደዚያ የሚቃጠለው በሃገሩ ተስፋ ስላጣ ነው፡፡ ኢህአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ እንኳ “የስደት ዘመን ይብቃ” ብሎ ከፖሊስ ጋር እንዴት እንደተጋጨ ተመልክተናል፡፡ አጥፍቶ የመጥፋት ፖለቲካ ይብቃ! የኢህአዴግ ባለስልጣናት ደጋግመው ያስቡበት። ህዝቡንም ወጣቱንም ተስፋ ማስቆረጥ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ወጣቱ በሃገሬ የተሻለ ሥራ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ሊያድርበት ይገባል፡፡ ይሄንን ወጣት ተስፋ ማስቆረጥ ለሁላችንም አይበጅም፡፡ ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡

No comments: