Tuesday, March 17, 2015

ወያኔና ሽብርተኛነት

March 17,2015
ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም
terrorist-cat
ወያኔነትና ሽብርተኛነት ትናንት ምን ዓይነት ግንኙነት ነበራቸው? ዛሬ ምን ዓይነት ግንኙነት አላቸው?
ወደዚያ ከመሄዳችን በፊት የአሸባሪነት የተግባር መገለጫው ምንድን ነው? ብለን እንጠይቅ፤ አሸባሪነት፡-
• ያለውን የሥልጣን ሥርዓት የማፍረስ ዓላማ ያለው ነው፤
• ዓላማውን ለማሳካት ጉልበቱን የሚያፈረጥመው ከሥርዓቱ ጠላቶች በሚያገኘው፡–
• የመሣሪያ እርዳታ፣
• የእውቀት ድጋፍና ገንዘብ
• ዓላማውን ለማሳካት
o ሰዎችን ገድላል
o ያስራል፤ ያሰቃያል
o ይዘርፋል፤ ይቀማል፤
• ዓላማውን ለማሳካት
o ሃይማኖቶችንና ባህልን ያዳክማል፤
o የጥንት ታሪክ ማስታወሳዎችንና የቆዩ መጻሕፍትን ያጠፋሉ፤
o የፖሊቲካ እምነትን ያግዳል፤
o የመሰብሰብ ነጻነትን ይከለክላል፤
o የመደራጀት ነጻነትን ይከለክላል፤
o ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ይከለክላል፤
o ጉልበትን ወደሥልጣን ይለውጣል፤
• አንድ ዓላማ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ሀሳብ፣ አንድ ዘዴ አንድ መንገድ በቀር ሌላው ሁሉ ይዘጋል፤ ይህንን ጥርነፋ የሚቃወም ሁሉ አሸባሪ ተብሎ ይታሰራል፤ የሲአይኤ ሰላይ ተብሎ ተሰቃይቶ ይሞታል፤
ከዚህ በላይ የተዘረዘረት በሙሉ የሽብርተኞች ወንጀሎች የሚባሉ ናቸው፤ እነዚህን እንደመመዘኛ አድርገን በአንድ በኩል ወያኔን፣ ከተፈጠረ ጀምሮ እስካሁን የሚያድርገውንና እያደረገ ያለውን በማስታወስ፣ በሌላ በኩል ከዚህ በታች የተዘረዘሩትና በሽብርተኛነት ተከስሰው በእስር ቤት የሚገኙት ሰዎችን
• እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት ዓለሙ፣ ተመስገን ደሳለኝ
• የዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁት ወጣቶች፣ (ማኅሌት ፋንታዬ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ኤዶም ካሣዬ፣ አቤል ዋበላ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ተስፋ ዓለም ወልደየስ፣ ዘለዓለም )
• አንዱዓለም አራጌ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ
• ሌሎች ከግንቦት ሰባት ጋር ንክኪ አላችሁ ተብለው የታሰሩት
ስናመዛዝን በሽብርተኛነት መመዘኛዎቹ ከብደው የሚታዩት የትኞቹ ናቸው? የአሸባሪነት የተግባር መግለጫ ተብለው በተዘረዘሩት ውስጥ ባሉት ዓላማዎችና መንገዶች የሚንቀሳቀሱት የትኞቹ ናቸው? ወያኔ ነው ወይስ የታሰሩት ሰዎች? ሽብርተኛ ተብለው ከታሰሩት ውስጥ ባንክ ሲዘርፍ የተያዘ አለ? እኔ አስከማውቀው የለም፤ ከወያኔ ውስጥስ ባንክ የዘረፈ አለ? ራሱ መለስ ዜናዊ በኩራት ነግሮናል! በሌሎች ወንጀሎችም ቢሆን ያው ነው፡፡
ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነው የዓለም የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ሁሉ በወያኔ በሽብርተኛነት የታሰሩት ሁሉ እንዲፈቱ እየወተወቱ በአንጻሩ የወያኔን የሰብአዊ መብቶችን መጣስ እያወገዙ ነው፤ ስለዚህ ጋዜጠኞችንና የፖሊቲካ ሰዎችን እየለቀሙ በሽብርተኛነት እየወነጀሉ በየእስር ቤቱ መወርወሩ አላዋጣም፤ አዝማሚያው እንደሚያሳየው የወያኔ ጸረ-ሽብርተኛ መምሰል ለሲአይኤም የሚሸጥ ሊሆን የሚችል አይመስልም፡፡
በዚያ ላይ ሽብርተኞች በኢራቅና በአፍጋኒስታን አድርገው የመን ገብተዋል፤ ከየመን ሶማልያ ቅርብ ነው፤ ኬንያን እየፈተሹት ነው፤ የሱዳን ትርምስ ሽብርተኞችን እንደሚጋብዝ ጥርጥር የለም፤ የናይጂርያው ወደሱዳን ሲጠጋ መፈናፈኛ ይጠፋል፤ በሽብርተኛነት የተከሰሰችው ኤርትራ ለመሸሸጊያ ትሆን ይሆን?
ጤናማ ሰው ሆኖ ሽብርተኛነትን የሚደግፍ ያለ አይመስለኝም፤ ዛሬ በኢራቅ የሚደረገውን በየቀኑ ስንመለከት ወደቤታችን አልተጠጋም ብለን ልንዝናና የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፤ በዋልድባና በበዙ ሌሎች ቦታዎች የኢትዮጵያ ቅርሶች አደጋ ላይ መሆናቸው ይሰማናል፤ ግን በአቅመ-ቢስነት በዝምታ እንመለከታለን፤ ይህንን የአዳፍኔ የፖሊቲካ አቅጣጫ ለመለወጥ የሃሳብ መለዋወጫ መድረክ የሚፈጥሩትን ወጣቶች ሁሉ በእስር ቤቶች እያጎሩ ነው፤ አዲስ የፖሊቲካ መድረክ እንፍጠር ብለው በሰላማዊ መንገድ የፖሊቲካ ትግል የጀመሩትን ሁሉ እያሰሩ ነው፤ በትግራይ ውስጥ አረና በትግራይ ያለውን የፖሊቲካ መሻገት ለማጥራት እንዳይሞክር እየተደረገ ነው፤ ከዚህ በፊት ገብሩ ዓሥራት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረትን በክፉ የጭካኔ ዘዴ እንዳዳከመ አሁንም አረናን ለማዳከም እየተሞከረ ነው፡፡
መቼ ነው ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው ነገን የማየት ዓይኖች የሚያበቅሉት?
መጋቢት 1/2007

No comments: