March 22,2015
‹‹ቤተሰቦቻቸው ምግብና ልብስ ማስገባታቸውን ሰምተናል›› ሰማያዊ ፓርቲ
የሰማያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ የምክር ቤት አባል የነበረችው ወ/ሪት ኢየሩሳሌም ተስፋውና የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል አቶ ፍቅረ ማርያም አስማማው ትክክለኛ ቀኑ ባይታወቅም፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ድንበር አቋርጠው ኤርትራ በመግባት ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ ሲሉ መያዛቸው ተሰማ፡፡
የፓርቲው አባላት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የ28 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መሆኑ እየተነገረ ቢሆንም መቼ፣ እንዴትና በማን ተይዘው የትኛው ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ሪፖርተር ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
በቁጥጥር ሥር ውለዋል ስለተባሉት ሦስቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የፓርቲያቸውን አባላት መታሰር የሰሙ ቢሆንም በቂ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ የተጨበጠ ነገር ማግኘት እንደተሳናቸው የሚናገሩት አቶ ዮናታን፣ ቤተሰቦቻቸው ምግብና ልብስ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) እንደወሰዱላቸው መስማታቸውን ጠቁመው፣ በአካል ያግኟቸው አያግኟቸው ግን እንዳላወቁ አስረድተዋል፡፡
እሳቸው ግን መቼ እንደታሰሩና የት እንደታሰሩ አለማወቃቸውንና ከ15 ቀናት በፊት ሌላ የፓርቲው ተወዳዳሪ ዕጩ መታሰሩን አስታውሰው፣ ምናልባት በዚያን ጊዜ ታስረው ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሁዳዴን ፆም በጸሎት ለማሳለፍ እንደሄዱ የሚናገሩት አቶ ዮናታን፣ የትና መቼ እንደሄዱ ግን ግልጽ አላደረጉም፡፡ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የተባሉት አባላት ቀደም ባሉት ጊዜያት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉና በፓርቲው ውስጥ ኃላፊነት የነበራቸው ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ከኃላፊነት ተነስተው አባል ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አቶ ፍቅረ ማርያም ግን እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሥራ ላይ እንደነበሩ አቶ ዮናታን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ብዙ ሰዎች በየድረ ገጹ ብዙ ነገር ይጽፋሉ፡፡ ትክክለኛውን ነገር ግን ማግኘት አቅቶናል፤›› የሚሉት አቶ ዮናታን፣ ማዕከላዊ ምርመራ ሄደውም ሆነ ሰው ልከው ምንም ያገኙት ምላሽ ባለመኖሩ፣ እስከሚጣራ ድረስ አስተያየት መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
ጊዜው የምርጫ ወቅት በመሆኑ በጣም ሥራ እንደሚበዛባቸው ገልጸው፣ አሁን መናገር ባይችሉም ወደፊት ሁኔታውን ተከታትለው ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳ ሦስቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በጎንደር በኩል አድርገው ወደ ኤርትራ ለመሻገር ሲንቀሳቀሱ ድንበር አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች መያዛቸውን ፓርቲው ቢያውቀውም፣ የተፈጠረውን ጉዳይ ለምን ይፋ አያደርግም ተብሎ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ወቀሳ እየቀረበበት ነው፡፡ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉትን የአባላቱን ጉዳይ በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ አለመስጠታቸው ያበሳጫቸው የተለያዩ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ እስካለፈው ዓርብ ሌሊት ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኙም፡፡
ኤርትራ በመግባት ግንቦት ሰባት የተባለውን ድርጅት ለመቀላቀል ድንበር አካባቢ ተይዘዋል ስለተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በመንግሥት በኩልም እስከ ዓርብ ሌሊት ድረስ ምንም የወጣ መረጃ አልነበረም፡፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ የመንግሥት ተቋማትም መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ግንቦት ሰባት የተባለው ድርጅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ጋር በአሸባሪነት መሰየሙ አይዘነጋም፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment