Sunday, March 15, 2015

እንግሊዝ በኢትዮጵያ ያለው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አፈጻጸም ያሰጋኛል አለች!!!

March 15,2015
የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ላልተገባ ዓላማ እየዋለ ነው በሚል ተችታለች

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው የ2014 (እ.ኤ.አ.) የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ሪፖርት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ኢትዮጵያ በምትፈጽማቸው ገደቦች ሥጋት እንደገባው አስታወቀ፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ላልተገባ ዓላማ እየዋለ ነው በሚልም ተችቷል፡፡

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችና ሌሎች አካላት ሕጉ ተጠቅሶ የተከሰሱት የመሰብሰብና ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ለመጠቀም ሙከራ ሲያደርጉ እንደሆነ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
በዓመቱ የዞን ዘጠኝ አባላት የሆኑ ሰባት ጦማሪያንና አቶ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ 17 ጋዜጠኞች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉም ሲፒጄን በመጥቀስ ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ይህም ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያ ከዓለም በአራተኝነት ደረጃ እንደሚያስቀምጣት አመልክቷል፡፡ 30 ጋዜጠኞች በዓመቱ ከአገር እንደተሰደዱ የገለጸው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የመክሰስ ሐሳብ ስለሌለው ሊመለሱ ይችላሉ ማለቱንም ጠቅሷል፡፡

እንግሊዝ ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት 20 ጋዜጠኞች የተባረሩት በክልሉ የተከሰተውን የተማሪዎች አመፅ በዘገቡበት ተቺ አቀራረብ የተነሳ እንደሆነም እንደሚታመን ጠቅሷል፡፡ የአምስት መጽሔቶችንና የአንድ ጋዜጣ ኅትመት የተቋረጡትም በመንግሥት ውሳኔ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ በአገሪቱ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ተደራሽነት የተገደበ እንደሆነም ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ የግል አሳታሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በአስተማማኝ ሁኔታ የማተሚያ ቤት አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውም እንደ ሳንካ እንደሚቆጠር ገልጿል፡፡ ለጋዜጠኞች የሙያ ሥልጠና በመስጠትም ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠበቅበትን እየሠራ እንዳልሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ሪፖርቱ የእንግሊዝ መንግሥት በሚዲያ ነፃነት ላይ መንግሥት የሚፈጽማቸውን ገደቦች በሚመለከት ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩንም ያስታውሳል፡፡ በተለይም በመስከረም 2007 ዓ.ም. በተመድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል በዓለም አቀፍ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ (UPR) ላይ፣ ኢትዮጵያ ምርጫ 2007 ከምርጫ 2002 በተቃራኒ ወካይና አሳታፊ እንዲሆን ተጨባጭ ዕርምጃ እንድትወስድ የእንግሊዝ መንግሥት ምክረ ሐሳብ ሲሰጥ ተቀብላው የነበረ ቢሆንም፣ ዕርምጃዎቹ እስኪወሰዱ እንግሊዝ አሁንም እየጠበቀች እንደሆነ ገልጿል፡፡

እንግሊዝ በፕሬስ ነፃነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ብላ ያመነችባቸውን ጉዳዮች በፍርድ ቤት መከታተሏንና ይህም ዓለም አቀፍ ደረጃ መሟላቱን ለመገምገም እንደረዳ ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት በግንቦትና በሐምሌ ወራት የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳሩና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጫው መጠቆሙን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ኅብረቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የፍርድ ሒደት ሰብዓዊ መብታቸውን ባከበረ መንገድ እንዲካሄድ መጠየቁን አመልክቷል፡፡

የእንግሊዝ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን ማክበር የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ እንደሚያጠናክርና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በአገሪቱ ዘላቂ መረጋጋትን ለማስፈን እንደሚያግዝ እምነት እንዳለው ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን አስተያየት የተጠየቁት የመንግሥት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን ከሽብርተኝነት ለመጠበቅ የምታደርገው ዕርምጃ አግባብ አይደለም የሚሉ አካላት ለተመሳሳይ ሥጋት ተመሳሳይ ዕርምጃ ሲወስዱ፣ የእነሱ ድርጊት ተገቢ የመንግሥት ሥራ የሚሆንበት አመክንዮ አይገባኝም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና መንግሥት ሪፖርቱን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ ምላሽ  እንደሚሰጥበት ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment