Thursday, January 15, 2015

ሬዲዩ ፋና፣ ‹‹አንድነት ከአሸባሪ ቡድኖች ገንዘብ ይቀበላል›› በማለት ወነጀለ

January15,2015

ፍኖተ ነፃነት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሬድዩ ፋና እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ/ኢቲቪ) በአንድነት ፓርቲ ላይ የጠነሰሱት ሴራ ተጋለጠ፡፡
አንድነት፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ካልሆኑ ሰዎች ገንዘብ ያሰባስባል›› የሚል ውንጀላ እየቀረበበት እንደሚገኝ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ለፍኖተ-ነፃነት ገልፀዋል፡፡ በተለይ ራዲዮ ፋና ‹‹አንድነት ከግንቦት ሰባት ገንዘብ ይቀበላል፣ በውጪ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ካልሆኑ ሰዎች ገንዘብ ይሰበስባል›› የሚል ውንጀላ እያቀረበ መሆኑን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አያይዘው ገልፀዋል፡፡
አንድነት እየቀረበበት የሚገኘው ውንጀላ መሰረተ-ቢስ መሆኑን የገለፁት አመራሮቹ፣ ፓርቲው አሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ገንዘብ እንደሚያሰባስብ እና ለዚህም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሆኑ የአንድነት ደጋፊዎች፣ በፓርቲው እውቅና ተሰጥቷቸው የድጋፍ ሰጪ ቻፕተር ማቋቋማቸውን ገልፀዋል፡፡ ‹‹አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት ብቻ ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ ከሆኑ ሰዎች ብቻ ገንዘብ እንደሚያሰባስቡ›› የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ አስታውቀዋል፡፡ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በበኩላቸው የፓርቲው የፋይናንስ አሰራር ግልፅነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ገልፀው፣ በየዓመቱም ኦዲት እንደሚደረግና ምርጫ ቦርድም ለተከታታይ ዓመታት የፓርቲውን የፋይናንስ አሰራር ግልፅነት የሚታይበት እንደሆነ ጠቅሶ ለፓርቲው ሰርተፍኬት መስጠቱን› አቶ ግርማ አውስተዋል፡፡ የራዲዮ ፋና ውንጀላም ከዚህ አንፃር ተገቢነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ ይህን መሰሉን ውንጀላ የአንድነት አባል ነን የሚሉ ሰዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሬዲዮ ፋና ላይ ቀርበው ያሰሙ ሲሆን የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛ ነኝ የሚል ብሩክ ከበደ፣ የተባለ ግለሰብም ይህን መሰሉን ውንጀላ እንዳቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ም/ፕሬዘደንት አቶ ግርማ ሰይፉ እና የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ ስዩም መንገሻ በሬዲዮ ፋና “ሞጋች” በተባለ ፕሮግራም ላይ ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም በቀረቡበት ወቅት የገዢው ቡድን ተጠሪ የሆነው ብሩክ ከበደ ፣ “አንድነት ፓርቲ በሽብር ከተፈረጁ ቡድኖች ገንዘብ ይሰበስባል” የሚል ውንጀላ ሲያቀርብ እንደነበር የፓርቲው አመራሮች ለፍኖተ-ነፃነት አስረድተዋል፡፡
ገዢው ፓርቲ አሰርጎ ባስገባቸው ሰዎች “የደንብ ጥሰት አለ” የሚል ውንጀላ ሲቀርብበት የነበረው አንድነት ዛሬ ላይ ደግሞ ውንጀላው በህዝብ ስም በተቋቋሙት ሚዲያዎች አማካኝነት “በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ገንዘብ ይቀበላል” በሚል ሌላ ውንጀላ እየቀረበበት ይገኛል፡፡
በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ገዢው ቡድን “አንድነት ፓርቲ ከግንቦት ሰባት 1 ሚሊዮን ብር ተቀብሏል፡፡” የሚል ክስ በተላላኪዎቹ በኩል ሊያቀርብ መዘጋጀቱን የሚያጋልጥ መረጃ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡

No comments: