January 23,2015
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የፓርቲያቸው ምክትል ፕሬዝደንት እና የሰሜን ቀጠና ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘመነ ምህረት እጅግ ዘግናኝ ድብደባ ደርሶባቸው ሲል ፓርቲው ጥር 15/2007 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡ አቶ ዘመነ የመኢአድን ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ወደ መኖሪያቸው ጎንደር ከተማ ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ የደህንነት ክትትልና ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ለፓርቲያቸው አሳውቀው ነበር ያለው ፓርቲው በ10/05/2007 ዓ.ም ጎንደር ከሚገኘው መኖሪያው ቤታቸው ከባቤታቸውና ከህጻን ልጃቸው ፊት የፖሊስ ልብስ በለበሱ አካላት ከፍተኛ ደብደባ ተፈጽሞባቸው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ግልጾአል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓርቲው አባላት ባደረጉት ክትትል አቶ ዘመነ አዘዞ የሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ውስጥ እንደሚኙ አረጋግጠናል ያለው መግለጫው የሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ከፍተኛ ስቃይና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
ከአቶ ዘመነ በተጨማሪ ጠቅላላ ጉባኤውን ተሳትፈው የተመለሱት የፓርቲው የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ እያሱ ሁሴን 3 አመት ተፈርዶባቸው እስር ቤት እንደሚገኙ፣ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ መ/አ ጌታቸው መኮንን፣ አቶ ጥላሁን አድማሴ የተባሉትን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው መግለጫው በአመራርና አባላቶቻቸው ላይ የሚደረገው እስር መኢአድ ምርጫውን ተጠቅሞ በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና ማሳደር ስለሚችል እንደሆነ ተገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል በአባላቶቻቸው ላይ በሚደርሰው በደልና ጫና ባሻገር ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ከምርጫ 2007 እንዳይሳተፍ የኢህአዴግ ቀኝ እጅ ሆኖ በመስራት ላይ እንዳለ ያወሳው መግለጫው ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከተደረገ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በፓርቲው ላይ የሚፈጽመውን በደል ተከትሎ ፓርቲው በሚደርገው ትግልም ህዝቡ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
No comments:
Post a Comment