Monday, January 5, 2015

አቃቤ ህግ በጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ላይ የቀረበውን ክስ እንዲያሻሽል በድጋሜ ታዘዘ

January5,2015
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ዛሬ ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ለ14ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የቀረበውን የክስ ማሻሻያ በተመለከተ ብይን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተሰየመው ቀደም ብሎ በጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲሻሻል ባዘዘው መሰረት የፌደራል አቃቤ ህግ ክሱን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አሻሽሏል ወይስ አላሻሻለም በሚለው ጉዳይ ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች ተሻሻለ የተባለው ክስ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት አለመሻሻሉን ያቀረቡትን አቤቱታ እና አቃቤ ህግ ይህንኑ አቤቱታ በተመለከተ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ የሰጠውን ብይን በንባብ አሰምቷል፡፡
በመሆኑም አቃቤ ህግ ተከሳሾች በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ከተመለከቱት የሽብር ተግባራት የትኞቹን ፈጸሙ የሚለው በክሱ ላይ አልተጠቀሰም በተባለው ጉዳይ ላይ ያቀረበውን ማሻሻያ እና ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹ የ‹ሽብር› ድርጊት ግብና ስትራቴጂን አስመልክቶ በግልጽ ተብራርቶ ክሱ እንዲሻሻል ተሰጥቶት የነበረውን ትዕዛዝ በተመለከተ በማሻሻያው ላይ የቀረበው በቂ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ እነዚህን ፍሬ ነገሮች እንደተሻሻሉ አድርጎ ተቀብሎታል፡፡
በቀሪዎቹ ነጥቦች ላይ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ማሻሻያውን አለማድረጉን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ አመልክቷል፡፡ በተለይም ይሻሻሉ ተብለው ትዕዛዝ በተሰጠባቸው አራት ነጥቦች ላይ፣ ማለትም በተከሳሾች ተመሰረተ የተባለውን ድርጅት (ቡድን) ከተቻለ በስም በመግለጽ ወይም ከሌሎች ድርጅቶች (ቡድኖች) ለይቶ እንዲገልጽ፣ የእያንዳንዱን ተከሳሽ የውስጥ የስራ ክፍፍል ለይቶ እንዲያመለክት፣ ተከሳሾች በተከሰሱበት ጉዳይ ወሰዱ ተብሎ በክሱ የተጠቀሰው ስልጠና በማን፣ የትና መቼ እንደተሰጠ ተለይቶና ተገልጾ ክሱ እንዲሻሻል፣ እንዲሁም ለአመጽ ተግባር እንዲውል ውጭ ሀገር ከሚገኙ ገንዘብ (48 000 ብር) ተላከ የተባለውን ገንዘብ በተመለከተ፣ ገንዘቡ ከማን እንደተላከና ለምን ዓላማ እንደዋለ ተገልጾ ክሱ እንዲሻሻል የሚሉት ፍሬ ነገሮች በትዕዛዙ መሰረት አለመሻሻላቸውን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ እንዲሻሻሉ ትዕዛዝ ከሰጠባቸው ነጥቦች መካከል አብዛኞቹ በአቃቤ ህግ አለማሻሻላቸውን በብይኑ ላይ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም አቃቤ ህግ ያልተሻሻሉ ነጥቦችን አሻሽሎ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ለጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment