Saturday, January 17, 2015

ሰማያዊ ቀለም በኢህአዴግ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል

January 17,2015
• ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ለቀለም አብዮት ከቻይና 20 ሺህ ቲሸርቶችን አስገብቷል›› ምክትል ሳጅን መላኩ
• ‹‹አብዮት እየጠራ ያለው ኢህአዴግ ነው›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
በትናንትናው ዕለት ፖሊስ የጥምቀትን በዓል ለማስተባበር በቀጨኔ መድሃኒያለም የተሰበሰቡ የበዓሉ አስተባባሪዎችን ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ለቀለም አብዮት ከቻይና 20 ሺህ ቲሸርቶችን ስላስገባ ሰማያዊ ቲሸርት እንዳትለብሱ›› ሲል ማስጠንቀቁን ተወካዮቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ሰማያዊ ቲሸርት እንዳይለበስ ያስጠነቀቁት የቀጨኔ ማዘዣ የወረዳ 4 ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ሳጅን መላኩ የጥምቀት በዓልን ለማስተባበር በቀጨኔ መድሃኒያለም የተሰበሰቡትን 150 ያህል ወጣቶች ‹‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ለቀለም አብዮት ከቻይና 20 ሺህ ቲሸርቶችን አስገብቷል፣ ቲሸርቶቹ አዲሱ ገበያ አካባቢ እንደሚገኙ መረጃ አግኝተናል፡፡ ማንም ሰው ሰማያዊ ቲሸርት እንዳይለብስ፡፡ ትዕዛዙ ከበላይ አካል የመጣ ነው›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ተወካዮቹ ለጥምቀት ያዘጋጁዋቸው ቲሸርቶች ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸውና ከመልበስም እንደማይቆጠቡ በመግለጻቸው ጉዳዩ ባለመግባባት ተቋጭቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መላከ ሰላም ቆሞስ አባ ፍቅረማሪያም ፖሊሶቹንና የበዓሉን አስተባባሪዎች ለማስታረቅ ጥረት ቢያደርጉም ፖሊሶቹ ‹‹ከበላይ አካል የመጣ ትዕዛዝ በመሆኑ እኛ የምንወስነው ነገር የለም፡፡›› በማለታቸው ባለመግባባት ተጠናቅቋል፡፡ ከቲሸርት በተጨማሪ ሰማያዊ ዣንጥላም እንዳይያዝ ፖሊሶቹ መከልከላቸውን የበዓሉ አስተባባሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ስለ ሁኔታው ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ‹‹ኢህአዴግ ህዝቡን ስለማያምነው የማያስደነግጠው ነገር የለም፡፡ በደነገጠ ቁጥር ህዝብን የሚከለክለው ለዚህ ነው፡፡ አብዮት እየጠራ ያለው ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ ምን ያህል ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ በሩ ዝግ እንደሆነ፣ ይህንም ሰብሮ ለመውጣት የተዘጋጀ ኃይል እንዳለ፣ ከዛ ውስጥ ሰማያዊ አንዱ መሆኑን ያውቀዋል፡፡›› ሲሉ የኢህአዴግን የስጋት ምንጭ ከምን እንደመነጨ ገልጸውልናል፡፡ ኢህአዴግ ህዝቡን በሆነ ባልሆነው ለማሸማቀቅና ለመከልከል ቢሞክርም ለውጡ እንደማይቀር፣ ፓርቲያቸው ይህንን ለውጥ ለመምራት የተዘጋጀ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ከሰጋም ‹‹አዲሱ ገበያን እንዳያቃጥለው እሰጋለሁ›› ብለዋል አቶ ዮናታን፡፡
በሌላ ዜና የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ንግድና ኢንዱስትሪ ሰራተኞች ሰማያዊ ቲሸርት (የደንብ ልብስ) ተሰርቶ መጥቶላቸው የነበር ቢሆንም በቀለሙ ምክንያት እንዳይለበስ በመከልከሉ ቢጫ ቀለም ያለው ሌላ ቲሸርት እንደተሰራላቸው ሰራተኞቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹የመለስ ፋውንዴሽን›› ካሰራቸው ቲሸርቶች መካከል ሰማያዊ ቀለም ያላቸው እንዳይለበሱ መከልከሉን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment