December 4,2014
ቤተሰቦቿ ሐኪሞችንና ፖሊሶችን ወቀሱ
* “አሸባሪዎችን” ለይቶ የመያዝ “ልዩ ችሎታና ብቃት” ያለው ፖሊስ ያልያዘው ተጠርጣሪ አለ
ሃና ላላንጎ የተባለችውን ተማሪ በሚኒባስ ታክሲ አፍነው በመውሰድ፣ በቡድን በመድፈርና ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙትን አምስት ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ጉዳይ በዝግ ችሎት መታየት ጀመረ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለሦስተኛ ጊዜ ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣ ፖሊስ ቀደም ባለው ቀጠሮ እንደሚሠራቸው ያስመዘገበውን ቀሪ የምርመራ ሒደት፣ ለችሎቱ ያስረዳበትና ተጠርጣሪዎቹን ያቀረበበት ሰዓት፣ ከሌሎች ቀናት የተለየ ነበር፡፡
ሟች ሃና ላላንጎ በቡድን ተደፍራ ሕይወቷ ማለፉ በመገናኛ ብዙኃን ከተሰራጨበት ጊዜ አንስቶ እያነጋገረ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በየቀጠሮው ፍርድ ቤት የሚገኘው ታዳሚ ቁጥር ጨምሯል፡፡ ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደተለመደው ፖሊስ ዘግየት ብሎ ከ4፡30 ሰዓት በኋላ እንደሚመጣ በማሰብ፣ ሕዝቡ ወደ ፍርድ ቤት መድረስ የጀመረው በአብዛኛው ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ጀምሮ ነበር፡፡
የጠዋቱ ጊዜ ወደ እኩለ ቀን እየተቃረበ በመሄዱ፣ ሕዝቡ እርስ በራሱ “አራዳ አቅርበዋቸዋል አሉ፤ አይ አይደለም ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ መሥርተዋልና ፖሊስ እንጂ ተጠርጣሪዎቹ አይቀርቡም፤” የሚሉና ሌሎች መላምቶችን በመነጋገር ላይ እያለ፣ ፖሊስ ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ላይ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ቀርቦ፣ ማንም ወደ ችሎት ሳይገባ በዝግ ችሎት፣ የሠራውን የምርመራ ሒደት ለፍርድ ቤቱ ካስረዳ በኋላ፣ ለሚቀረው ተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናትን ጠይቆ እንደተፈቀደለት ተሰማ፡፡ ለታኅሣሥ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. መቀጠሩም ታወቀ፡፡
የተነገረውን ለማረጋገጥና ተጨማሪ መረጃ ለመስማት ቀጠሮውን ወደሰጡት ዳኛ የሟች ዘመዶችና የመገናኛ ብዙኃን በመሄድ ሲጠይቁ፣ ጠዋት በሥራ ሰዓት ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ በመቅረብ፣ ችሎቱ በዝግ እንዲታይለት ባመለከተው መሠረት ፍርድ ቤቱም ስላመነበት በዝግ ችሎት መታየቱ ተረጋገጠ፡፡
በሕገ መንግሥቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች አሠራር በዝግ መታየት ያለባቸው የወንጀል ድርጊቶች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ፣ ተማሪ ሃና ላላንጎን ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ፣ ለሁለት ጊዜያት በግልጽ ችሎት ከታየ በኋላ፣ በየትኛው የሕግ መሠረት ሦስተኛው ቀጠሮ በዝግ ሊታይ እንደቻለ ማብራሪያ እንዲሰጡ ዳኛው ተጠይቀው ነበር፡፡
የሃና ጉዳይ በዝግ ችሎት እንዲታይ የተወሰነው፣ ፖሊስ ምርመራውን ሳይጨርስ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና ድረ ገጾች፣ የሆነውንና ያልሆነውን ዘገባ በማሰራጨት ለምርመራው እንቅፋት እየፈጠሩበት መሆኑን አስረድቶ፣ ምርመራውን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ በዝግ ችሎት እንዲታይለት መጠየቁ አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ በዝግ ችሎት እንዲታይ መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎቹን በችሎት አቅርቦ ቀደም ባለው ችሎት ያስመዘገበውን ቀሪ የምርመራ ሒደት ምን ያህሉን እንደሠራና ምን ያህሉ እንደቀረው ማወቅ ባይቻልም፣ ቀደም ባለው ቀጠሮ ተጨማሪ 14 ቀናትን ጠይቆ፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹10 ቀናት ይበቃሃል›› በማለት ከጠየቀው ቀናት ላይ አራት ቀናትን የቀነሰ ከመሆኑ አንፃር፣ ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. የጠየቀውን 14 ቀናት ሙሉውን መፍቀዱ፣ ሌላ ተጨማሪ ተጠርጣሪ የመያዝና በርካታ ቀሪ ምርመራ ሳይኖረው እንዳልቀረ ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡
የሟች ተማሪ ሃና ወላጅ አባት አቶ ላላንጎ አይሶ ኅዳር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በየሳምንቱ እሑድ ምሽት ላይ በኢቢኤስ በሚቀርበው “ሰይፉ ፋንታሁን ሾው” ላይ ቀርበው ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪን መያዝ እንደሚቀረው በመናገራቸው፣ ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉዳዩ በዝግ መታየቱንና 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን ተከትሎ ጥርጣሬውን አጠናክሮታል፡፡
አቶ ላላንጎ ሟች ልጃቸው መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ታፍና መወሰዷንና ለ20 ቀናት አስታመዋት፣ በደረሰባት ከባድ ጉዳት ልትተርፍ አለመቻሏን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ላላንጎ ገለጻ፣ ልጃቸው ጦር ኃይሎች ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተጥላ ከተገኘች በኋላ፣ ወዲያውኑ ወደ አለርት ሆስፒታል ወስደዋታል፡፡ የአለርት ሆስፒታል ዶክተሮች ተመልክተዋት በስለት በመወጋቷና በደረሰባት የመደፈር አደጋ ሕይወቷን ልታጣ እንደምትችል በመናገር፣ ሕይወቷ ከማለፉ በፊት ቃሏን ለፖሊስ እንድትሰጥ በመናገራቸው ቃሏን እንድትሰጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የሃና ላላንጎ ወላጅ አባት ስለልጃቸው ስቃይ እንዳብራሩት፣ አለርት ሆስፒታል ከአቅሙ በላይ መሆኑን ገልጾ ወደ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሪፈር ተብለው ሲወስዷት፣ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ደግሞ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሪፈር እንዲወስዷት እንደነገራቸው አስረድተዋል፡፡ ያለምንም ሕክምና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ መልሶ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲልካቸው ተስፋ የቆረጡት አቶ ላላንጎ፣ ልጃቸውን በቀጥታ ወደ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል መውሰዳቸውን ትተው፣ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ አንድ ቀን አድራና ቤተሰቦቿን ተሰናብታ፣ በማግስቱ ወደ ጋንዲ ሆስፒታል እንደወሰዷት ገልጸዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ጋንዲ ሆስፒታል በሪፈር የሄደችው ሟች ሃና፣ ይኸ ሁሉ ውጣ ውረድ ሲደረግ ደም እየፈሰሳትና ቁስሏም ወደ ሌላ ሕመም እየተቀየረ መሆኑን የገለጹት አባቷ፣ ሙሉቀን በጋንዲ ሆስፒታል ከቆየች በኋላ፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል አልጋ ተገኝቶላት መተኛት መቻሏን ተናግረዋል፡፡
የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሐኪሞች የሃናን ጉዳትና ሕመም ሲመለከቱ፣ በከፍተኛ ሐዘንና እንባ ታጅበው ለማትረፍ የተረባረቡ ቢሆንም፣ ችግሩ ወደ ሌላ ነገር ተቀይሮ የነበረ በመሆኑ ሕይወቷ ሊተርፍ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
አቶ ላላንጎ የልጃቸውን ስቃይ በሐዘን ሲገልጹ፣ ሐኪሞችንና ፖሊሶችን ወቅሰዋል፡፡ “ሁሉንም ሐኪምና ሁሉንም ፖሊስ በጅምላ መውቀስ አልፈልግም፤” ብለው፣ መልካምና ሥራቸውን የሚወዱ፣ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ሐኪሞችና ፖሊሶች ስላሉ እነሱን ማመስገን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ልጃቸው ደም እየፈሰሳት በሄዱበት ሆስፒታሎች “አልጋ የለም፣ ውጭ አስመርምሯት” ማለትና ችላ ማለት ተገቢና የገቡለትም ቃል ኪዳን ባለመሆኑ፣ ተገቢ አለመሆኑን በመናገር፣ መንግሥትም ሊከታተለው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ፖሊሶችም ቢሆኑ፣ ጉዳዩን በትጋት ተከታትለውና ራሳቸው የሚሆነውን እንደማድረግ “እዚያ ውሰድ እኛ ጋ አይደለም” በማለት እንዲንገላቱ ማድረጋቸው ተገቢ ባለመሆኑ መንግሥትም ሊያየው የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ (ምንጭ ሪፖርተር)
No comments:
Post a Comment