Sunday, December 7, 2014

ከትብብሩ የተሰጠ መግለጫ – በአገዛዙ አረመኔያዊ እርምጃ ትግላችን አይቆምም!

December 7, 2014

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ባለፈው አንድ ወር ‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› በሚል መርሃ ግብር ቀርጸን ስንቀሳቀስ ዋናው አላማችን የስርዓቱን አረመኔያዊነት ለህዝብ በማጋለጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው፡፡ እንደጠበቅነው ገና ከጅምሩ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ትግላችንን በጭካኔ ለማስቆም ጥሯል፡፡ ህዳር 7/2007 ዓ.ም የመጀመሪውን የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በጠራንበት ወቅት ስብሰባውን በኃይል በትኗል፡፡

ትብብራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ ያሰጋው ህወሓት/ኢህአዴግ በተለይ የህዳር 27/28 2007 ዓ.ም የአደባባይ አዳር ሰልፍን እንዳይካሄድ የትብብሩን አመራሮችና አባላቶቻችን በማዋከብ፣ በመደብደብና በማሰር ተጠምዶ ሰንብቷል፡፡ በተለይ በትናንትናው ዕለት ሰልፍ በወጣንበት ወቅት ስርዓቱ አመራሮችንን፣ አባላቶቻችንን፣ ተሳታፊዎችንን እንዲሁም አልፎ ተርፎ መንገደኛውን ህዝብ በጭካኔ ደብድቧል፡፡ አፍሶ አስሯል፡፡ ሙስሊም እህትና ወንድሞቻችን በየጎዳናው ታፍሰው የአገዛዙ አረመኔያዊ እርምጃ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ በርካቶችም በ እስር ቤቶቹ ታጉረዋል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ከ300 በላይ የትብብሩ አመራሮችና አባላት የታሰሩ ሲሆን የትብብሩና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርን ጨምሮ በርካታ አመራሮች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ድርሶባቸዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆነው አቤል ኤፍሬም ራሱን እስኪስት ተደብድቧል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ የተገኙ ሴት አመራርና አባላት አንድ አገርን እየመራሁ ነው ከሚል አካል በማይጠበቅ መንገድ በጭካኔ ተደብድዋል፡፡ እነዚህ በጭካኔ የተደበደቡ አመራሮች፣ አባላትና የሰልፉ ተሳታፊዎች ህክምና እንዳያገኙ ተከልክለዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በጥበቃ ሰራተኝነት የሚሰሩ የ72 አመቱ አቶ ቀኖ አባጆቢር ከስራ ሲወጡ በደህንነት ኃይሎች ታፍነው የተወሰዱና እስካሁን የት እንደደረሱ ያልታወቀ ሲሆን ይህም አገዛዙ የመጨረሻው የአረመኔነት ደረጃ ላይ እንደደረሰና ይህን የስርዓቱ ውንብድና ለማስቆም ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑን በግልጽ የተገነዘብንበት ነው፡፡

አገዛዙ በትናንትናው ዕለት በፍጹም ሰላማዊ ሰዎች ላይ የወሰደው የውንብድና እና አረመኔያዊ እርምጃ በትግሉ ውስጥ የምንጠብቀውና ስርዓቱ ለኢትዮጵያ የማይበጅ መሆኑን ዳግመኛ ያያ ረጋገጠበት ነው፡፡ የትናንትናው ትላችን አገዛዙ ለይስሙላ እከተለዋለሁ ከሚለው ‹‹ህጋዊ ሰርዓት›› ይልቅ ስልጣኑን በኃይል ለማስጠበቅ ቆርጦ መነሳቱን እና በህገ መንግስት ስም ህዝብን የሚበድልበትን የአረመኔያዊነት ጭንብል ገልጠን ለዓለም ያሳየንበት የትግላችን ውጤት ነው፡፡

አገዛዙ ላላፉት 24 አመታት ስልጣኑን በኃይል ለማስጠበቅ ሲጥር ቆይቷል፡፡ በትናንትናው ዕለት የፈጸመው ፍጹም አረመኔያዊ እርምጃም እንደተለመደው ሰላማዊ ታጋዮችን ያሸማቅቃል ብሎ አስቦ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የአገዛዙ አረመኔያዊነት ከሰላማዊነታችን ፍጹም ወደኋላ ሊያንሸራትተን አይችልም፡፡ ወደ ትግል ስንገባ የስርዓቱን ጭካኔና ለኢትዮጵያ የ ማይመጥን መሆኑን አውቀንና የሚያስከፍለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተንም ነው፡፡ አሁንም አገዛዙ የህዝብን ድምጽ በማፈን ስልጣኑን ለማስጠበቅ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን መጀመሪያውንም ትግሉን ስንቀላቀል አስበን የገባነው እየቆሰልን፣ እየታሰርንም፣ እየሞትንም ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለመሆን ነውና ከትግላችን ቅንጣት ሊያደናቅፈን አይችልም፡፡ ስለሆነም ወደፊትም ይህን የአገዛዙን አረመኔያዊነት በማጋለጥና ህዝቡን በትግሉ በማሳተፍ ለኢትዮጵያ የሚገባት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመመስረት በቀጣይነትም ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡

በዚህ አጋጣሚ ሰላማዊ ሰልፉን ለማሳካት እንዲሁም የህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን የፈጸመውን ጭካኔ በማውገዝ ከጎናችን ለቆማችሁ ሁሉ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ ከህወሓት/ ኢህአዴግ አገዛዝ ጋር የሚደረገው ትግል እልህ አስጨራሽ፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚያስከፍልና የእያንንዳንዳችን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም በጋራ እንድንቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን

ያለ መስዋዕትነት ድል የለም፡፡

No comments:

Post a Comment