Friday, November 21, 2014

ምርጫ ሲባል አማራጭ ሳያሳጡ መሆን ይኖርበታል!!!

November 21,2014
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

un3በሀገራችን ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚደረግ በመንግስት በኩል በከፍተኛ ደረጃ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተከናወኑት አራት ምርጫዎች ያየን እንደሆነ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ወደፊት ሊወስዱ እንዳልቻሉ እሙን ነው፡፡ ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ በተቃራኒው መንግስትና ገዢው ፓርቲ በፍፁም መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ተቀናጅተው ለአንድ ለአውራ ፓርቲ ግንባታ እየሰሩ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ተግባር ምርጫን ያለ አማራጭ እንዲሆነ እያደረገው እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡
በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዘመቻ በሚባል ደረጃ እየተካሄደ ያለው አፈናና እስር፤ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ክልከላውና ወከባው ተጠናከሮ መቀጠሉ፤ ገዥው ቡድን የምር ተቃዋሚ ፓርቲ ናቸው ብሎ የሚያስባቸው ፓርቲዎች ለማዳከምና ከምርጫው ውድድር ውጪ ለማድረግ ያለው ቁርጥ አቋም የሚያሳይ ነው። ይህ የገዢው ቡድን አካሄድ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመሰረት ፍላጎት እንደሌለው በደንብ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዲመርጥ እድል ሊጠሰው ሲገባ በሥርዓቱ በእኩል ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳያካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉበት የሚካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ትርጉም አልባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ የገዢው ቡድን ሀላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ በተግባር የሚደግፈው ከሠላማዊ ትግል ይልቅ የኃይልና የአመፅ መንገድ እንደሚሆን የተረዳ አይመስልም፤ ይልቁንም በሠላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፓርቲዎች ወደ አላስፈላጊ መስመር በመግፋት ሀገራችን ወደ ብጥብጥና ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንድትገባ የሚያደርግ ሁኔታ እየተከተለ ነው የሚገኘው። በሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በትክክል እንዳያዩ ጭፍን የሥልጣን ጥም ጋርዷቸዋል፡፡
በቀጣይ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚደረገው ምርጫም በመንግስት በኩል የመድበለ ፓርቲን ስርዓት ለማጎልበት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከአሁኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመደርደር ላይ ነው። የአንድነት አመራሮችና አባላት በግፍ በማሰር ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከፍተኛ የሆነ ጫና እየተደረገ ቢሆንም አንድነት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ህዝቡ እንዲሳተፍ በመቀስቀስና በማበረታታት የተዘጋውን የዴሞክራሲ በር በምርጫ ካርዱ ሊያስከፍት እንደሚችል ከፍተኛ እምነት አለው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደከዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን ብቻ በመራጭነት አስመዝግቦ ምርጫ የሚያደርግበት ሁኔታ ማብቃት ይኖርበታል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን በእኛ በኩል ደጋፊዎቻችን በመራጭነት እንዲመዘገቡ ከማበረታት ጀምሮ የህዝብና የፓርቲ ታዛቢ በመሆን የምርጫ ሂደቱን በሙሉ በንቃት እንዲከታተል እንዲሳተፍ የበኩላችንን ጥረት በማድረግ የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ከጅማሮው ህዝባዊ እንዲሆን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ይህ እርምጃም ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው የሚል እምነት አለን፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥው ቡድን መልካም ፍቃድ ወይም በማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደማይሰፋ ሊገነዘብ ይገባል። ምህዳሩ የሚሰፋውና ትክክለኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚኖረው ህዝቡ በጠቅላላ ከፍርሀት ቆፈን ተላቆ በሙሉ ልብ ለመብቱ ሲቆም፣ ለፓርቲዎች ተገቢው ድጋፍ ሲሰጥ፤ ከፍ ሲልም ወደ ትግሉ ሲቀላቀል መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በእኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ ነው። በዚህ ዘመቻ ላይ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment