Thursday, November 27, 2014

የሚሊዮኖች ድምፅ ቀጣይ መርሀ ግብሮች በቀለ ገርባ

November 27,2014
የሚሊዮኖች ድምፅ ቀጣይ መርሀ ግብሮች
አቶ በቀለ ገርባ
10734019_734141523337451_8980381146422839409_n
አቶ በቀለ ገርባ
ነሐሴ 21/2003 ዓ/ም ከምሠራበት ቦታ በስልክ ተጠርቼ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ከሚጠራው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተወስጄ ከአንዲት ትንሽ ጨለማ ክፍል ውስጥ ከተወረወርኩ በኋላ በማግስቱ አራዳ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርቤ የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆብኝ ተፈቅዶላቸው ያም ሲያልቅ እንደገና ሌላ ቀጠሮ ተጠይቆ ተፈቅዶላቸው፣ የማይመለከቱኝን ጥያቄዎች ስጠየቅና ስመልስ ቆይቼ ጥቅምት 3/2004 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቤ የክስ ወረቀት ደርሶኝ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተልኬ እነሆ እስከዛሬ ድረስ ዞን አንድ ቅጣት ቤት ተብላ በምትጠራው ቤት እገኛለሁ፡፡

የቀረበብኝ ክስ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 241 የተመለከተውን በመተላለፍ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል ሲሆን ዝርዝሩ፡- “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦ.ነ.ግ/ አባል በመሆን ሶሎሎ ጐልቦ ሥልጠና ወስደሃል፤ በጥር ወር 2002 ዓ/ም በአምቦ ከተማ ኦ.ነ.ግ በቅርብ ወደ አገር ውስጥ አሸንፎ ይገባል፤ ከጐኑ ቆመን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት መጣል አለብን ብለህ መመሪያ ሰጥተሀል፤ በሐምሌ 2003 ዓ/ም ተማሪዎችንና ህዝቡን ለአመጽና ለብጥብጥ እንዲነሳሱ ቅስቃሳ አካሂደሀል፤ እንዲሁም በ2004 ዓ/ም በመላው ኦሮሚያ አመጽና ብጥብጥ በማስነሳት በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መጣል አለብን በማለት ትዕዛዝ አስተላልፈሀል፤ በዚሁ ወር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነትህን ሽፋን በማድረግ ቢሮህ ተገኝተው የመመረቂያ ጽሁፍ ሊሰጡህ የመጡትን ተማሪዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት በሃይል ከሥልጣን እናውርድ በማለት መመሪያ ሰጥተሀል” የሚል ነው፡፡

እነዚህ የቀረቡብኝ ክሶች ፈጽሞ የሀሰት ውንጀላዎች መሆናቸውን ለማስረዳት በመጀመሪያ ደረጃ ትጥቅ ትግልና ሰላማዊ ትግልን አስመልክቶ ያለኝን አቋምና እምነት ባጭሩ ከገለጽኩ በኋላ በቀረቡብኝ ምስክሮችና የሠነድ ማስረጃ ላይ ያሉትን እውነታዎች አቅርቤ በአጭሩ የማጠቃለያ ሀሳብ እደመድማለሁ፡፡

1.የትጥቅ ትግል በአንድ ወገን ድል አድራጊነት የሚጠናቀቅ እንደመሆኑ አሸናፊውን ወገን ክብርና የበላይነትን ሲያጐናጽፍ ተሸናፊውን ወገን ደግሞ የውርደትና የበታችነት ስሜት ይፈጥርበታል፡፡ በዚሁ የተነሳ ተሸናፊው ወገን ቂም አርግዞ ጊዜውን ጠብቆ አድፍጦ የሚያደባበት ስለሆነ እውነተኛ ያልሆነ አሉታዊ ሠላም የሰፈነበት ነው፡ ፡ ፖለቲካውም የምሬት፣ የጥላቻ የበቀልና የጠላትነት ስለሚሆን እስራት፣ ስደት፣ ከሥራ መፈናቀልና ሌሎች ምስቅልቅሎችን ያስከትላል፡፡ ይህን የትግል ዘዴ በታሪካችን ደጋግመን ሞክረነዋል፡፡ መዘዙንም ቀምሰነዋል፤ ለኋላ ቀርነታችን አንደኛው ምክንያት ሆኗልና፡፡ በአንፃሩ ግን ሠላማዊ ትግል አሸናፊና ተሸናፊ ስለሌለው መቋጫው እርቅ ወንድማማችነትና ዘላቂ ሰላም ነው፡፡ አውንታዊ ሠላም ፖለቲካውም ልዩነትና ብዙሀንነት ስለሚያስተናግድ የሚማረር ወገን አይኖርም፡፡ ስለዚህ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ የትግል ዘዴ መሆን አለበት የሚል እምነት ስላለኝ ህጋዊ በሆነ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ የድርሻዬን በማበርከት ላይ እገኛለሁ፡፡

2.የትጥቅ ትግል አሸናፊው ቡድን የአልበገር ባይነት ስሜት እንዲሰማውና እብሪተኛና ጨካኝ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ድሉን ለማግኘት ለከፈለው መስዋዕትነት ካሳ ፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሥልጣንንና የሀብት ምንጮችን ጨምድዶ በመያዝ በትግሉ ያልተሳተፉትን በማግለል ፍትሀዊ ክፍፍልን አዛብቶ የዜጐችን የእኩልነት መብት ወደ መርገጥ ያመራል፡፡ ውሎ ሲያድርም ይህን ስህተቱን ማረም ስለሚሳነው የሃሳብ ልዩነትን የማይቀበል አምባገነን ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጐችን በጠላትነት ፈርጆ ሊያጠፋቸው ሕጋዊ የሚመስል ህገወጥ ድርጊቶችን በስውርና በግልጽ በመፈጸም ለሌላ ትጥቅ ትግል በር ይከፍታል፡፡ ይህን የትጥቅ ትግል ዑደት አንድ ቦታ ላይ ሰብሮ በማቆም አገሪቱን ከትርምስና የመገዳደል ባህል መታደግ የሚቻለው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ሳይገድሉ እየሞቱ እየታሠሩና ከሥራ እየተፈናቀሉ በሠላማዊ መንገድ ብቻ በሚታገሉ ኃይሎች አማካኝነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መርጬ እየተጓዝኩበት ያለሁትም ይህን ነው፡፡

3.የትጥቅ ትግል ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብትን ከማውደሙም በላይ ጊዜያዊም ቢሆን ሥርዓተ አልበኝነትን ያስከትላል፡ ፡ በጣም ውስን በሆነች የሀገር ሀብት አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ የሚሄድ ከሆነ መጨረሻችን የት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ የትጥቅ ትግል ለዜጎች ስንዴና ዘይት እንኳን ማቅረብ የማይቻል እንደኛ ያለ አገር ቀርቶ የሚዋጉበት በጦር መሳሪያ ለሚያመርቱ አገሮች እንኳን አዋጭ ስላልሆነ ዘለው አይገቡበትም፡፡ ብጥብጥና ሁከት በሚነሳባቸው አገሮች ዋነኞቹ ተጐጂዎች ተራ ዜጎች እንጂ እንደከሳሾቼ ያሉ ባለሥልጣናት ወይም የመንግሥት መሪዎች አይደሉም፡፡
በኛ አገርም ይህ ሁኔታ ቢከሰት ግንባር ቀደም ሰለባ መሆን ከሚችሉት ውስጥ እኔና ቤተሰቤ እንገኛለን፡፡ ምክንያቱም የምጓዘው በተራ ትራንስፖርት፤ የምኖረው በተራ መንደር በተራ ቤት፣ ልጆቼ የሚማሩት በተራ ትምህርት ቤት ሲሆን ከሳሾቼ ግን ይህ ሁሉ የማይመለከታቸውና የማያስጋቸው በመሆኑ ከነሱ የበለጠ ሠላም ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ነው ምንም ዓይነት ዜግነት፣ ቀለም ወይም ዘር ይኑርው ስብአዊና ቁሳዊ ውድመትን የሚያስከትል ጦርነትም ሆነ ብጥብጥ ከሚራምድ አካል ጋር የማልተባበረው

4.በትጥቅ ትግል ወደ ሥልጣን የሚመጡ መንግስታት ከውይይትና ድርድር ይልቅ በኃይል መፍትሔ ስለሚያምኑ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ከማቀጨጭ አልፎ እስከነአካቴው ይፃረራሉ፡፡ ለይስሙላ በሚገኙባቸው የድርድር መድረኮችም ሌላም ወገን እንዲቀበል የሚፈልጉትን ለመንገር እንጂ ሰጥቶ ለመቀበል ስላልሆነ በድርድሩ ማግስት ወደ ቀድሞ የኃይል ተግባራቸው ይመለሳሉ፡፡ ህዝቡ የጦር ሜዳ ገድሎቻቸውን አይቶና ሰምቶ አይበገሬነታቸውን ተረድቶ በፍርሃት እንዲገዛላቸው ሚዲያውን በጦርነት ወሬ ያደምቃሉ፡፡

በሰላማዊ ትግል አግባብ ስልጣን የሚይዙት ግን የስልጣናቸው ምንጭ የሆነው ሕዝብ ጥቅሙና መብቱ ካልተጠበቀለት ነገ ደግሞ ለሌላ መስጠት እንደሚችል ስለሚገነዘቡ ዜጐቻቸውን ያከብራሉ፤ ከመፍራት ይልቅ መከበርን ይሻሉ ከመናገር ይልቅ ማዳመጥን ያስቀድማሉ፡ ፡ እውነተኛ ዴሞክራሲን በማስፈን ሕዝባቸውን ወደ ዘላቂ ሰላምና እድገት ይመራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰላማዊ ትግል ነው እንዲካሂድ የምሻውና ዋጋ እየከፈልኩበት ያለው፡፡

5.በእምነት ዝንባሌዬ ነፍስ የፈጣሪዋ ብቻ ስለሆነች የሰውን ልጅ ነፍስ ማጥፋት ከወንጀል አልፎ ኃጢአት መሆኑንና ይህን ክቡር ነገር በኃይል ከሰው የሚነጥቁ ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ እንደሚነጠቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሠይፍ የሚመዙ በሠይፍ ይጠፋሉ” የሚለውን መለኮታዊ ቃል አምናለሁ፡፡ ስለዚህ የኃይል ተግባርን እንደአማራጭ ወስጄ አላውቅም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፈጣሪ እውነት ነው፤ በፈጣሪ የሚያምን ሁሉ እውነትን ያመነ ማለት ይገባዋል፡፡ “እውነትን ሲሻና ለፍትህ ሲከራከር በፍቅር ብቻ ማድረግ አለበት” የሚለውን የጋንዲ “ሳትያግራሀ” ፍልስፍና እቀበላለሁ፡፡ “ሳትያግራሀ” “የእውነት ኃይል፤ የፍቅር ኃይል” ማለት ሲሆን ጥቃት ለሚሰነዘር ሰው አፀፋ ሳይመልሱ በፍቅር ቀርቦ በውስጥ ያለውን መልካም ነገር በማንቀሳቀስ በህሊና ወቀስ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ማድረግ ይቻላል፡ ፡ የሚል ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ የሰላማዊ ትግል የመጨረሻ ተሞክሮ በሰላማዊ ታጋዩ ወይም ሳትያግራሂው ላይ ከፍ ያለ ሥቃይን የማያስከትል እንደመሆነ በአስተሳሰቦች በሞራላዊነታቸውና በትዕግሥታቸው የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች ብቻ የሚተገብሩት ነው፡፡ ከሳትያግራሀ የሰላማዊ ትግል ስልቶች አንዱና ዋነኛው ከክፉ ሥራ ጋር ያለመተባበር ነው፡፡ እኔም አንድን ዓላማ ለማሳካት ኃይልን ከመጠቀም የበለጠ ክፉ ነገር አለ ብዬ ስለማሰብ ከእንዲህ አይነት ተግባር ጋር ተባብሬ አላውቅም፡፡ እንግዲህ ትጥቅ ትግል ውስጥ ያልተሳተፍኩት እላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች እንጂ በማንምና በምንም ፍራቻ አሊያም አጋጣሚ አጥቼ አልነበረም፡፡ ከሳሾቼ እንደሚሉት ልጆች ሳላፈራና በትምህርት ሳልገፋ በአፍላ የወጣትነት ጊዜዬ ያላሰብኩትን ድንገት በሃምሳኛ ዓመት እድሜዬ ላይ በተራ የኦ.ነ.ግ ተዋጊነትና ካድሬነት ለመሠልጠን ኬንያና ሰሎሎ አልሄድኩም፡፡

ነፍስ ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች መብት እንዲከበር ጽኑ ፍላጎና አቋም የነበረኝ ቢሆንም ሁሉም ሰው ፓለቲከኛ መሆን አለበት የሚል እምነት ስላለነበረኝ እስከ 2002 ዓ/ም ድረስ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኜ አላውቅም፡፡ ተሰጥኦውና ዝናባሌው ያላቸው ጥቂቶች የፖለቲካ ማህበር መስርተው ለስልጣን ተወዳድረው ህዝባቸው በፍትሀዊነት ማስተዳደር ከቻሉ ሌሎች ዜጐች በተለያየ ሙያ ተሰማርተው አገራቸውን ማገልገል አለባቸው ብዬ ስለማምን እኔም በመምህርነት ሙያ ብቻ ተሰማርቼ ተግባሬን በትክክል ስወጣ ኖሬያለሁ፡፡

ይሁን እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰዎች ስብሰብ እንደመሆናቸው መጠን ሁሉን ነገር ያለእንከን ይፈጽማሉ ብሎ ማመን ስለማይቻል ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በመረዳት ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲ የሚሰብከውን መተግበር እየተሳነው ሲሄድ ወይም በተፃራሪው ሲተገብር ሆን ብሎ አለመሆኑን ለራሴ ለማሳመን ሃያ አመታት ያህል ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በመጨረሻም በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል ዝም ብሎ መመልከትን ህሊናዬ አልቀበል አለኝ፡፡

– ሦስት መቶ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጥያቄ እንኳን ሳይቀርብላቸው በአንድ ቀን ሲባረሩ
– በየዩኒቨርስቲው ያሉ ሌሎች ደግሞ በየዓመቱ ሲደበደቡና ሲንገላቱ
– የፋብሪካ ዝቃጭ አተላዎች በማንአለብኝነት ህዝብ ወደሚጠጣቸው ወንዞች ሲለቀቁና አደጋ ሲያስከትሉ
– ለፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛውን ገቢ የሚያስገባ ህዝብ በአንፃሩ ግን በነፍስ ወከፍ እጅግ ዝቅተኛው የፌዴራል በጀት ድጐማ ሲመደብለት
– መሬቱ በስበብ አስባቡ በግፍ እየተወሰደ ተቸብችቦ ሌሎችን ባለፀጋ ሲያደርግ፤ የሱ ቤተሰቦች ግን የትም ሲበተኑ
– ቋንቋው ቀድሞ ሲነገር ከነበረበት ቦታ እየጠፋ ሲሄድ
– ከኤኮኖሚው ዘርፍ ወጥቶ የበይ ተመልካች ሲሆን
– የዛሬ 120 ዓመት የኦሮሞ መንደር በነበረቸው ፊንፊኔ በቋንቋው የሚማርበት አንድ ት/ቤት ወይም አንድ የእምነት ሥፍራ እንኳ ሲነፈገው
– የፌዴራል ሠራተኞች ቅጥርና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራር ብሔራዊ ተዋጽኦ አግባብ ባልሆነ መልኩ ሲከናወን
– ከሁሉም በላይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ በእስር ቤት ከነበሩ ኦሮሞ፣ ዛሬ በብዙ እጥፍ የሚሆኑት በፌዴራል ወህኒ ቤቶች ሲማቅቁና ቤተሰቦቻቸው በረሃብ አለንጋ ሲገረፉ እያየሁ ዝም ማለት እንዴት ይቻለኛል?
እነዚህ ነገሮች እንዲሰተካከሉ ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በሠላማዊ መንገድ አስተዋፅኦ ለማድረግ የአንድ ፓርቲ አባል መሆንን ሳውጠነጥን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኦ.ፌ.ዴ.ን/ ጥሪ አድርጐልኝ በ2002 ዓ/ም ለመጀመሪ ጊዜ አባል ሆንኩ፡፡ ከዚያም የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆንኩ፡፡ በ2002 ዓ/ም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኜ መላው ሕዝባችን በሚያውቀው ሁኔታ ተሸነፍኩ፡፡ በምርጫ ዘመቻ ወቅትም በግልና በቡድን የተካሄዱብኝን ትንኮሳዎች ተቋቁሜ መንግሥት ባሰማራቸው ሁከት ፈጣሪዎች መካከል ቆሜ ለሠላማዊ ትግልና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ያለኝን ቁርጠኝነት አስመስክሬያለሁ፡፡ ምርጫውን እንደማላሸንፍና መጨረሻዬም አሁን ያለሁበት እስር ቤት እንደሆነ እየተነገረኝ አንድ ሰላማዊ ታጋይ ማድረግ ያለበትን አድርጊያለሁ፡፡

በፖርቲዬ ውስጥ በተሰጠኝ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ድርሻ ምክንያት በእስር ላይ ስላሉ ኦሮሞዎች ሁለት ጊዜ ያህል ለውጪ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ በመሰብሰብ ከሳሾቼን እንዳላስደስታቸው ከራሳቸው ተነግሮኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰጠሁት መረጃ ሀሰትም፣ ምሥጢርም እንዳልሆነ ነግሬያቸው በተያየን በሃያ ቀናት ከቢሮዬ ተጠርቼ ታሰርኩ፡ ፡ ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመጡ ሰዎች አነጋግረውኝ ነበር፡፡ የእነዚህ ነገሮች ድምር ነው “የአገርና የሕዝብን አንድነት በማፍረስ” ወንጀል አስከስሶ ለእስራት የዳረገኝ፡፡

በሕዝቦች መካከል ግልጽ ልዩነት እየፈጠረ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር ኅብረቱ እንዲላላና አንድነቱ እንዲፈርስ እያደረገ ያለ ሥርዓቱ ነው ወይስ ይህ ሁኔታ እንዲሰተካከል በሰላማዊ መንገድ እያሳሰበ በመታገል ላይ ያለ ሰው ነው የአገሪቱን የግዛትና የፖለቲካ አንድነት በማፍረስ ወንጀል የሚጠረጠረው? ህገ መንግሥቱን በተግባር እየጣሰ ያለውስ መብቴ ይከበር የሚለው ነው ወይንስ መብቱን የገፈፈው ነው?
ድርጅታችን በኢ.ፌ.ዴ.ን ህዝቦች መብታቸው እስከተከበረላቸው ድረስ የመገንጠል ጥያቄ አያነሱም መለየትንም አይፈልጉም የሚል እምነት ስላለውና የአገር አንድና ቁልፍ እውነተኛ እኩልነት የሰፈነበት ሥርዓት ማስፈን መሆኑን ያምናል፡፡

ስለዚህ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ያለው እስከመገንጠል የሚለው ሀረግ ጠቃሚ አይደለም በሚል እምነት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክረሲያዊ አንድነት መድረክ መለስተኛ የፖለቲካ ፕሮራም ውስጥ እንዲካተት ከፈረሙት አባል ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እኔም የድርጅቱ አባልና አመራር ይህን ለማሳመን ጉንበስ ቀና በምልበት ሰዓት የአገር አንድነትን ለማፍረስ በመሞከር እንዴት ልከሰስ እችላለሁ?
ማንኛውም ኦሮሞ መብቱን የመጠየቅ አዝማሚያ ወይም ከሥርዓቱ ጋር ያለመተባበር ዝናበሌ ያሳየ እንደሆነ በኦነግነት ፈረጆ ማናቸውንም የግፍ ተግባር መፈፀም ከተጀመረ ሃያ አመታት ተቆጠሩ፡፡ ይህ አድራጎት በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ሲታይ ወደር የለሽ ነው፡፡ ናይጄሪያ በየጊዜው ፍንዳታ እያደረሰ ኃላፊነት በሚወስደው የቦኮሃራሞ ድርጅት አግባብ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩና ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ዜጐቿን ቁም ስቅል አላሳየችም፡፡ የወደቀው የግብጽ መንግስት እንኳን ህገወጥ ነው ብሎ በፈረጀው የሙስሊም ወንድማማቼች ፓርቲ አመካኝቶ ተቀናቃኞችን ለማጥፋት ዘመቻ አልከፈተም፡ ፡ ከአንድ የዘር የተገኘ ሁሉ አንድ አይነት የፖለቲካ አመለካከት አለው ብሎ የሚገምት ቢኖር በሥልጣን ላይ
ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ይመስለኛል፡፡ አገር የሚያፈርሰው እንዲህ አይነት አመለካከት ነው፡፡ እኔ ግን ይህን በመርህም ተቀብዬ በተግባርም ሞክሬ አላውቅም፡፡
ነገር ግን ለሥርዓቱ ካለመመቸት ውጪ በሀገሬና በሕዝቤ ላይ አንዳች ጥፋት እንዳልፈፀምኩ ጠንቅቀው የሚያውቁት ከሳሾቼ በወህኒ ቤቶች አካባቢ “አዳፍኔ” በመባል የሚታወቁ የሀሰት ምስክሮችን አቅርበው አስመስክረውብኛል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 21 ላይ አጽመርስቴን አልለቅም ስላለ “ንጉሡንና እግዚአብሔርን ሰድቧል” ብለው የሀሰት ምስክሮችን አስመስክረው ናቡቴን በድንጋይ አስወግረው እንዳስገደሉት የአክአብ ባለሥልጣኖች የሰው ልጆች መብት ይከበር ባልኩ ኢትዮጵያዊው ናቡቴ ሆኜ ቀርቤያለሁ፡፡ ይህ ድርጊት ከዚህ መዘምር ከሳሾች እራሳቸው ሲኒማ ቤት ውስጥ የእጅ ቦምብ ወርውረው ብዙ ሰዎችን ካቆሰሉ በኋላ ይህን ያደረገው ማሞ ነው በማለት በሀሰት አስመስክረው ሞት ተፈርዶበት አለም በቃኝ እስር ቤት ውስጥ በስቃላት ተቀጥቷል፡፡
በኔ ላይ የቀረቡት የአቃቤ ህግ ምስክሮች በቁጥር አራት ሲሆኑ ሁለቱ ቤቴ ሲፈተሸ ታዛቢ የነበሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም ያዩትን በመመስክራቸው በምስክርነት ቃላቸው ውስጥ ወንጀለኛ የሚያሰኘኝ ነገር ባለመኖሩ ሌሎች ሁለት ምስክሮች በሰጡት የሀሰት ምስክርነት ቃል ላይ አተኩራለሁ፡፡ የአቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረበብኝ አንደኛው ሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዬ ሆኖ የተመደበ የክረምት ተማሪ ኢዮስያስ አበራ ማሞ ከሌሎች ተማሪዎች ተነጥሎ ቢሮዬ መጥቶ የገዥው ፓርቲ አባል እንደሆነ ይህን ያደረገውም የደህንነት አባል የሆነውን አባቱን በመፍራት እንደሆነ አሁን ግን በፓርቲው ውስጥ የሰፈነውን ኢፍትሐዊነት በመፀየፍ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን እንደሚፈልግ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክን እንደሚያደንቅ ነግሮኝ እንድመለምለው ጠይቆኝ ነበረ፡፡ እኔም እኔ ያለሁበት ፓርቲ የኦሮሞ ድርጅት እንደሆነና የመድረክ አባላት ከሆኑ ህብረብሔር ፓርቲዎች ውስጥ ወስኖ አንዱን መጠየቅ እንዲሚችል ነግሬው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባል የሆነውን የአቶ አንዱአለም አራጌን ስልክ ቁጥር ሰጠሁት፡፡

ግለሰቡ ክቡር ፍ/ቤቱ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ ተማሪዬ እንደሆነ ኮርስ ሰጥቼው እንደማላውቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ሐምሌ ወር 2003 ዓ/ም የመመረቂያ ጽሁፉን ሊያስረክብ ቢሮዬ በተገኘበት ዕለት መሆኑን በዚሁ የመጀመሪያ ግኑኝነታችን “መንግሥት የኦሮሞንና የደቡብን ህዝብ ስለሚጠላ ይጨቁናቸዋል፣ ስለዚህ ተነሳስተን በአመጽ እናስወግደው” እንዳልኩት ተናግሯል፡፡ ሌሎችንም ተማሪዎች ጨምሮ እንደተወያየን አስመስሎ መስክሯል፡፡

ይህ ግን ፈጽሞ ሀሰት ነው፡ ፡ ግለሰቡ አግኝቶኝ የማያውቅ ከሆነ በሐምሌ 2003 ዓ/ም ሊያስረክበኝ የመጣው የመመረቂያ ጽሁፍ ማን ያማከረውን ነበር? ከአማካሪው ጋር አንዳች ግንኙነት ሳያደረግ ምንነቱ ያልታወቀ የመመረቂያ ጽሁፉን ይዞ ከመጣ ተማሪ ጋር ያውም በመጀመሪያው ግንኙነት ከአካዳሚ ነክ ጉዳዮች ወጥቶ ስለ መንግስት ግልበጣ ማውራት ይታሰባል ወይ? ለአንድ የዩኒቨርስቲ መምህር ተመካሪ ተማሪዎች የሚመደቡት በሚመለከተው ትምህርት ክፍል እንደመሆኑ የተለያየ ፖለቲካ ዝናባሌ እንዳላቸው እየታወቀ አንድን ወገን ብቻ በሚመለከት ፖለቲካ ውይይት መክፈት እንዴት ይታሰባል? የተከሰሰኩት በአሽባሪነት ከተፈረጀ የኦሮሞ ድርጅት ሆኖ ሳለ ግለሰቡ ደግሞ የዚህ ማህበረሰብ አባል አለመሆኑን በግልጽ እየተናገረ፤ ኦሮሞዎች ተበድለዋልና በመንግስት ግልበጣ ተባብረን ልል እንዴ እችላለሁ? ይህ ሰው ኦሮሞዎችን ከጭቆና ለመታደግ ከሰማየ ሰማያት የተላከ አዳኝ ነው ብዬ ልገምት አልችልም፡፡ ይልቅ እሱስ ፍትህን ሲገድል የተመደበ የአክአብ ምስክር ኖሯል፡፡
ሌላኛው ስሜን እንኳን በትክክል ያላስጠኑት የአቃቤ ሕግ ምስክር አመና አርኮ በክቡር ፍ/ቤቱ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ “በጥር ወር 2002 ዓ/ም አቶ ጉቱ ሙሲሳ ቤት ተገናኝተን ለአመጽ አነሳስቶኛል” ሲል ተናግሯል፡፡

እኔ ይህን ግለሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ከዚሁ ፍ/ቤት ውስጥ ነው፡፡ ነገሩ የማይታመንና ዱብዕዳ ስለነበረ በዕለቱ ጥያቄም አላቀረብኩለትም፤ ስለማንነቱ ለማወቅ ባደረግሁት ጥረት በቂና ተጨባጭ መረጃዎችን ለማግኘት ችያለሁ፡፡ ግለሰቡ እውነተኛ ማንነቱ ኢመና ኢርኮ ሳይሆን ሺፈራው ኤቢዳ ሲሆን የትውልድ ሥፍራው በምዕራብ ሸዋ ዞን ሸነን ወረዳ ሆኖ አድራሻዬና የሥራ ቦታዬ ነው ያለውን ነቀምቴ ከተማ 01 ቀበሌን ረግጦ እንኳን አያውቅም፡፡

ይህ ግለሰብ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ /ኦ.ህ.ኮ /አባል የነበረ ሲሆን በ1997 ዓ/ም የምርጫ ታዛቢ ስነበር በ1998 ዓ.ም ታስሮ የተሠቃየ በ1999 ዓ.ም አጣሪ ኮሚሽን ፊት ቀርቦ ቃሉን የሠጠ በ2000 ዓ/ም ኦህኮን ወክሎ ለወረዳና ለቀበሌ ምርጫ የተወዳደረ፡ ፡ በ2003 ዓ/ም እንደገና ታስሮ የነበረ ሲሆን ይህን ሁሉ ያደረገው በእውነተኛ ስሙ ነበር፡ ፡ በመጨረሻም ከደረሰበት ስቃይ የተነሳ እንዲሁም የሚሉትን እሺ ካላለ መኖር እንደማይችል ስለተገለጸለት ያሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ግብቶ በመፈታት በኔ ላይ በምስክርነት የቀረበ ነው፡፡ ይህንን የመከላከያ ምስክሮች ያስረዱልኛል፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት ከግለሰቡ ጋር በአካልም ሆነ በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ተገናኝተን የማናውቅ ከመሆን አልፎ ቤቱ ተገናኘን ያለውን አቶ ጉታ ሙሊሳን እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ማረሚያ ቤት ሁለታችንም እስረኞች ሆነን ነው፡፡ ይህንንም ምስክሮቼ ያረጋገጡልኛል ለመሆኑ በ2002 ዓ.ም ህገ መንግሥቱን አምኜና አክብሬ በምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የነበርኩ ሰው እንዴት ሆኖ ለአመጽ ቅስቀሳ ማካሄድ የምችለው?
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ግለሰቡ በኔ ላይ ስለመሰከረው ነገር ብቻ ሳይሆን ማንነቱንና አድራሻውን ጭምር እንዲዋሽ የተገደደ እንደመሆኑ መጠን ክቡር ፍ/ቤቱ ይህን ተመልክቶ የሰጠውን የምስክርነት ቃል ውድቅ እንዲያደርገልኝ እጠይቃለሁ፡፡
አቃቤ ህግ ወንጀለኛ ለመሆኔ እንደአስረጂነት ያቀረበው ሌላው የሠነድ ማስረጃ በ1989 ዓ/ም መጀመሪያ ላይ የተነሳሁት የኦነግ አርማ ተሰቅሎ የሚታይበት ፎቶ ግራፍ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም መጨረሻ ደረግ እሠራበት የነበረችውን ዓለም ተፈሪ ከተማ ለቆ ሲሄድ ብዙ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ሲሰደዱ ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የተቋቋመውን ኮሚቴ እንድመራ በህዝብ ተመርጬ እስከ 1984 ዓ/ም መጨረሻ ድረስ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ወቅት በከተማው ፍ/ቤት ከፍተው በይፋ ይንቀሳቀሱ ለነበሩ ሁለት የኦሮሞ ድርጅቶች ኦህዴድና ኦነግ ስብሰባዎችን እየጠራሁና እየመራሁ በገለልተኝነት ሥሰራ ቆይቻለሁ፡ ፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ለኦህዴድ በርካታ ስብሰባዎችን ለኦነግም ጥቂት ሰብሰባዎችን ከተማው መሃል በሚገኝ የወረዳው አስተዳደር ግቢ ሜዳ ላይ መጥራቴን አስታውሳለሁ፡ ፡ ከነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ የተወሰደ ነው የተጠቀሰው ፎትግራፍ ያ ወቅት ሁለት ድርጅቶች እንኳን በመሰብሰቢያ ቦታዎች ቀርቶ በየምሶሶዎቹና ዛፎቹ አርማቻቸውን ይሰቅሉ የነበረ የትኩሳት ጊዜ ነበር፡፡
ኢፍትሐዊነትንና አድሎን …
ከ ገፅ 15 የዞረ….
በፎቶግራፍ ላይ እንደሚታየው ቁጥሩ ብዙ የሆነ ህዝብ ሜዳ ላይ ተሰብስቦ ይታያል፡፡ እንደሚታወቀው ኦነግ በ1984 ዓ/ም በመጨረሻ ሽግግር መንግሥቱን ለቆ ከወጣ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስብሰባ በመሀል ከተማ አደባባይ ሊደረግ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በፎቶ ግራፉ ላይ የሚታዩ ሰዎች ብዙዎች በህይወት የሉም፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው የራሴ ገጽታም ከዛሬ ጋር ሲስተያይ የፎቶውን ዕድሜ ይናገራል፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው ቦታም ዓለምተፈሪ መሆኑ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ እኔ ደግሞ በ1985 ዓ/ም ከዚያ ተዛውሬ ስለሄድኩ እና ወደዚያ ለመመለስ እድሉ ስላልነበረኝ፣ ቢኖረኝ ኖሮም ያንን ሰብሰባ ማካሄድ እንደማልችል ይታወቃል፡፡
በአጠቃላይ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በወቅቱ ህጋዊ የነበረና በሚኒስትሮች ም/ቤት አራት የካቢኔ ሚኒስተሮች የነበሩትና መዲናዋን (አዲስ አበባን) ጭምሮ በአርማዎቹ አጥለቅልቆት በነበረ ድርጅት አርማ ጋር የተነሳኸው ፎቶ ግራፍ የአገር ግዛትና ፖለቲካዊ አንድነት ለመንካትህ ማስረጃ ነው ተብሎ ሊቀርብብኝ ስለማይገባ ክቡር ፍ/ቤቱ ውድቅ እንዲደረግልኝ እጠይቃለሁ፡፡
ማጠቃለያ
ያለመተደል ሆኖ በአገራችን መልካም አስተዳደር አፈአዊ እንጂ ተግባራዊ ሆኖ ስለማያወቅ አንዱ የሠራውን ሌላው እያፈረሰ በዓለም ፊት በኩራት አንገታችንን ቀና የምናደርግበት ሳይሆን በሀፍረት የምንሸማቀቅበት፤ ለልጆቻችንም ተስፋን ሳሆን የስጋት ቅርስ እየተውንላቸው አበሳን እንደ ዱላ እየተቀባበልን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ እንዳይቀጥል የሳተው በጊዜ እንዲመለስ የተጣመመው እንዲቃና የተበላሸው እንዲስተካከል ጎረቤት ሳይሰማ፣ ፈረንጅ ገመናችንን ሳያውቀው አድብተን ሰንጠፋፋ ችግራችን ገለጥለጥ አድርገን ተወያይተን ተከራክረን ተወቃቅሰን መፍትሔ እናበጅለት፡፡ ይህንንም አንዱ ባንዱ ላይ ዱላ ሳይሰነዝር ቃታ ሳይስብ፣ ወደ እስር ቤት ሳይጎትተው በሠላማዊ መንገድና በፍቅር እናድርገው የሚል ጽኑ አቋም ነው፡፡ እኔና ድርጅቴ የምናራምደው፤ ይህ በኛ በጎ ጥረትና ፍላጎት ብቻ የሚሳካ ባይሆንም እኛ ግን በዚሁ መንገድ እንጓዛለን፤ ኢፍትሃዊነትንና አድልኦን አሜን ብሎ ውርደት ከመቀበል መከራና ስቃይን በክብር ማስተናገዳችንን እንቀጥላለን፡፡ በመጨረሻም ፍትህ ከጎናችንትቆማለች፡፡

No comments:

Post a Comment