Thursday, October 16, 2014

በግል ፕሬሶች ላይ የተከፈተው ዘመቻ ለነፃነት የቆሙ ዜጎችን አንገት የሚያስደፋ አይሆንም !!!

October 15,2014

ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

******************
UDJበግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለው እስር ሀገር ለቀው እንዲሰደዱ የሚደረገው አሰተዳደሪዊ ጫና እንዲሁም የግል ሚዲያው ዘርፍ ላይ እየተፈፀመ ያለው ሴራ ገዢው ፓርቲ በህገ ወጥ መንገድ በስልጣን ለመቆየት ከሚወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ገዥው ፓርቲ በሚከተለው ከዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያፈነገጠና ሴራን ማዕከል ያደረገው ፖለቲካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከመሄዱም ባሻገር በአደባባይ የሚከወን አሳፋሪ ድርጊት ሆኗል፡፡ ይህም የሚያሳየው ገዢው ፓርቲ በስልጣን የሚቆየው በሃሳብ የበላይነት ሳይሆን ለጊዜው በቁጥጥሬ ስር ናቸው በሚላቸው የመንግሰት መዋቅሮችን በመጠቀም መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፓርቲያችን የኢህአዴግ የ2007 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ዘመቻ አካል እንደሆነ የሚያምነው ማሳደድና ማሰር በጋዜጠኞች ላይ ተጠናክሮ መቀጠሉ ገዢው ቡድን አሁንም መግባባት የተሞላበት ምርጫ እንዲከናወን ፍላጎት እንደሌለው ያረጋግጣል፡፡ የዚህ ዓይነት ድርጊትን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት ከማባባስ ውጭ የሚጨምረው ፋይዳ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ በዚህ የተነሳ ለነፃነት የቆሙ ዜጎች አንገት ያሰደፋል ብለንም አናምንም፡፡
በዓለማቀፍ ደረጃ አንገታችንን እንድንደፋና እንደ ዜጋ እንድንሸማቀቅ በሚያደርግ መልኩ በተወሰደው አማራጭ የግል ፕሬስ የማጥፋት እርምጃ በርካታ ጋዜጠኞች ለሚወዷት ሀገራቸው ጀርባቸውን ሰጥተው ስደትን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ በቅርቡ ያለወገን ድጋፍና ያላስታማሚም የስደት ሰለባ የሆነው የግል ፕሬስ ባልደረባ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ በተሰደደ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ህይወቱ ማለፉ አሳዛኝ ክሰተት በመሆኑ ፓርቲያችን ለቤተሰቦቹና ወዳጆቹ አዘኑን ይገልፃል፡፡ ለዚህም ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ጋዜጠኞች በሀገራቸው ላይ የመስራት መብታቸው ተገፍፎ በሚደርስባቸው ወከባ ከሀገር እንዲሰደዱ ያደረገው መንግስት ሃላፊነቱን መውሰድ አለበት፡፡ ገዢው ቡድን የሚሊዮንን ሞተ አስመልክቶ ለሚነሳ የህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ እንፈልጋለን፡፡
በተሰደዱ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ሰምተን ሳናበቃም አልሰደድም ባሉ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የገዥውን ፓርቲ አምባገነንነት ሳይታክት በግልፅ የሚተቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሀገራችን ህገ መንግሰት አንቀፅ 29 በተደነገገው መስረት ሃሳቡን በነፃነት ስለገለፀ ብቻ ህግን ተገን ተደርጎ በተከፈተበትና ለአመታት ፍርድ ቤት ሲመላለስ በኖረበት ክስ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ የምርጫ ወቅቱን ጠብቀው ጥፋተኛ በማለት ወደ ወህኒ ቤት ማውረድ ፖለቲካዊ እርምጃ መሆኑን አንጠራጠርም፡፡ ፓርቲያችን ይህን በህግ ሽፋን የሚፈፀም የፖለቲካ ሸፍጥ በቁርጠኝነት መታገሉን እንደሚቀጥልና እንደዚህ አይነቱ ግፍ ሊቆም የሚችለው ህዝቡን በማስተባበር በሰላማዊ ትግል አምባገነኑን ስርኣት መቀየር ሲቻል እንደሆነ ያምናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን በመቆም የዜጎች የመከራ ዘመን እንዲያጥርና ፍትሃዊነት እንዲሰፍን እንድናደርግ ሃገራዊ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
በግፍ የታሰሩ ጋዜጠኞች፤ ጦማሪያንና ፖለቲከኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም እንጠይቃለን፤ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከገዥዎች በችሮታ የሚሰጥ እንዳለሆነ ህዝቡ የሚገነዝብና መንግስት በሚወሰደው እርምጃ የተነሳም አንገቱን የሚደፋ አንድም ነፃነት ወዳድ ዜጋ እንደማይኖር እናረጋግጣለን፡፡
በመተባበር የኢትዮጵያውያንን መከራ ዘመን እናሳጥር!!
-- 

No comments:

Post a Comment