Friday, August 15, 2014

የሁለተኛው የበይነመረብዘመቻ ጋዜጣዊ መግለጫ!(ዞን ዘጠኝ)

August 15, 2014
“ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ለሁሉም፣ አሁኑኑ!”

ዞን ፱ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ የተለየ ተረክ ለመፍጠር እና ለአገሪቱ ሁለንተናዊ መሻሽል የሚበጁ ሐሳቦች የሚፈልቁበትን ሕዝባዊ ተዋስኦን ለማበረታታት ብሎም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ እና በአገር ጉዳይ በቂ መረጃ ያላቸው አንባቢያን ለመፍጠር የተመሠረተ ኢ-መደበኛ የጦማሪዎች እና አራማጆች ቡድን ነው፡፡

ይህንን ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ፣ ወቅታዊ የበይነመረብ ዘመቻዎችን ማካሄድ ውጤታማ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ስለሆነም፣ በ2005 ብቻ አራት ዘመቻዎችን ለማካሄድ ያቀድን ሲሆን የመጀመሪያውን ዘመቻ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር›› በሚል መርሕ ከሕዳር 27 እስከ 29/2005 ለሦስት ቀናት ያክል በማካሄድ በበቂ ሁኔታ ውጤታማ የተባለ እና በሕገ መንግሥቱ ጉዳይ በርካታ ኢትዮጵያዊ የበይነመረብ ማኅበረሰብን ያዳረሰ ዘመቻ ሊሆን በቅቷል፡፡

የሁለተኛው የበይነመረብ ዘመቻችን ከነገ (የካቲት 14) ጀምሮ እስከ ቅዳሜ (የካቲት 16/2005) ድረስ ‹‹ሐሳብን የመግለጽ
ነጻነት ለሁሉም፣ አሁኑኑ!›› በሚል መርሕ ይካሄዳል፡፡ የዘመቻው መርሕ ከሕገ መንግሥታዊ መብቶች በአንዱ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም ባሻገር የዞን ዘጠኝ ጦማር እና የፌስቡክ ገጽም ጭምር መታገዱን እና ሌሎችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ የመጡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አፈናዎች እንደምክንያት አድርጎ የተመረጠ መርሕ ነው፡፡ የዚህ ዘመቻ ጥቅል ግብ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣውን የቀጥታ እና ተዘዋዋሪ ሳንሱር መበራከት የሚያመጣው ውጤት ላይ ያለንን ስጋት ማንፀባረቅ ነው፡፡ የሳንሱር ዓይነቱ የተለያየ ነው፤ ከዜጎች በፍርሐት ግለ-ሳንሱር ማድረግ ጀምሮ እስከተደራጀ የመንግሥት ጦማሮች እና ድረገጾች ብሎም ጋዜጣና መጽሔቶች እገዳ ድረስ ይዘልቃል፡፡

ለጥቂቶቹ የሳንሱር ተግባራት የሕዝቦችን አብሮነት ለመጠበቅ የተደረጉ እንደሆኑ ተደርጎ ምክንያቶች ቢሰጡም ምንም ምክንያት የማይሰጥባቸው ሌሎች እገዳዎችም ቀላል አይደሉም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ እርምጃዎች በመጨረሻ አማራጭ ሐሳቦችን በመግደል መንግሥትን ያለተጠያቂነት ያስቀረዋል የሚል ፍራቻ አለን፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ቀጥለን የምንዘረዝረው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 እንዲከበር የምንጠይቀው፡-

1. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡

2. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡

3. የኘሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነጻነት ተረጋግጧል፡፡ የኘሬስ ነጻነት በተለይ የሚከተሉትን መብቶች ያጠኝልላል፣

ሀ/ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣

ለ/ የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን፡፡

4. ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ኘሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡

5. በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፡፡

6. እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሀሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ሕጐች ብቻ ይሆናል፡፡ የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡ የጦር ቅስቃሴዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ ይሆናል፡፡

7. ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን የችላል፡፡

ዘመቻው በሚካሄድባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ በዞን ዘጠኝ ጦማር እና የፌስቡክ ገጽ እንዲሁም ለዚሁ ዘመቻ ሲባል በተፈጠረው ሕገ-መንግሥቱ ይከበር የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ላይ
የተለያዩ የመብቱን ጥሰት ደረጃ የሚያሳዩ፣ አማራጭ ሐሳቦችን የሚያመለክቱ እና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጽሑፎች እና አስተያየቶች ይቀርባሉ፡፡.

የዘመቻው ዋና መካሄጃ መደብ ፌስቡክ እና ትዊተር ይሆናሉ፡፡ መጣጥፎች እና አጫጭር አስተያየቶች በዘመቻው ገጽ እና በሌሎችም ግለሰቦች ገጽ ላይ ይቀርባሉ፤ በትዊተር ላይ ‘#StopCensorship’ በሚል ‹ሐሽታግ› አስተያየቶች እና እውነታዎች ይሰፍራሉ፡፡ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዘመቻውን በሚመቻቸው መንገድ እንዲቀላቀሉ በማሰብ የተዘጋጀላቸውን የፕሮፋይል ምስል እና ባነሮች ይጠቀማሉ፡፡

የዞን ዘጠኝ ቡድን አባላት እና ወዳጆች፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች፣ የመጀመሪያው ዘመቻችን ላይ ያሳዩትን ጉልህ ተሳትፎ፣ አሁንም በሁለተኛው ዘመቻ ላይ በማድረግ ለሐሳብ ነጻነት ያላቸውን ተቆርቋሪነት እንዲያስመሰክሩ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡
ስለሚያገባን እንጦምራለን!!!
ዞን ፱!
ኢሜይል: zone9ners@gmail.com;

No comments:

Post a Comment