Wednesday, August 27, 2014

ከፖለቲካ ተሰናባቹ አቶ ሙሼ ሰሙ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ

August 27/2014
“የኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪዎች ትግሉን ውስብስብና እልህ አስጨራሽ አድርገውታል”
“ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ለመሆን የሚያስችል ቁመና አልፈጠሩም”
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ን ከመሰረቱት አንጋፋ ፖለቲከኞች አንዱ የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኢዴፓን ከ92 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት፣ በዋና ፀሐፊነትና በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ሙሼ፤ ከፓርቲያቸው መልቀቃቸውን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ዙሪያ በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡ በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ፣ኢዴፓና እሳቸው ለአገሪቱ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ስለመጪው ምርጫ፣ ስለተከሰሱት የግል የፕሬስ ውጤቶች፣ ስለኢህአዴግ…እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
Mushe Semu
Mushe Semu
– ባለፈው ሳምንት ከፓርቲ ፖለቲካ ራስዎን እንዳገለሉና ለፓርቲዎ የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳስገቡ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ ምክንያትዎን ቢያብራሩልን?
አቶ ሙሼ ሰሙ- ከኢዴፓ ጋር ላለፉት 15 ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ በፓርቲው ውስጥ የአመራርነት ሚና ነው የነበረኝ፡፡ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የፓርቲውን የፖለቲካ ፍልስፍናና አቅጣጫ በመቅረፅ—ስራ እሳተፍ ስለነበር ፋታ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ጫና የበዛበት ነው፡፡ በዚህ ቦታ በአንድ መስክ ተሰማርቶ መቆየት ቆም ብሎ ራስን ለመፈተሽና ለመገምገም ጊዜ አይሰጥም፡፡ የሄድኩበት መንገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበረ፣ ከዚህስ ማህበረሰቡ ምን ተጠቅሟል—የሚለውን ለመረዳት ትንፋሽ መውሰድ —- ራሴን ማረጋጋት አለብኝ ብዬ ወስኛለሁ፡፡ ከተቋማዊ አሰራር ወጣ ብዬ ራሴን መገምገም ፈልጌአለሁ፡፡
የኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ እንደ ባህል የተለመደ ነገር አለ፡፡ ሰዎች ሰሩም አልሰሩም፣ፋይዳ ኖራቸውም አልኖራቸውም ተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ዝም ብሎ የመቆየት ባህል፡፡ እየታገሉ መኖር ይቻላል፤ ነገር ግን ለመኖር ብቻ የሚኖርበት ሁኔታ አለ፡፡ እዚያ ፓርቲ ውስጥ መቆየቴ አንድ ቀን ለውጥ ይመጣና የማገኘው ጥቅም ይኖራል ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሻሻልና ሚናዬን ለመፈተሽ እድል ይሰጠኛል በሚል ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
አቶ ሙሼ ሰሙ-
 እኔ ግን በአንድ ፓርቲ ውስጥ እስከአለሁ ድረስ ስራዬን መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሚገባውን ሰዓትና ጊዜ ሰጥቼ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ የስራዬ ባህሪ፤ ለረዥም ጊዜ ባለማቋረጥ በትግሉ ውስጥ በመቆየቴ፤ የቆየሁባቸውም ጊዜያቶች በከፍተኛ አመራር ውስጥ በመሆኑ—-ቆም እንድልና ራሴን እንድመረምር አስገድዶኛል፡፡ ለእንጀራ የሚሰራ ስራም ቢሆን እኮ 15 ዓመት ይሰለቻል፡፡
-የእርስዎን ከፓርቲ ፖለቲካ ራስን ማግለል አስመልክቶ አንዳንድ ወገኖች “መጪውን የ2007 ምርጫ ሽሽት ነው፤ ከፖለቲካ ጫና ራስን ለማግለል ነው” የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ ይሰማል…
አቶ ሙሼ ሰሙ-
ሰዎች ብዙ ነገር ሊሉ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ቁምነገሩ ግን ከእኔ እምነትና አስተሳሰብ ጋር ነው ያለው፡፡ በአለፉት 15 የትግል ዓመታት ከተቃዋሚዎችና ከመንግስት በኩል የተለያዩ ጫናዎችን አሳልፌያለሁ፤ ታስሬያለሁ፤ ተሰድጃለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ ጫና ተቋቁሜ መጥቻለሁ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ተቃዋሚው ኃይል የነበረው ጫና፣ ግፊት፣ ስም ማጥፋትና ዘመቻው እጅግ ከባድ ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን ሃሳቤን አልለወጥኩም። ጫናን የምፈራ ቢሆን ኖሮ ወደ ትግሉ አልመጣም ነበር፤ እነዚያን የጫና ዘመኖች ተቋቁሜ አላልፍም ነበር፡፡ በምርጫ ወቅት የስራ ጫና ይበዛል፤ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም፡፡ በየአካባቢው ተሂዶ አባላት ከመመልመል ጀምሮ ቅስቀሳ እስከ ማድረግ ያለው ስራ ከባድ ነው፡፡ “እንደዚህ አይነት ከባድ ስራ አሁን መቋቋም ትችላለህ ወይ?” ብትይኝ፣ አሁን አልችልም። እረፍት እፈልጋለሁ፤ ትንፋሽ መውሰድ አለብኝ፤ ራሴንም ቆም ብዬ መገምገም ያስፈልገኛል፡፡ እንደ ሀገራዊ ምርጫ ያለን የምርጫ ዘመቻ ለመምራት ጊዜ ያስፈልጋል፣ መረጋጋትን —- አእምሮ ነፃ ሆኖ መዘጋጀትን ይጠይቃል።
-ምርጫውን ሽሽት ነው የሚሉ ተሳስተዋል ማለት ነው?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አምስት ጊዜ አገር አቀፍ ምርጫ ተደርጓል፤ በአራቱ ተሳትፌያለሁ፡፡ የተለየ የምርጫ ባህሪ የታየበት 1997 ዓ.ም ነው፡፡ የተለየ ባህሪ እንዲኖረው ያደረገው ትግሉ የሄደበት መንገድ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ በፖለቲካው ታስሬበታለሁ፡፡ ከምርጫው ውጪ በነበረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታስሬያለሁ፣ ተሰድጃለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከዚህ በላይ ሊኖር አይችልም፡፡ መጪው ምርጫ እንደዚህ ቀደሙ አስቸጋሪና የተወሳሰበ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በውጤቱም ቢሆን ብዙ ትርጉም ያለው ነገር ይገኝበታል ብዬ አላስብም፡፡ ተቃዋሚውም ኃይል በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መንግስትን የሚገዳደርበት ጉልበት እየፈጠረ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ መጪው ምርጫ ለተቃዋሚው በጎ ነገሮች አያመጣለት ይሆናል እንጂ ችግር የሚከሰትበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የ2007 ዓ.ም ምርጫ ከእኔ ውሳኔ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡
-አሁን ባሉት የኢዴፓ አመራሮች ፓርቲው በመጪው ምርጫ ውጤት ያመጣል ብለው ያስባሉ?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
 ሰዎች እንደየአቅማቸው የተለያየ ባህሪና አቋም ይኖራቸዋል፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን ኢዴፓ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ አመራሮች ወጣቶች ናቸው፡፡ በትግል ተመክሮዋቸው ጠልቀው የሄዱ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሌሎች ጠንካራ ጐኖች አሏቸው። እኛ ስንጀምር ኢዴፓን ኢዴፓ ለማድረግ ትልቁ ጉልበታችን ወጣቶች መሆናችን ነበር፡፡ አሁን አርጅተናል ማለቴ አይደለም፡፡ ሰርተን አይደክመንም፤ ሀሳባችንን በሰዎች ዘንድ ለማስረፅ አንታክትም፡፡ ያ የፓርቲያችን ጠንካራ ጎን አሁንም ኢዴፓ ውስጥ አለ፡፡ አሁን ፓርቲው ውስጥ ያሉት ልጆች እየተማሩ ያሉ ናቸው፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ እና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ልጆች ናቸው። የእኛን ዓይነት ተመክሮ ላይኖራቸውና አጋዥ ኃይል ላይሆናቸው ይችላል፡፡ ይሄ አስቸጋሪም ቢሆን መታለፍ ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሰው ላይ እየተማመኑ ፖለቲካ ማራመድ አይቻልም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ትግሉን እየተገዳደረ እያሸነፈ፣ እየሰበረ፣ እየለወጠ መሄድ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሊቸገሩ ይችላሉ፤ ችግሩ ግን የትግሉ አካል ነው፡፡ አቅማቸውን ለማጠናከርና ለማጎልበት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ያለው ተጨባጭ ሁኔታም ያግዛቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቅሬታ የሰላ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለኢህአዴግ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል። ድህነት፣ ረሃብ፣ ስራ አጥነት፣ የአገልግሎት እጦት፣ የትራንስፖርት ችግር— እነዚህ ሁሉ ቅራኔዎች በቅጡ ከተያዙና ከተጠቀሙባቸው ሌላ ተጨማሪ መታገያ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አላምንም፤ እናም ለውጤት ብዙ ሩቅ አይደሉም፡፡
- “ሶስተኛ አማራጭ” የሚለው የፓርቲው ስትራቴጂ አሁንም ቀጥሏል?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
 ሶስተኛ አማራጭ የፓርቲው መሰረታዊ አቋም ነው፡፡ ይሄን አቋም የሚሸረሽርበት፤ አስተሳሰቡን የሚለውጥበት ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ እስካሁን ካለኝ ተመክሮ ለኢዴፓ የተለየ ዋጋ ከሚያሰጡት ነገሮች አንዱና ሊደርስበት ላሰበው ግብ እንደ ትግል ስልት የሚጠቅመው መንገድ ይሄ ብቻ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እኔ የምወስነው ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን እኔ ኢዴፓ ውስጥ አይደለሁም፤ ኢዴፓ ውስጥ ያሉ ሰዎች “ለትግል የሚያዋጣን ስልት ይሄ ነው” ብለው እስከአመኑ ድረስ ይቀጥሉበታል፡፡ ይሄ የእነሱ ውሳኔ ነው የሚሆነው።
-በ15 ዓመት የትግል ዘመንዎ፣ ለኢትዮጵያ ምን አበረከትኩ ብለው ያስባሉ?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
ትልቁ ነገር ኢዴፓን መመስረታችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ኢዴፓ ፓርቲ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ የህብረ ብሄራዊ አስተሳሰብና አጀንዳ እጅግ የተዳከመበት ጊዜ ነበር፤ ህብረ ብሄራዊነት የሚያዋጣ የትግል ስልት እንደሆነ አምነን፤ ህዝቡንም አሰባስበን ለሚፈልገው ግብ ለማድረስ፣ አደረጃጀትን በዚህ መንገድ መቀየድ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር እንደ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ማድረጋችን ትልቁ ድላችን ነው፡፡ በዚያን ወቅት በህብረ ብሄራዊ አስተሳሰብ የተደራጀ ማንም አልነበረም፡፡ ለረዥም ጊዜ በህብረ ብሄራዊነት መደራጀት ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ ሆኖ የቆየበት ጊዜ ስለነበር፣ ያ ትልቁ አስተዋፅኦዬ ነው እላለሁ፤ እንደ ድርጅት፡፡
ሰላማዊ ትግል ብቸኛው አማራጭ መሆኑን፣ በሰላማዊ ትግል ውስጥም ህገ መንግስቱን ማክበርና ልዩነቶችን በግልፅ አውጥቶ መታገል እንደሚቻል… ይሄን አስተሳሰብ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በህዝቡ ውስጥ ማስረጽ ችለናል፡፡ እኛ ወደ ትግሉ ከመምጣታችን በፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው ህገ መንግስቱን የሚያዩበት መንገድ የተዛባ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱን ያለመቀበል (አንዳንዶቹ እንደውም ቀዶ መጣል ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው) ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ ያንን ሁሉ ማሸነፍ ችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ደግሞ ትልቁ አስተዋፅኦ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ በበርካቶቹ ዘንድ የተለመደው መፈክር ነበር፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮት ዓለም፤ የፖለቲካ ፍልስፍና አልነበራቸውም፡፡ የፖለቲካ ፍልስፍናን በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ አስተዋውቀናል፡፡ ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም፤ ቀላል የማይባሉ ሰነዶችን አዘጋጅተናል፡፡
የፓርቲውን ፕሮግራም፣ በብሄራዊ እርቅ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ—ወዘተ አምስት ጥራዝ ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡ ከዚያም በተከታታይ ሰፊ ሰነድ አዘጋጅቷል ኢዴፓ፡፡ ቀደም ሲል ትግሉን የሚመሩት አስተሳሰቦች ሳይሆኑ መፈክሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ርዕዮት አለም ሰነዶች አሏቸው፡፡ ሌላው ኢዴፓ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያስተዋወቀው ለምርጫ ክብር መስጠትን ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ምርጫ ብቸኛው የስልጣን ማግኛ መንገድ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ በተቃዋሚው ዘንድ እንዲሰርፅ አድርገናል፡፡ ለምርጫ የሚመጣ ማንኛውም ኃይልም አማራጭ ሃሳብ ይዞ እንዲመጣ (ማኔፌስቶ እንዲያዘጋጅ) አነቃቅተናል፡፡ የመጀመሪያ የማኔፌስቶ ባለቤት ኢዴፓ ነው፡፡ ለቅንጅትም ማኔፌስቶ ያበረከትነው እኛ ነን። ፈፅሞ የተዘነጋውና ትርጉም የለውም ተብሎ ይቆጠር የነበረውን የባህር በር ጥያቄ ዛሬ የሁሉም ፓርቲዎች መፈክር ማድረግ ችለናል፡፡ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ፒቲሽን አስፈርመን ለተባበሩት መንግስታት አቅርበናል፡፡ ውጤቱ ምንድን ነው ብለሽ እንዳትጠይቂኝ፡፡
ከ1997 ዓ.ም የምርጫ ጊዜ በኋላም ትግሉ አደጋ ደርሶበት በነበረበት ጊዜ ማህበረሰቡ ቆም ብሎ ጉዳዩን እንዲያጤን፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያት እንዲታገል ሶስተኛው አማራጭን እንደ ሀሳብ ፓርቲው ይዞ መጥቷል፡፡ እነዚህ የጠቀስኩልሽ ነገሮች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የእኔ አሻራ አለባቸው፡፡
-ቀጣዩ ምርጫ በ97 ዓ.ም. ከነበረው ምርጫ ጋር ሲነፃፀር ሊሰጠው የሚገባውን ግምት ሊገልጹት ይችላሉ?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
በአሁኑ ጊዜ ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የሚይዙ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ኢህአዴግን ግን ሊገዳደሩት ይችላሉ። በርከት ያለ ቁጥር አግኝተው ተወካዮች ምክር ቤት የመግባት እድል ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በተጨባጭ መንግስት ለመሆን የሚያስችል ቁመና አልፈጠሩም፡፡ ግልፅ ነው፤በቂ ህዝብ በደጋፊነት ማሰለፍ አልቻሉም፡፡ ኢህአዴግም ብዙዎች እንደሚያወሩት ዝም ብሎ ለጥቅማቸው፣ ለሆዳቸው፣ ለጊዜያዊ ፍላጎታቸው ያደሩ ሰዎች የተሰበሰቡበት አይደለም፡፡ እንደ ድርጅት በእምነት የሚከተሉት ቀላል የማይባል አባላቶች አሉት። የሚደረገው ውድድር ዝም ብሎ በአየር ላይ ካለ ድርጅት ጋር አይደለም፡፡ ውድድሩ በደንብ በህዝቡ ውስጥ መደላደል ይዞ ከሚንቀሳቀስ ድርጅት ጋር ነው። በፋይናንስ፣ በሰው ሃይል አቅም… መንግስት በመሆኑ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ አኳያ በቀላሉ ልታሸንፊው የምትችይው ፓርቲ አይደለም፡፡
ከዚህ አኳያ ተቃዋሚዎችን ስታይ ደግሞ በተቃራኒው ነው፡፡ በሰው ሃይል ሲታዩ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ አመራሮች የሚታዩበት እውነታ ነው ያለው፡፡ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ጊዜ በቅለው ሲጎለብቱና ሲጠነክሩ አናይም፡፡ ሁሌም የተለመዱ ፊቶች፣ ሰዎች፣ አመራሮችን ናቸው ያሉት፡፡ ከአንዱ ፓርቲ ወደ አንዱ ፓርቲ ሲሄዱ ነው የምናው፡፡ ይሄ አንደኛው የድክመታቸው መገለጫ ነው፡፡ በአብዛኛው ከተማ ተከል ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞቹ ውጭ ገጠር ሄደው አርሶ አደሩን በቅጡ መድረስ የቻሉ አይደሉም፡፡ ለዚህ ምክንያት ሊደረደር ይችላል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ በገጠር የሚኖር እንጂ በከተማ የሚኖረው 15 ፐርሰንቱ ነው። አጠቃላይ የከተማው 15 ፐርሰንቱ ቢደግፋቸውም እንኳን በምርጫ ሊያመጡት የሚችሉት ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሃይሎች ለዚህ ያበቃቸው መሰረታዊ ምክንያት በ1997 ዓ.ም. የተፈጠረባቸው ችግር ነው ከተባለ— አዎ። በርግጥ ብቸኛው ምክንያት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፈጣጠራቸው ችግር አለባቸው፡፡ በውስጣቸው ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በደንብ ሰርጽዋል ብዬ አላምንም፡፡ በምርጫ ሲወርዱና ሰዎች ሲተኩ አናይም፡፡ በውስጣቸው ዲሞክራሲ ያላበበ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለህዝብ ዲሞክራሲ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ብሎ የሚያምናቸው የለም፡፡ ከባህሪም አኳያ ስታይው እየተካሄደ ያለው ትግል የአስተሳሰብ የበላይነትን ከመፍጠር ይልቅ የአርበኝነት መንፈስ ያየለበት ነው፡፡ የምናየው ኢህአዴግን ለመጣል የሚደረግ ትግል እንጂ አስተሳሰብን በህዝቡ ውስጥ አስርጾ መንግስት ለመሆን የሚያስችል አቅም ወይንም አቋም አይደለም፡፡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ኢህአዴግ እንዲወድቅ መመኘት ብቻ ነው፡፡ በርዕዮት ዓለም አለምም ደረጃ ጠንከር ጠብሰቅ ብለው የሚሰሩ ነገሮች አይታዩም፡፡ እነዚህ እነዚህ ሁሉ ከመነሻቸው ድክመቶቻቸው ናቸው፡፡
-በ1997 ዓ.ም. የተፈጠረው ችግር ደግሞ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ የነበራቸውን እምነት እንዲያጡ አድርጓል፡፡ መከፋፈሉ፣ የተፈጠረውን እድል መጠቀም አለመቻላቸው፣ በኋላም ከእስር ቤት ወጥተው ራሳቸውን አጎልብተው በብቃት አለመራመዳቸው —- ህዝብ የነበረውን እምነት ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት የኢህአዴግ አስተዋጽኦ ምንድነው?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
 የኢህአዴግን ችግርን ማየት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግን እንደ ድርጅት ሳየው አንድ የተለየ ተልዕኮ ይዞ እንደመጣ ተዓምር አድርጐ ነው ራሱን የሚያስበው፡፡ ይሄንን የሚደግፈው ደግሞ ሰማዕታትንና የተከፈለውን መስዋዕትነት በመጥቀስ ስለሆነ፣ የአስተሳሰብ የበላይነትን ለመቀበል የተዘጋጀ ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ ለረጅም ዘመን በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ማንኛውም ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ቀድሞ ግብ አስቀምጦ፣ ከግቤ ከመድረሴ በፊት ማንኛውንም ሃይል መታገስ አልችልም ብሎ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ምርጫ ማድረግ ብቻውን ግን አንድን አገር ዲሞክራሲያዊ አያስብላትም፡፡ የምርጫ ውጤትም ትርጉም አለው፡፡
መንግስት በተቃውሞ ትግል ውስጥ ያለው ሚና መንግስት እንደ ኢህአዴግ፤ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ማየት ይቻላል፡፡ መንግስት ብዙ ጊዜ መንግስትነቱና ኢህአዴግነቱ ይምታታበታል፡፡ የዚህ ስርዓት ፈጣሪም ባለቤትም ስለሆነ፣ ይሄ ስርዓት በሌላ አስተሳሰብ ተፈትሾ፣ ከስልጣን ወርዶ ስለማያውቅ ስርዓቱንና ኢህአዴግን መንካት አንድ ሆነዋል፡፡ ስርዓቱን ስትታገይ ኢህአዴግን መታገል ነው፤ ኢህአዴግን ስትታገይ ስርዓቱን መታገል ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች እየተፈራረቁ በመጡበት ሁኔታ መቼም ቢሆን የአስተሳሰብ ለውጥ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰርፅ አያደርግም፡፡ የኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪዎች ትግሉን ውስብስብ፣ በጣም አድካሚና እልህ አስጨራሽ አድርገውታል፡፡
-ስለ ህዝቡስ አስተያየትዎ ምንድነው?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
ህዝቡም ጋር ስትመጪ ቀላል የማይባል ችግር አይደለም ያለው፡፡ ህብረተሰቡ ለፖለቲካ ያለው ዝንባሌ በፍርሃትና በስጋት የተሞላ ነው፡፡ የትግሉ ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ ከተቃዋሚዎች የሚቀርብበት ወቀሳ ሊኖር ይችላል፡፡ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊናና ለመረጃ ያለ ቅርበት በራሱ ችግር ነው፡፡ ትግሉ በእነዚህ መንገዶች በማይታገዝበት ሁኔታ የተቃዋሚዎች ሚና ደካማ መሆኑ አይቀርም፡፡ ተቃዋሚዎች ተጨባጭ ሁኔታው የማይፈቅድላቸው ነገር አለ፡፡ ስራውን ለመስራት የሚያስችል በቂ ምህዳር የለም፡፡ ከኢህአዴግ በኩል ያለው ተፅዕኖ በጣም ከባድ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥም ራስን የትግሉ ባለቤት አድርጎ የሚገኘውን ጥቅም ለመጋራት በቂ ተነሳሽነት አታይም፡፡
-የተቃዎሚ ፓርቲዎች ወዲያው ተዋህደው ወዲያው መከፋፈል፤ እርስ በርስ መወነጃጀል… ህብረተሰቡን ተስፋ አያስቆርጠውም ይላሉ?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
በፖለቲካ አስተሳሰብ ዙሪያ ካልተሰባሰብሽ ጥላቻ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥላቻ ሊወስድ የሚችለው መንገድ አለ፡፡ ኢህአዴግን መጥላት ብቻ በራሱ በቂ ርቀት ሊወስድ አይችልም፡፡ ፍልስፍና ሆኖ፣ የሰው ልብ ገዝቶ ትግልን ሊያጎለብትና ሊያጠነክር አይችልም፡፡ የመቻቻል፣ እውቅና የመስጠት፣ የተሞክሮ አለመኖር፣ የድርጅታዊ ብቃት ማነስ፣ የስልጣን ጥም—- እነዚህ ሁሉ የሚጫወቱት ሚና አለ፡፡ ከፖለቲካ ፍልስፍናው ውጪ፡፡ በአስተሳሰብ ዙሪያ ስትሰባሰቢ እምነትሽ አስተሳሰብ ይሆናል፡፡ ማንም ያንን አስተሳሰብ ቢያራምደው የአስተሳሰብ ባለቤት እስከሆንሽ ድረስ ችግር አይኖርብሽም፡፡ ሲጀመር የጠራ አስተሳሰብ አይደለም ያለው፡፡ ሁሉም የራሱን አስተሳሰብና እምነት በበላይነት ማራመድ ስለሚፈልግ ሽኩቻው የማያቋርጥ ነው የሚሆነው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ ጥሩና ጠንካራ የምለው አስተሳሰባችን የጠራ መሆኑ ነው፡፡ እኛ ግለሰብ ላይ ሳይሆን በአስተሳሰባችን ላይ ነው የምናተኩረው። ቦታው ላይ በተቀመጠው ሰው ችግር የለብንም፡፡ በፓርቲ ውስጥ ክፍፍል የሚያመጡት እነዚህ ናቸው፡፡ በውስጣቸው በርካታ ችግር አለ፡፡ ፖለቲካ በትምህርት የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ በተግባር፣ በተሳትፎ ነው ፖለቲካን ማጠናከርና ማዳበር የሚቻለው። ድርጅት የሚጠነክረውና የሚጎለብተው በተሳትፎ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ሰዎች ስለተሰበሰቡ አይደለም ፓርቲ ጠንካራ የሚሆነው። ፓርቲ በሂደት ነው ሙሉ የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ፣ የተቃውሞ ፖለቲካ ዕድሜው እና ተመክሮው አጭር ነው፡፡ የሚፎካከሩት ድርጅት ደግሞ ያለው ተሞክሮ ቀላል አይደለም፤ የስርዓቱ ባለቤትና ፈጣሪውም ነው፡፡ ስለዚህ ለተቃዋሚዎች ፈተና ነው፡
-በቀጣዩ ምርጫ እንደ ተቃዋሚ ወይንም እንደተፎካካሪ ኢህአዴግን ሊገዳደረው የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብለው ያስባሉ?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
 እኔ ኢዴፓ ነው፣ ነው የምለው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ ስላለሁ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የምርጫ ስርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ካደረገው፣ የሚዲያ ተጠቃሚነትን ከፈጠረ፣ ሃሳቦች በደንብ እንዲንሸራሸሩ ሁኔታዎችን ካመቻቸ፣ ሰዎችን ማፈናቀሉን ካቆመ፣ ኢህአዴግን በአስተሳስብ በመገዳደር ብቁ ነው ብዬ የማስበው ድርጅት ኢዴፓ ነው፡፡ የጠራ የጠነከረ አስተሳሰብና አመለካከት ያለው ኢዴፓ ነው፡፡
-በቅርቡ የተከሰሱ የግል የፕሬስ ውጤቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኞችም ሃገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ መጪው ምርጫ ነው—-
አቶ ሙሼ ሰሙ-
ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ለመጀመሪያዎቹ ሶስትና አራት አመታት በህዝቡ ዘንድ ኢህአዴግ ታማኝነት የነበረው ድርጅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በህዝብ ላይ ያለው እምነት ሁልጊዜ በጥያቄ የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አማራጭ ሃሳቦች አንዲጎለብቱና እንዲዳብሩ አይፈልግም፡፡ እናም ማድረግ የሚችለው መረጃዎች ወደ ህዝብ የሚደርሱበትን ድልድዩን ማጥፋት ነው፡፡ የግል ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ላይ የሚደርስባቸው ቅጥቀጣ እነሱ የተለየ አስፈሪ ስለሆኑ አይደለም፡፡ በማህበረሰቡና በአስተሳሰቡ መሃል ድልድይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እነሱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ድልድዩን ለመስበር ነው፡፡ ህዝብ ባወቀ በነቃ በተደራጀ ቁጥር እንደሚፈታተነው ያውቃል። ህዝቡን ያወናብዱብኛል፣ ህዝቡን ያሳስቱብኛል፣ እኔ ከምፈልገው መንገድ ያስወጡብኛል የሚል ስጋት አለው። ስለዚህ የህዝብ ልሳን፣ አንደበት ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ያዳክማል፡፡
አሁን በቅርቡ መጽሄቶች ላይ የደረሰው ነገር ለእኔ ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ አለማቀፍ ተጽዕኖውን አይፈልግም፤ ምክንያቱም ተበዳሪ መንግስት ነው፡፡ በተለያዩ መልኩ የሚደርሱበትን ተፅዕኖዎች ከወዲሁ ለመቋቋም እቅድ አድርጎ ኢህአዴግ የወሰደው የሚመስለኝ፣ የክስ ቻርጁን በግላቸው ከመስጠትና ከማሰር በፊት በቴሌቪዥን እንደ ቀይ ሽብር ማወጅ ነው፤ እናም ተነስተው ይጠፉለታል፡፡ ከዚያ ተገላገልኩ ነው የሚለው፡፡ ሙከራው በከፊል ተሳክቷል፡፡ ጋዜጠኞቹ ጥለው እየሄዱ ነው፡፡ በአዋጅ መልክ ክስ ከቀረ 23 ዓመቱ ነው፡፡ ደርግ ነበር ይሄን ያደርግ የነበረው፡፡ እነዚህ መጽሔቶች በብዙ አቅጣጫ ከፋይናንስ፣ ከአደረጃጀት፣ ከሰው ሃይል አኳያ ቀላል የማይባል ጉልበት የፈጠሩ ናቸው፡፡ ባለፈው አምስት ዓመት እንዴት ህትመታቸው፣ ስርጭታቸው፣ እንደሚጎለብትና እንደሚጠነክር ያውቃል። እነዚህን ማዳከም ነው የያዘው፡፡ በእነሱ ምትክ አዲስ ጋዜጣ ያስገባል፤ አቅማቸው ደካማ ነው፣ እየተቆራረጡም እየተንጠባጠቡም ነው የሚቀጥሉት፡፡ በበቂ ደረጃም ህዝቡን አይደርሱም፤ ይቆማሉ፡፡ ስለዚህ ቀጣይነት፣ ወጥነት፣ ተከታታይነት ባለው መንገድ የሚታገሉትን መጽሔቶች ነው እንዲሰደዱ ወይም ፍርድ ቤት እንዲቆሙ ያደረገው፡፡ ይሄ ምርጫው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከመፈለግ ውጭ አይደለም፡፡ ሰው ይወናበዳል፣ ተወናብዶ እኔን አይመርጠኝም፤ የሚል ስጋትና ጥርጣሬ ስላለው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ኢህአዴግ ከእሱ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ማንኛውም ሃሳብን ለማራመድ የሚያገለግል መሳሪያ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ እንደ እኔ አስቡ፣ እንደ እኔ ገምቱ የሚለው ደግሞ አያስኬድም፡፡
-በዓለም ላይ የየሀገሩ ስጋት ተብለው የሚጠቀሱ የሀይማኖት፣ የዘር፣ የአምባገነናዊ ስርዓቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ስጋት የትኛው ነው?
አቶ ሙሼ ሰሙ-
ሰዎች በተፈጥሮዋቸው አማራጭ ይፈልጋሉ፤ መፈለግ ብቻ ሳሆን አማራጭንም መፈተሽ ይሻሉ፡፡ አንድ መንግስት ለረዥም ጊዜ እንዲገዛቸው ፈቃደኛ አይደሉም፤ ይሰለቻሉ፡፡ ሰው ስሜቱን፣ ሃሳቡን፣ ፍላጎቱን እንዲያወጣ፣ እንዲገልጽ የሚያደርጉት ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በተዳከሙ ቁጥር በሰው ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ እንዴት ይቻላል? ይሄ ደግሞ ወደ አመጽ፣ ወደ አለመረጋጋት ለመለወጥ የማንንም ይሁንታ አይጠብቅም፡፡ በደህንነትና በስለላ መዋቅር የሚቆም አይደለም፤ እንደ ጋዜጦችና እንደ ፓርቲዎች፡፡ ፓርቲዎችን አመራሮችን ሰብስቦ አስሮ፣ ትግሉን ማዳከም ይቻላል፡፡ በህዝብ ውስጥ ያለ ቁጣና ብስጭትን ግን መቆጣጣር አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች የዚያ ውጤት ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ችግር ይገጥማታል ብዬ አላስብም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ግን ስርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ስርዓቱ በዚህ መንገድ ያሉትንም እድሎች እያጠበበ፣ እየጨፈለቀ በሄደ ቁጥር ሰዎች በውስጣቸው የሚቀጣጠለው ነገር የበለጠ እየጠነከረ እየጎለበተ ነው የሚሄደው፡፡ ጥያቄያቸው እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ የተገኘውን እድል ተጠቅመው ፍላጎታቸውን ለማራመድ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይህችን አገር ወደ መልካም አስተዳደርና ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለመውሰድ ከተፈለገ፣ ተጨባጭ ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ አሳታፊ የሆነ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ግዴታ ነው፡፡
ግብጽን ብናይ እስከ አሁን ድረስ መውጣት ባልቻለችበት የፖለቲካ ቀውስ እየታመሰች ነው ያለችው። ቀደም ብሎ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብጽ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው፤ ትክክለኛ ቦታቸውን አግኝተው፣ ሃሳባቸውን ለመግለፅና ለማራመድ በሩ ክፍት ቢሆን ኖሮ፣ በአመጽና በህዝብ ቁጣ ሳይሆን በተቃዎሚ ፓርቲ ሃይሎች የስልጣን ሽግግር ሀገሪቱ ቀጣይነትዋን ታረጋግጥ ነበር፡፡ ህዝቡ ስሜቱን የገለጸው በምርጫ አይደለም፤ በአመጽ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖራቸው ጥቅሙ ህዝብ ፍላጎቱን በምርጫ እንዲገልፅ እድል ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ለእኔ የሚታየኝ ስጋት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መንገድ አልተሰራም፤ ልማት አልተካሄደም እያልኩሽ አይደለም፡፡ ስራ አጥነትን ለመቀነስ እንቅስቃሴ የለም፣ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን በዚህች አገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ የተነሳ፣ የእኔ አማራጭ ነው የሚሻለው የሚልም አለ፡፡ ይሄ ሰው ሃሳቡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተደምጦ፣ በምርጫ ተሸንፎ ካልሆነ፣ በጉልበት በማፈን እንዳይራመድ ከተደረገ መጨረሻ ላይ ህዝቡ ውስጥ የሚፈነዳው ሌላ ነገር ነው፡፡

Source: Addis Admas

No comments:

Post a Comment