Wednesday, July 23, 2014

የትግል ጥሪ በውጭ ለመትኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ

July22/2014

የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ የአፈና ቀንበር ስር ከወደቀ አንስቶ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በማህበራዊ ሕይወቱ እጅግ ወደከፋ አቅጣጫ እያመራ ይገኛል በተለይም የመንደር ፖለቲካው በኢትዮጵያዊያን መካከል ለመፍጠር እየተሞከረ ያለው ልዩነት ስርዓቱ እንዳሰበውና እንደሚፈልገው ገቢር አይሁን እንጂ አገዛዙ የለኮሰውን የጥፋት እሳት በአፋጣኝ ተረባርበን ካላጠፋነው ለወደፊት በኢትዮጵያዊነት ስሜት እና መንፈስ ላይ አደጋ የሚፈጥር ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር አምባገነኑንና ጎጠኛዉን የወያኔ አገዛዝ ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋአትነት ከፍሏል። ድርጅታችን ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ጥቅም ሲል ዳገት ቁልቁለቱን፣ ረሃብና ጥሙን፣ ውርጭ ቸነፈሩን የኔ ብሎ በመቀበል አጥንቱን በመከስከስ ደሙን በማፍሰስና መተኪያ የሌላት ውድ ህይወቱን በመክፈል ለአገሩና ለሕዝቡ ያለዉን ጥልቅ ፍቅር በተግባር አስመስክሯል ።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለለውጥ ትግሉ በሰላማዊ ሰልፍ ፣ በሻማ ማብራት፣ የወያኔን ድብቅ አጀንዳ የተለያዩ መንግስታት እንዲያውቁት በማድረግ፣ በማማከር፣በገንዘብ ወ.ዘ.ተ ድጋፍ በማድረግ ቀላል የማይባል ሚና ተወጥተዋል ።
ይህ የተቀደሰ የአርበኝነት ትግል በተደራጀ እና ወጥነት ባለው መልኩ እንዲከናወን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በአቶ የዋርካው መንግስቱ የሚመራ የዓለም አቀፍ ኮሚቴ በጊዜያዊነት መቋቋሙን እያስታወቅን ኮሚቴው ግንኙነቱና አጠቃላይ የውጭ እንቅስቃሴዎቹ ከግንባሩ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ አርበኛ ኑርጀባ አሰፋ እውቅናና ምክክር ይሆናል ከዚህ አሰራር ውጭ የሚደረግ ማንኛውንም አይነት የውጭ እንቅስቃሴ ግን ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጥብቀን እናሳስባለን። 
በተቋቋመው የዓለም አቀፍ ኮሚቴ ስር በመደራጀት መላው ዲያስፖራ የየበኩሉን ድርሻ በመወጣት ለስደት የዳረገውን የወያኔ አገዛዝ ለመታገል ነገ ሳይሆን ዛሬ ሊነሳ ይገባል።
አንድነት ሃይል ነው !
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር
ሐምሌ 14-2006 ዓ/ም

No comments:

Post a Comment