Sunday, July 13, 2014

እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ!

July13/2014

አንድን ሰዉ ጀግና የሚያሰኙ ብዙ መለኪያዎች አሉ፤ የእነዚህ መመዘኛዎች ስፋትና ጥልቀት ደግሞ እንደያገሩ ባህልና ወግ ይለያያል። የጀግንነት ትልቁ መለኪያ ጦር ሜዳ ዘምቶ ጠላትን ቁጭ ብድግ እያሰኙ መቅጣት ነዉ ብለዉ በሚያምኑ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገሮች ዉስጥ “ ጀግንነት” የሚለዉን ጽንሰ ሀሳብ ጽንሰ ሀሳቡ በሚነካካዉ ሁሉም መልኩ መግለጽ አስቸጋሪ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ ግን በዬትኛዉም አገርና ባህል አንድን ሰዉ ጀግና ሊያሰኙ የሚችሉ መስፈርቶችን በሙሉ ከወጣትነት ዘመኑ ጀምሮ ያሟላ ሙሉ ህይወቱን ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ አሳልፎ የሰጠ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነዉ። አገርህን አድን እያልንም ሆነ ወይም በርዕዮተአለም እየቀሰቀስን እልፍ አዕላፋትን ወደ ጦር ሜዳ ማዝመት ተችሏል፤ ለወደፊትም ይቻላል። ግን ይህ ስራ በራሱ ብዙም ጀግንነት የሚጠይቅ ስራ አይደለም። ለጦርነት ከቀሰቀስናችዉ ሰዎች ጎን ተሰልፈን ጦር ሜዳ ድረስ መዝመት ግን እሱ አሱ ወደር የለሽ ጀግንነት ነዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ የነጻነትና የፍትህ አርበኞችን ያፈራ ብቻ ሳይሆን እሱ እራሱ አንደ አንድ አርበኛ ዉግያዉ ወረዳ ድረስ ሄዶ አብሯቸዉ ሊዋደቅ የተዘጋጀ ቆራጥ ሰዉ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ ፍትህ በሌለባቸዉ ቦታዎች መኖርን የሚጸየፍ ፍትህን የቀመሙትን ሰዎች ወይም ተቋሞች ደግሞ ባሉበት ቦታ ሁሉ በጽናት የሚታገል አሁንም የፍትህና የነጻነት ጠላቶች በመታገል ላይ እንዳለ በየመን ከሀዲዎች አዉሮፕላን ጣቢያ ዉስጥ ታግቶ ለወያኔ ዘረኞች ተላልፎ የተሰጠ ዘመን ስራዉን የማያደበዝዘዉ ጀግናና የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጅ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ ጽጌ ዕድሜዉ ከሃያ አመት በታች ከነበረበት ግዜ አንስቶ የፊዉዳሉን ስርዐት፤ የደርግን ስርዐት ዛሬ ደግሞ የዘረኞችን ስርዐት የተቃወመ ብቻ ሳይሆን የተፋለመ እዉነተኛ ጀግና ነዉ። አብረዉት ትግል የጀመሩ ግለሰቦች የራሳቸዉ ህይወት ከህዝብ አደራ በልጦባቸዉ ከትግል አለም ሲለዩ፤ አንዳንዶች በቃን ደከመን ብለዉ ወኔ ሲከዳቸዉ ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለስልጣንና ግዜያዊ ጥቅም ሚኒልክ ቤ/መንግስትን ከተቆጣጠረ ሁሉ ጋር ቤተኛ ሲሆኑ አንዳርጋቸዉ ግን በአካሉም በመንፈሱም ያልተሸነፈ፤ ለገንዘብም ለስልጣንም ሲል ህሊናዉን ያልሸጠ ህዝብና አገር የሰጡትን የፍትህና የነጻነት አደራ እንደተሸከመ ከአርባ አመታት በላይ ጸንቶ የቆመ እዉነተኛ የነጻነት አርበኛ ነዉ። እንዳርጋቸዉ ጀግና ብቻ ሳይሆን በዘመናት ዉስጥ አንዴ ብቅ ብለዉ ሰማይን በብርሃን አድምቀዉ አንደሚሰወሩ ሰማያዊ አካላት ወይም ከዋክብት ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያዉያን በድፍረት የነጻነት ችቦ የለኮሰ የህዝብ ባለአደራ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት የሆኑት የወያኔ ዘረኞችም ይህንን የህዝብ ልጅ አፍሪካ አዉሮፓና መካከለኛዉ ምስራቅ ዉስጥ በየሄደበት የተከታተሉትና በመጨረሻም እነሱን በመሳሰሉ ከሀዲ መንግስታት አማካይነት እንዲያዝ ያደረጉት አንዳርጋቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የለኮሰዉ የፍትህና የነጻነት ችቦ እንደሚያጋልጣቸዉ ብቻ ሳይሆን ጠራርጎ እንደሚያጠፋቸዉም ስለሚያዉቁ ነዉ።
አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ “እባብን መመታት ጭንቅላቱን ነዉ” የሚባል የቆየ አባባል አለ። በእርግጥም እባብን ለመግደል ከጭንቅላቱ የበለጠ ጉዳት የሚያደርስበት ሌላ ቦታ የለም። ሆኖም እዚህ ላይ አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ፤ እሱም እባብን ጭንቅላቱን መትተን ስንገድለዉ የሚሞተዉ አንድ እባብ ብቻ ነዉ፤ ብዙ እባቦች በህይወት ይኖራሉ፤ አዳደሶች ደግሞ ይወለዳሉ። ጅሎቹ የወያኔ ዘረኞች “እባብን መምታት” በሚለዉ ተረት ተሞኝተዉ አንዳርጋቸዉን ይዘዉ በማሰቃየት ወይም በመግደል ህዝባዊ ትግሉን አኮላሽተነዋል ብለዉ አስበዉ ከሆነ እጅግ በጣም ተሳስተዋል። የወያኔ ዘረኞች አንዳርጋቸዉን አሰሩ አላሰሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱን መታገሉን የሚያቆመዉ መብቱን፤ ነጻነቱንና የአገሩን አንድነት ለሱ ለራሱ ዉሳኔ ሲተዉለት ብቻ ነዉ። የሰዉ ልጅ እባብን መቀጥቀጡን የሚያቆመዉ እባብ መናደፉን ሲያቆም ብቻ ነዉ፤ የወያኔም ነገር እንደዚሁ ነዉ፤ ዘረኝነቱን፤ መብት ረጋጭነቱንና የአገር ድንበር መሸርሸሩን እስካላቆመ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ይታገለዋል ፤ መታገል ብቻ ሳይሆን የሚገባዉን ቅጣት ይሰጠዋል።
የወያኔ ዘረኞች እነሱ በእራሳቸዉ ሞክረዉ ሞክረዉ ያቃታቸዉን ነገር በዉንብድናና በክህደት እነሱን ከሚመስል የሌላ አገር መንግስት ጋር በመተባበር አንዳርጋቸዉ በህገወጥ መንገድ ታግቶ በህገወጥ መንገድ እጃቸዉ ዉስጥ እንዲገባ በማድረግ ለግዜዉም ቢሆን አንዳርጋቸዉን ከትግሉ ሜዳና ከትግል ጓደኞቹ ነጥለዉት ይሆናል፤ ሆኖም ግን የአንዳርጋቸዉ መታሰር በተሰማበት በአጭር ግዜ ዉስጥ ኢትዮጵያ ዉስጥና ከኢትዮጵያ ዉጭ እልፍ አዕላፋት ጀግኖች በቅጽበት ተፈጥረዉ አንዳርጋቸዉ ያበራዉን ችቦ አንግበዉ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያሉ ትግሉን ተቀላቅለዋል።
ወያኔና የመን በመመሳጠር በጋራ አስረዉ የሚያሰቃዩት አንዳርጋቸዉ ጽጌ ሰነዓ ላይ ሲታሰርና ለወያኔ ተላልፎ ሲሰጥ አንድ ብቻዉን ነበር። ዛሬ ግን በየመኖች መታገቱና ለወያኔ ተላልፎ መሰጠቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮ በገባ ሳምንት በማይሞላዉ ግዜ አንድ ብቻዉን የታሰረዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ብለዉ እስከ መጨረሻዉ ወያንን ለመፋለም የቆረጡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቆራጥ ኢትዮጵያዉያንን ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል። ዛሬ ከዉጭዉ አለም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባዉና ከኢትዮጵያ ወደ ዉጪዉ አለም የሚወጣዉ ድምጽ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” የሚል የትግል ጥሪ ድምጽ ነዉ።
አንዳርጋቸዉን በህገወጥ መንገድ አግተዉ ለወያኔ ያሰረከቡት የመኖችም ሆኑ ዘረኞቹ የወያኔ ባለስልጣኖች አንዳርጋቸዉ ዬት አንዳለ አናዉቅም ብለዉ አይክዱ ክህደት ክደዉ ነበር፤ ሆኖም አዉነትን ደብቀዉ ማቆየት እንደማይችሉ ስለተረዱ አንዳርጋቸዉን ለሁለት ሳምንታት ያክል ሲቀጠቅጡ ከቆዩ በኋላ ባለፈዉ ማክሰኞ አንዳርጋቸዉ እጃቸዉ ላይ እንደሚገኝ አምነዋል። በጥላቻ ተወልደዉ በጥላቻ ያደጉት የወያኔ መሪዎች አንዳርጋቸዉ ጽጌን የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባል ስለሆነ ብቻ አይደለም እንደዚህ አክርረዉ የሚጠሉት። አንዳርጋቸዉ ለነጻነቱና ለእናት አገሩ ደር ድንበር መከበር አጥብቆ የሚሞግትና ሌሎችም እንደሱ ለነጻነታቸዉና ለአገራቸዉ አንድነት እንዲሟገቱ የሚገፋፋ የመብት፤ የነጻነትና የአገር አንድነት ጠበቃ ነዉ። ለዚህ ነዉ ይህንን የአገር አለኝታ የሆነ ሰዉ እስክ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ድረስ የሚሆን ገንዘብ ለየመኖች ሰጥተዉ ታግቶ እንዲሰጣቸዉ ያደረጉት።
የወያኔ ዘረኞች ይህንን አገርና የወገን አለኝታ የሆነ ሰዉ አስረዉ የሰዉ ልጅ አይቶትም ሰምቶትም የማያዉቀዉን ሰቆቃ ሁሉ እንደሚያወርዱበት ጥርጥር የለንም።አንዳርጋቸዉ ጽጌ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብት፤ ነጻነትና የግዛት አንድነት መከበር ህይወቴ ታልፋለች ብሎ በአንድ ህይወቱ የተወራረደ ሰዉ ነዉ፡ እንደተናገረዉም ቃሉንም ያከበረ ሰዉ ነዉ። የወያኔ ዘረኞች ይህንን ጀግና ሰዉ ባሰቃዩና የስቃይ ድራማቸዉን በዚያ እንደ ቤት ዉስጥ ዕቃችዉ በሚቆጣጠሩት ቴሌቪዥን ላይ ባሳዩን ቁጥር ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር በቁጣና በእልህ ተነሳስተን “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያልን ትግሉን መቀላቀል ነዉ እንጂ አንገታችንን ደፍተን እነዚህ ዘረኞች እንድንሆንላቸዉ የሚፈልጉትን መሆን የለብንም።ህዝባዊ ትግሉ አምርሯል፤ ትንቅንቁ ተጀምሯል። ጎንበስ ቀና እያለ እንደ ህፃን ልጅ በእንብርክኩ ይጓዝ የነበረዉ የቱኒዝያ አብዮት በሁለት እግሩ ቆሞ እንዲሄድ መሐመድ ቦአዚዝ እራሱን መስዋዕት አድርጎ ማቅርብ ነበረበት። አይነካም አይሞከርም ሲባል የነበረዉን ሞባረክን በ15 ቀናት ከስልጣን አባርሮ ለፍርድ ያቀረበዉ የግብጹ አብዮት ከዳር ዳር እንዲቀጣጠል የሃያ ስምንት አመቱ ወጣት ከሊል መሐመድ ሰይድ መሞት ብቻ ሳይሆን አንደ ክትፎ መከታተፍ ነበረበት።
ኢትዮጵያን የሚጠብቅ አይተኛምና ለእኛም እንደ ሙሴ መርቶ ወደ ተስፋዉ አገር እንዲያደርሰን አንዳርጋቸዉ ጽጌን አድሎናል። አንዳርጋቸዉ ልክ እንደ ሙሴ የታገለለትን ማየት አይችል ይሆናል- እሱ የታገለለት አላማ ግን ምንም ጥርጥር የለንም ግቡን ይመታል። አንዳርጋቸዉ ከአርባ አመታት በላይ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለእኩልነት የታገለዉ አልበቃ ብሎት እራሱን መስዋዕት አድርጎ አቅርቦልናል፤ በዚህ ጀግና ሰዉ መስዋዕትነት የማይቀሰቀስና ትግሉን በቀጥታ የማይቀላቀል ኢትዮጵያዊ ካለ እሱ ከክብር ዉርደትን፤ ከነጻነት ዉርደትን የሚወድ ደሙ ከደማችን ያልተቀላቀለ ሰዉ መሆን አለበት። እኔ አንዳርጋቸዉ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ፤ አገሩን ኢትዮጵያን የሚወድ ኢትዮጵያዊ፤ ጉልበትና አቅም ያለዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህንን አንዳርጋቸዉ የጀመረዉን ትገል ነገ ሳይሆን ዛሬዉኑ መቀላቀል አገራዊ ግዴታዉ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ ጽጌ ወያኔን መቃወም ብቻ ሳይሆን ከመቃወም አልፎ የወያኔን ሰርዐት ለማሰወገድ ዱርቤቴ ብሎ በአይን የሚታይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረና የጀመረዉን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወያኔን ፊት ለፊት ተፋልሞ ማስወገድ በሚችልበት አስተማማኝ ቦታ ላይ ያደረሰ ቆራጥና ደከመኝን የማያዉቅ ጀግና ነዉ።ለዚህ ነዉ የአንዳርጋቸዉ እንቅስቃሴ እንቅልፍ የነሳዉ ወያኔ በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመንግስታት ደረጃ ተመሳጥሮ ይህንን ጀግና ሰዉ በህገ ወጥ መንገድ በዉንብድና የያዘዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ ደብዝዞ የነበረዉን ህዝባዊ ትግል ህይወት የዘራበት እሱ አራሱ ግን አንደ ሻማ የቀለጠ እኛ ኢትዮጵያዉያን እንደ ቱኒዝያዉ ቦዚኦዚዝና እንደ ግብጹ ከሊድ ልንመለከተዉ የሚገባን የትግላችን አቀጣጣይ ችቦ የሆነ ሰዉ ነዉ። ዛሬ አንዳርጋቸዉ የሚፈልገዉና የሚመኘዉ በመታሰሩ ከንፈራችንን እየመጠጥን እንድንዘናጋና ሀሞታችን እንዲፈስ አይደለም። ይልቁንም የሱ ምኞትና ፍላጎት በሱ መታሰርና ስቃይ የእኛ ክንድ እንዲበረታና ሞራላችን እናሸንፋለን በሚል ጥርጥር የለሌለዉ ጽኑ ፍላጎት እንዲገነባ ነዉ።የአንዳርጋቸዉ ፍላጎት ቀፎዉ አንደተነካበት ንብ ‘ሆ’ ብለን ተነስተን እሱንና ሌሎች ተቆጥረዉ የማያልቁ ዜጎቻችንን የሚገድሉትንና እያሰሩ የሚያሰቃዩትን የወያኔ ዘረኞች ከአገራችን ምድር ጠራርገን እንድናጠፋ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ እንደ ብዙዎቻችን አባት አለዉ፤ እናት አለዉ፤ ባለትዳርና የልጆች አባት ነዉ፤ ወንድም፤ እህትና ጓደኞችም አሉት። እሱ ግን ከእናቱ፤ ከአባቱ፤ ከልጆቹና ከትዳሩ አገሬ ኢትዮጵያ ትበልጥብኛለች ብሎ የአዉሮፓን ትኩስ ምግብና የተሞናሞነ ህይወት ምን ሊሆነኝ ብሎ ምግብና ዉሃ ብርቅ ወደ ሆነበት በረሃ ሄዶ ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤ ጠንካራ መሠረት ያኖረ ሰዉ ነዉ። አንዳርጋቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀግና ያለህ ብሎ ለግማሽ ምዕተ አመት አርግዞ በጣር የወለደዉ የቁርጥ ቀን ልጁ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ወያኔ ሃያ ሶስት አመት ሙሉ በዘር፤ በቋንቋ፤ በከልልና በሃይማኖት ሲከፋፍል የከረመዉን ህዝብ ካልሰበሰብኩ እንዳለ እንደ ወጣ የቀረ ጀግናችን ነዉ፡፡ አዎ አንዳርጋቸዉ እንደ ስሙ አንድ ሊያደርገን ጎንበስ ቀና ሲል የለየላቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች እጅ ወድቋል። አንዳርጋቸዉን የምንወድና የአንዳርጋቸዉ በድንገት ከትግል ሜዳ መለየት ያንገበገብን በብዙ ሚሊዮኖች የምንቆጠር ኢትዮጵያዉያን ወደድንም ጠላን ዛሬ ያለን ምርጫ ከወያኔ ጋር ተናንቀን እኛንም አገራችንንም ነጻ ማዉጣት ወይም በወያኔ እየተረገጥን ልጆቻችንን፤ ጓደኞቻችንንና ወዳጅ ዘመዶቻችንን ተራ በተራ እየገበርን መኖር ብቻ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ዛሬ እጁ በዘረኞች ተይዞ የሚሰቃየዉ ከባርነት ነጻነት፤ በግሉ ከሚያገኘዉ ህብትና ብልጽግና የአገሩ ህልዉና በልጦበት ነዉ። አንዳርጋቸዉንና አገሬን የምንል ኢትዮጵያዉያን ከዛሬ በኋላ ይህ አንዳርጋቸዉ ያቀጣጠለዉ ህዝባዊ ትግል ወያኔንና ወያኔ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት እስካልደመሰስ ድረስ ለአንድም ቀን ቢሆን እንቅልፍ ሊወስደን አይገባም። አንዳርጋቸዉ የሂሊናም ሆነ የአካል እረፍት አግኝቶ እፎይ የሚለዉ እሱ ከወያኔ ቁጥጥር ስር ነጻ ሲወጣ አይደለም። አንዳርጋቸዉ እፎይ ብሎ የሰላም እንቅልፍ የሚተኛዉ እሱ የጀመረዉን የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጉዞ እኛ ስንጨርስለት ብቻ ነዉ። ስለዚህ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፤ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፤ እዉቀት ያለህ ደግሞ በእዉቀትህ ነገ ዛሬ ሳትል ይህንን ትግል ተቀላቀል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment