July20/2014
ዳዊት ሰለሞን
አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዳለፉት አመታት ሁሉ የኢትዮጵያን መንግስት የሚያስቆጣ ባለ 70 ገጽ ሪፖርት ከሁለት ሳምንታት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡ የተቋሙን ሪፖርት ከሌላው ጊዜ የተለየ የሚያደርገው በአንድ ርዕሰ ጉዳይ በአንድ ተቋም በማጠንጠኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የወንጀል ምርመራ ማዕከሎች መካከል በአዲስ አበባ ዕምብርት በሚገኘው ማዕከላዊ ተጠርጣሪዎች ግርፋት፣ማሰቃየትና ድብደባ እንደሚፈፀምባቸው ሪፖርቱ አትቷል፡፡
አሜሪካ በሁለቱ የኒውዮርክ መንትያ ህንጻዎቿ ላይ በአልቃይዳ የተቀነባበረ ጥቃት ከተሰነዘረባት በኋላ ‹‹ሽብርተኛ›› በማለት የሰየመችውን ቡድን አባላት ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በጆርጅ ቡሽ ፊት አውራሪነት የሽብር ቡድኑ ዋነኛ መጠለያ ያለቻችትን አፍጋኒስታንን ወረረች፡፡ በዘመቻው በቁጥጥር ስር የዋሉ የአልቃይዳ አባላትና ተጠርጣሪዎች በጄኔቭ ስምምነት መሠረት በህግ የመዳኘት መብት እንዳያገኙ ለማድረግ የቡሽ አስተዳደር ከግዛቱ ውጪ በኩባ ድንበር የሚገኘውን ጓንታናሞ ቤይን ከዛሬ አስር አመታት በፊት ከጦር ካምፕነት ወደ ማሰቃያ ማዕከልነት አሸጋገረው፡፡
‹‹በሽብርተኝነት›› ተጠርጥረው ወደ ጓንታናሞ ቤይ እንዲገቡ የተደረጉ ተጠርጣሪዎች የዜግነት ስብጥር የሚበዛበት ቢሆንም አንዳንድ መረጃዎች የሚበዙት ተጠርጣሪዎች አፍጋናዊያን፣ ኢራቃዊያን፣ የመናዊያን፣ ሊቢያዊያንና ግብጻዊያን ስለመሆናቸው ይጠቁማሉ፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል 99 ከመቶ ያህሉም የሙስሊም እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡
አሜሪካ በህገ መንግስቷ ተጠርጣሪዎች ዋስትና፣ ጠበቃ፣ ጎብኚና ነጻ የፍትህ ስርዓት እንዲያገኙ ለማድረግ ቃል የገባች ቢሆንም በጓንታናሞ ቤይ የተጣሉ ተጠርጣሪዎች ለረዥም አመታት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዳይታይ፣ ጎብኚዎች እንዳያገኙ፣ ግርፋትና ስነ ልቦናዊ የሆነ ቶርቸር እንዲደርስባቸው በማድረግ ከህገ መንግስቷ የተጣረሰ ኢ ሰብአዊ ድርጊት ስትፈጽምባቸው ቆይታለች፡፡
እስረኞቹን አጋቾቻቸው እጅና እግሮቻቸውን ለ24 ሰዓታት በሰንሰለት በማሰር ሲያሰቃዩአቸው ቆይተዋል፣ በረመዳን የጾም ወቅት እስረኞቹ የሃይማኖታቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ከምግብ ተከልክለው ወሩን ለማሳለፍ ቢዘጋጁም የማጎሪያው ሃላፊዎች ሀይልን በመጠቀም በቀን ለሁለት ጊዜያት ምግብ እንዲመገቡ በማድረግ ጥቃት ፈጽመውባቸዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት (የቡሽ አስተዳደር) ይህንን ግፍ በጓንታናሞ ቤይ ሲፈጽም የከረመው በገዛ ዜጎቹ ላይ ባይሆንም በሰብአዊ ፍጥረት ላይ የሚደርስን በደል የአገሪቱ ህዝብ በራሱ እንደደረሰ በመቁጠር የቡሽን የበቀል እርምጃ በተለያዩ መድረኮች ሲቃወም ተስተውሏል፡፡
ጥቁር አሜሪካዊው ባራክ ሁሴን ኦባማ ለፕሬዝዳንትነት ያደርጓቸው በነበሩ ቅስቀሳዎች ‹‹ጓንታናሞን›› ከተመረጡ እንደሚዘጉ መግለጻቸውም በአስገራሚ ሁኔታ የአገራቸውን ህዝብ ድጋፍ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል፡፡ ኦባማ የማሰቃያ ማዕከሉን ለመዝጋት ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ከተፎካካሪዎቻቸው ጠንከር ያለ ተቃውሞ ማስተናገዳቸው አልቀረም፡፡ አሁን የኦባማ ምኞት እውን ሆኖ ጓንታናሞ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ተዘግቷል፡፡ ፍትህ ተነፍገው የወታደሮች መጫወቻ ሆነው የቆዩ ተጠርጣሪዎችም በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እንዲቀርቡ ተደርገዋል፣የሚበዙትም ከአልቃይዳ ጋር ምንም አይነት የሚያገናኛቸው መስመር እንደሌለ በመረጋገጡ ከቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል፡፡
በኢትዮጵያው ጓንታናሞ ቤይስ?
የዛሬው የአፍሪካ ህብረት ህንጻ የቆመበት መሬት በዘመነ ደርግ ላቅ ያለ የስቃይ ምድር ነበር፡፡ ከርቸሌ ብዙ ሺህ ወጣት ኢትዮጵያዊያንን በልታለች፣ በወታደራዊው መንግስት ላይ ተቃውሞን ያሰሙ ዜጎች በከርቸሌ ፊደል የማይተርከውን ስቃይ አስተናግደዋል፡፡ በኢትዮጵያውያኑ የለቅሶና የደም መሬት ላይ የአፍሪካ መሪዎች አመታዊ ስብሰባቸውን ለማድረግ ሲመጡ በቻይና እርዳታ የተሰራላቸውን ህንጻ ውበት እንጂ በከርቸሌ የፈሰሰው ደም፣ የባከነው አእምሮና የተፈፀመው ግፍ አይታሰባቸውም፡፡ በዘመነ ደርግ ለከርቸሌ እስረኞችን ይመግብ የነበረው የምርመራ ማእከል ደግሞ ማዕከላዊ ነው፡፡
ማዕከላዊን በመገንባት የተቃዋሚዎቻቸውን በአደባባይ ለመገንፈል ያሰፈሰፈ ቁጣ መሸበብ የጀመሩት አጼ ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ ንጉሱ ተማሪዎችን፣ አመጽ ያማራቸውን ወታደሮች፣ ስልጣኔ የሸተታቸውን ሰራተኞችና የባላባት ጭሰኛ መሆን የመረራቸውን ገበሬዎች በምስጢር ፖሊሶቻቸው አማካኝነት እያደኑ ማስፈራሪያና ግርፊያ ይፈጽሙባቸው እንደነበር ለዚህ ፊቸር ያናገርኳቸው ሰዎች እማኝነታቸውን ሰጥተውኛል፡፡ ደርግ የንጉሱን ወንበር በመገልበጥ ስጣኑን እንደተረከበ የተነሳበትን ተቃውሞ ለማፈን ከሁሉም የማጎሪያ ካምፖች በተሻለ ማዕከላዊን ስለመጠቀሙ በዛ ያሉ ምስክሮችን መቁጠር ይቻላል፡፡
የኢህአፓ ወጣቶች በማዕከላዊ የሚያውቁትን ምስጢር እንዲያወጡ፣ያልተያዙ ጓደኞቻቸውን እንዲጠቁሙ በሚል በወታደሮች ተደብድበዋል፣ ሴቶቹ ተደፍረዋል፣ በኤሌከትሪክ ሽቦ ተጠብሰዋል፣ ጥፍሮቻቸው በጉጠት እንዲነቀሉ ተደርገዋል፣ ሰውነታቸው ተገልብጦ ውስጥ እግራቸው በበሬ ቆለጥ ተገርፏል፡፡ ድብደባውን መቋቋም ተስኗቸው ይህችን ጨካኝ አለም የተሰናበቱ የት የሌለ ናቸው በማዕከላዊ፡፡የወቅቱ የምርመራ ሰራተኞች ብቃት የሚለካው እየገረፉና እያሰቃዩ በሚያገኙት መረጃ እንጂ መረጃውን ለማግኘት በሚጠቀሙት ፖሊሳዊ የምርመራ ጥበብ አልነበረም፡፡ይህ ጥበብም እነሆ እስካሁን ድረስ እየተወራረሰ ይገኛል፡፡
በ1983 የሰርዓት ለውጥ ተደርጎ ራሱን ነጻ አውጪ በማድረግ የሚቆጥረው ኢህአዴግ ስልጣነ መንግስቱን ሲቆናጠጥ ማዕከላዊ ዑደቱን እንዲያቋርጥ አለመደረጉን በየጊዜው ከማዕከላዊ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡
በ1987 ዓ.ም የፀደቀው ህገ መንግስት ተጠርጣሪዎች ህገ ወጥ ለሆነ አያያዝ እንደማይደረጉ፣ ኢሰብአዊ የሆነ ጥቃት እንደማይደርስባቸው፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ፣ በምርመራ ወቅት የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃል በፍርድ ቤት መለወጥ እንደሚችሉ ቢደነግግም በማዕከላዊ እነዚህ ህገ መንግስታዊ መብቶች ሆን ተብለው እንደሚጣሱ በምርመራ ጣብያው ዘግናኝና የሰቆቃ ጊዜያትን ያሳለፉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ላወጣው ሪፖርት እማኝ እንደሆኑ የተነገረላቸው 35 በማዕከላዊ የነበሩ እስረኞችም የተናገሩት ለወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቆየታቸውን፣ በጨለማ ቤት መክረማቸውን፣ ከጠያቂዎች ጋር እንዳይገናኙ መደረጋቸውንና በምርመራ ወቅት ግርፋት፣ ማሰቃየትና ማስፈራራቶች ይፈፀምባቸው እንደነበር ነው፡፡
ከሪፖርቱ ውጪ ጀሚል አክበር፣ ስዬ አብርሃ፣ ደበበ እሸቱና ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል በጻፏቸው መጻህፍት በማዕከላዊ የምርመራ ማእከል ቆይታቸው ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ስቃዮችን ማለፋቸውንና መስማታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ የመጻሕፍቱ መልእክት አንድና አንድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመንግስታት ለውጥ ቢደረግም ማዕከላዊ ግን የየስርዓቱን ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞችና ተቺዎች ማሰቃ በመሆኑ ቀጥሏል፡፡
ጣውላ፣ ጨለማ ቤትና ሸራተን በማዕከላዊ
በማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል እንዲገቡ የተፈረደባቸው ዜጎች ቆይታ ለሚያደርጉባቸው ክፍሎች ተገቢ ነው ያሏቸውን ስያሜዎች አውጥተውላቸዋል፡፡ ጨለማ ቤት እጅግ ቀዝቃዛና ዘና ብሎ ለመተኛት የማያወላዳ የተፈጥሮ አልያም የሰው ሰራሽ ብርሃን አልቦ ነው፡፡ ወደዚህ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቀንና ሌሊት በጨለማ የሚዋጡ በመሆናቸው ሰዓት፣ ቀንና ምሽትን ለመለየት ይቸገራሉ፡፡ የቅንጅቱ ሊቀመንበር የነበሩት ኃይሉ ሻውል በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፍ ለ28 ቀናት ጨለማ ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸውን በመጨረሻም መርማሪዎቹ ‹‹መብራት የሚሰራልን አጥተን ነው ይቅርታ›› በማለት አምፑል በማስገባት እንዳበሩላቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሪፖርት ከሆነ በዚህ ጨለማ ክፍል የቆዩ ሰዎች ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ ወደ ውጪ ሲወጡ ለከፍተኛ የአይን ህመም ይዳረጋሉ፡፡
ጣውላ ቤት የተሻለ ስፋትና አጋር እስረኛ የሚገኝበት ከመሆኑ ባለፈ በጨለማ የተዋጠ ነው፡፡ ቤቱ ከጣውላ የተሰራ በመሆኑም ድምጽ ከየትኛው ክፍል እንደሚመጣ አይታወቅም፡፡ ይህም እስረኞቹ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲያንጎረጉሩ፣ የመሰላቸውን እንዲናገሩ ይረዳቸዋል፡፡ አንደኛው እስረኛ ለመጸዳዳት ከክፍሉ ወጣ በሚልበት አጋጣሚም ከሌላው እስረኛ ጋር የሚገናኝበት፣ የሚተያይበት በመሆኑም ለታሳሪዎቹ ህይወት እንድትሸታቸው ያደርጋል፡፡ ሸራተን በማዕከላዊ የቅንጦት ክፍል ነው፡፡ የክፍሉ ስፋት በመጠኑ የሚያወላዳ ከመሆኑም በላይ የመብራት ባለቤት ነው፡፡በዛ ያሉ እስረኞች የሚገኙበት በመሆኑም በማዕከላዊ እንደ ቅንጦት ተቆጥሮ ሸራተን ለመሰኘት በቅቷል፡፡ ሸራተን የገቡ እስረኞች በአብዛኛው የምርመራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በመሆናቸው በጨለማ ቤትና በጣውላ ቤት ያሳለፉትን መከራ እያነሱና እየጣሉ ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር ፍርድ ቤት የሚያሳልፍባቸውን ውሳኔ ይጠባበቃሉ፡፡
የመንግስት ምላሽና ሪፖርቶች
ሂዩማን ራይትስ ዎቹ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ኢሰብአዊ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ ሲያጋልጥ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የመንግስት ኃላፊዎችም ሪፖርቱን ከመንግስት ተቃዋሚዎች የተሰበሰበና እውነታውን የማያሳይ በማለት ከማጣጣል ተቆጥበው አያውቁም፡፡
የአሜሪካ መንግስት /ስቴት ዲፓርትመንት/ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች የእስረኞች አያያዝ እንዳሳሰበው የገለጸባቸው አጋጣሚዎች በዛ ያሉ ናቸው፡፡ በ2007 ኤፕሪል በዊኪሊክስ አማካኝነት የወጣ መረጃም በኢትዮጵያ የሚገኙ እስረኞችን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት የፕሪዝን ፌሎው ሺፕ መስራች ፓስታር ዳንኤል ለአሜሪካ ኤምባሲ ሰዎች መንግስት በእስረኞች ላይ ግርፋት፣ ማስፈራራትና ማሰቃየት እንደሚፈጽም መናገራቸውን አትቶ ነበር፡፡ በቅርቡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ላወጣው ሪፖርት የመንግስት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሽፈራው በጽሁፍ እንዲሁም የመንግስት ኮሚኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ለኤኤፍፒ በሰጡት ምላሽ ክሱን አጣጥለውታል፡፡
በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ቆይታ አድርገው የነበሩት ሁለቱ ስዊዲናዊያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሺብዬና ዮሃን ፒርሰን ‹‹ፖሊስ ሁሉም ነገር የሚያልቀው በፍርድ ቤት እንደሆነ ይናገራል፣ ነገር ግን ሁሉም ነገር የሚሆነው በምርመራ ወቅት ነው፡፡ ፖሊስ በሀይል ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ጉዳይ መፈፀማቸውን እንዲያምኑ ያደርጋል›› ይላሉ፡፡
በሪፖርቱ ዙሪያ ለኤ.ኤፍ.ፒ በእስር ላይ ስለምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የተናገሩት ወላጅ አባቷና ጠበቃዋ አቶ አለሙ ጌቤቦ ለሦስት ወራት ያህል ልጃቸውን በማዕከላዊ ማየት እንዳልቻሉ በመጥቀስ በእነዚያ 90 ቀናት ውስጥ ከቤተሰብና ከጠበቃዋ ለይተው ምን ሲፈጽሙባት እንደቆዩ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ርዕዮትን ከሦስት ወራት በኋላ እንዲመለከቷት ሲፈቀድላቸው ተጎሳቁላ ማግኘታቸውንና ለዘጠኝ ቀናት ያህል ምግብ ሳትመገብ መቆየቷን መረዳታቸውን መስክረዋል፡፡
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ወደ ማዕከላዊ የገቡ ሌሎች ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ከርዕዮት ጋር የሚመሳሰል ታሪክ እንዳላቸው የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ይናገራሉ፡፡
ፓስተር ዳንኤል በእስር ቤቶች ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽሙ መርማሪዎች መኖራቸውን መንግስት ከደረሰበት በኋላ የሚበዙትን ከስራ እንዳባረራቸው ለአሜሪካው ዲፕሎማት መናገራቸውን ዊኪሊክስ ቢዘግብም የመረጃ መረቡ ባወጣው ሪፖርት ፓስተሩ ነገሩን ለማድበስበስ ያህል እንደተናገሩት እንደቆጠረባቸው አትቷል፡፡
በምርመራ ላይ የቆዩ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡባቸው አጋጣሚዎች በምርመራ ወቅት ድብደባ፣ ማስፈራራትና ማሰቃየት እንደደረሰባቸው የተናገሩባቸው አጋጣሚዎችም በዛ ይላሉ፡፡ ዳኞች እንዲህ አይነት የመብት ጥሰት አቤቱታ ሲቀርብላቸው ፖሊሶች ላይ ጫን ያለ እርምጃ እንዲወሰድ አለማድረጋቸው የምርመራ ውስጥ ስቃዩ እንዲቀጥል የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
የእኛ ኦባማ የት ነው?
የኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊዎች የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች አልያም የአለም ባንክ ለሚያወጧቸው ሪፖርቶች የሚሰጧቸው ምላሾች አንድ ጫፍ የረገጡ ናቸው፡፡ የሪፖርቶቹን መውጣት ተከትሎ ጉዳዩን ለማጣራት ገለልተኛ ቡድን እንዲዘጋጅ የተደረገበት ጊዜ የለም፡፡ ጆርጅ ቡሽም እንዲህ ነበሩ፡፡ በጓንታናሞ ለሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ ወታደሮቻቸው ሴት እስረኞችን እንደሚደፍሩ፣ ታሳሪዎችን በረመዳን የጾም ወቅት በኃይል እንዲመገቡ ማድረጋቸው፣ ተጠርጣሪዎች ለወራት ፍትህ ሳያገኙ መቆየታቸው ሲነገራቸው ለመስማት አልፈቀዱም፡፡ በፕሬዝዳንቱ እምነት እየተሰቃዩ የሚገኙት ሰዎች ሳይሆኑ ‹‹ሽብርተኞች›› ናቸው፡፡
ኦባማ ግን እንደ ቡሽ በጭፍን ጥላቻ የታወሩ አልነበሩም፡፡ ጓንታናሞ የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚፈፀምበትና አሜሪካ ቆሜለታለሁ ለምትለው ዲሞክራሲ ተቃራኒ መሆኑን በመረዳት ጓንታናሞን ላይከፍቱት ቆለፉት፡፡
የእኛው ማዕከላዊ በእኛው ዜጎች እኛው ላይ ኢ- ህገ መንግስታዊና ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈፀምበት ማዕከል ነው፡፡ በጓንታናሞ አሜሪካዊያኑ የገረፉት፣ ያሰቀዩት አፍጋኑን፣ ግብጻዊውን፣ ኢራቃዊውን፣ አፍሪካዊውን ነው፡፡ በማዕከላዊ መሰቃየቱንና ህገ መንግስታዊ መብቱ እንደተጣሰበት የሚናገረው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኦባማ ጓንታናሞን ስለ አሜሪካዊያን አልዘጉትም፡፡ ስለ ፍትህ እንጂ፡፡ የእኛ ኦባማ ለጊዜው እዚህ ነኝ ባይለንም የመጣ ቀን ግን ማዕከላዊን ስለእኛ ይዘጋዋል፡፡
ከዘ-ሐበሻ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment