Thursday, June 26, 2014

እሥረኛው ጠቅላይ ሚንስትር ደሳለኝ ኃይለማርያም በምግብ ራሳችን ችለናል ማለቱ ከምኑ ላይ ነው ስህተቱ?!

June 26, 2014
በጌታቸው ፏፏቴ
መግቢያ፦ ህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊ የሆነ አጀንዳ እንደሌለውና ሊኖረውም እንደማይችል ከተቋሙ መሠረታዊ ፕሮግራም በመነሳት ግንቦት 20/1983 በሚል ባቀርብኳት ጦማሬ አስረግጨ አሳውቄ ነበር። እነዚህን የምልበት ምክንያት ከባዶው ተነስቼ ሳይሆን ድርጅቱ ከፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ካለው ፀረ-ሕዝብና አሰቃቂ ዘግናኝ ተግባሮቹ በመነሳት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እወዳለሁ።የዚህ ድርጅት መነሻውም ሆነ የመጨረሻ ግቡ ከተቻለ የህወሃት/ኢህአዴግ ትውልዶች ብቻ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር አለዚያም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነውን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነገድ ተራ በተራ እያዘናጉ መጨረስና አገሪቱንም ለባእዳን እንዳወጣች ሸጦ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳልነበረች ማድረግ እንደሆነ ለማንም ስውር ሊሆንበት አይገባም።

ድርጅቱ ቀደም ሲል ጫካ ውስጥ በትግል በነበረበት ወቅትም ሆነ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የፈፀማቸውና እየፈፀማቸው ያሉት አፀያፊ ድርጊቶች ታይተው ያማያውቁ የኢትዮጵያዊነት ሞራልና ስብእና የጎደላቸው ስለመሆናቸው ብዙ የተባለ ሲሆን አንድ ግልጽና ቀላል አስረጅ መጥቀስ የበለጠ እውነታውን ያሳያል ብየ አስባለሁ።

የፌደራል መንግሥት እየተባለ የሚጠራ የይስሙላ መንግሥት ቢኖርም የመንግሥትንም ሆነ የድርጅትን ሥራ ጠቅልሎ የሚያከናውነው ህወሃት/ኢህአዴግ ነው። በግንባሩ ውስጥ የተካተቱት ድርጅቶች የመወሰንና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ባይኖራቸውም በህወሃት በጎ ፈቃድ የሌሎችን ነፃ ተፎካካሪዎች እድል ለመዝጋት የግል ባንኮችን ኮታው እንዲሸፍኑ ተደርጎ በሥራቸው የሚያንቀሳቅሱት ባንክ አላቸው።እነዚህ ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሥራ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ሆን ብሎ የታቀደ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ሊሰሩ ያሰቡትን ተግባር እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ተንኮለኛ ሴራ ነው።ከነዚህ ከተጠቀሱት የህወሃት አዳማቂ ድርጅቶች ባንክ ብድር ተበድሮ ኢንቨስት ለማድረግ ቢታሰብ ደግሞ አይሞክሩትም እንጅ የግድ መሟላት ያለበት አንድ ነገር አለ። ይኸውም የህወሃት/ ኢህአዴግን የአባልነት ካርድ መያዝ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንቅስቃሴን ለመግታትና የውጭ ምንዛሬ እንዳያገኝ ከማድረጉ አልፎ ባንኩ ራቁቱን እንዲቀር ያደረጉ ሌሎች የተቀነባበሩ ተንኮለኛ ተግባሮችም ተፈጽመዋል እነሱም ከባለ ሥልጣናቱ ቀጭን ትእዛዝ እየተሰጠ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች በኢንቨስትመንት ስም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እንዲበደሩ ይደረጋል። ገንዘቡን ወስደው ከተጠቀሙ በኋላ ለባንኩ መክፈል የሚገባቸውን የተጠቀሙበትን የአገልግሎት ዋጋ(interst) መክፈል ይገባቸዋል ነገር ግን ይህ ሊሆን ይቅርና ዋናውን ብድርም አሻፈረን አንከፍልም ብለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኪሳራ እንዲደርስበት አድርገዋል።ይህችን ትንሽ ምሳሌ ያቀረብኩት የሌሎቻችሁንም ስሜት ለመቀስቀስ እንጅ ወንጀሉማ ስፍር ቁጥር የለውም እያልኩ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልግባ።

አዎ! አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም በግንቦት 20 ንግግሩ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏን ተናግሯል።ንግግሩን ሰምቸዋለሁ።ነገር ግን ስለማን እንደተናገረ ለማወቅ ለኔ ጊዜ አልወሰደብኝም።የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ወይም የልማታዊ መንግሥቱ መርህ ህወሃት/ኢህአዴግን፤ የግንባሩ አባላትንና ደጋፊዎችን ብቻ የሚመለከት እንጅ ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም።ወደፊትም እንዲኖር የሚታሰበው ትውልድም በዚህ ዘረኛ ድርጅት ፕሮግራም ተኮትኩቶ የሚወጣን ትውልድ እንጅ ሌላ ኢትዮጵያዊ ትውልድ እንዲሆን በፍጹም አይታሰብም ይህን ነው ማወቅ ያለብን።

ቀደም ሲል በአንድ ጹሑፌ ላይ ደርግ ከወደቀ በኋላ በሠራዊት ግንባታና አደረጃጀት ጉዳይ ላይ የተፈጸመ አሳዛኝ ድርጊት ጠቅሸ ነበር። ይኸውም ህወሃት አሰልፎት የነበረው ሠራዊት ከፍተኛ ቁጥር የነበረው መሆኑና የአዲሱ የሠራዊት አደረጃጀት ደግሞ ክልሎች ባላቸው የሕዝብ ብዛት ነው ስለሚል የህወሃትን ሠራዊት ላለመበተን ሲባል የተወሰደው እርምጃ አማርኛ የሚችለው የህወሃት ሠራዊት የመከረኛውን አማራ ሕዝብ ኮታ እንዲሸፍን ማድረግ ነበር ። የቀረውን በትግራይ ሕዝብ ባዛት መጠን ማሰለፍና ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተላበሱትን ደግሞ መዳረሻቸውን በማጥፋት ህወሃት ዓላማውን ስኬታማ ለማድረግ ችሏል።አሁን ደግሞ የህወሃት አባላት የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲማሩና የኦሮሞውን ክልል በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተወሰደውን አቋምና በየዐረብ አገሩ በዐረብኛ ቋንቋ የሰለጠኑ ወጣቶች ለማፍራትና በየኮሚኒቲውና ኤምባሲው ለመሰግሰግና የስለላ ተግባራትን ለማካሄድ ሲባል የሀገሪቱ ሀብት(ገንዘብ)ለዚህ ወጭ መሸፈኛ እየተመዘበረ ያለበት መሠረታዊ ምክንያት (አንድምታው )ህወሃት ወለድ የሆነ አዲስ ትውልድን የመገንባትና
የመትከል አባዜ ነው።

ህወሃት ጫካ ውስጥ በነበረበት ወቅት ወደ ፊት ድርጅቱ ወደየት እንደሚሄድ የሚያሳይ ማኒፌስቶ በ1976 ዓ/ም ማውጣቱ ይታወቃል።ከ1983ዓ/ም ከደርግ መውደቅ በኋላ ግን ህወሃትን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት በመቁጠር ሕዝቡ የተዘናጋበት ጉዳይ ቢኖር የህወሃትን የመጨረሻ ግብ መርሳቱ ነው።ህወሃት ለ23 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ያደረገው ቆይታ ኢትዮጵያዊ በመሆን ሳይሆን እንደ ጣሊያንና ድርቡሽ(የመሐዲስት) ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ መጥፋት ያለበትን ለማጥፋት ሊዘረፍ የሚችለውን የሀገሪቱ ሀብት ለመዝረፍና ኢትዮጵያን በታትኖ በማጥፋት ለትውልደ ህወሃት የሚሆነውን አዲሱን የህወሃት ሥርዎ መንግሥት ለማመቻቸት ነው።

ከአፋር ጀምሮ የኤርትራን አጎራባች ድንበሮች እያጠቃለለ ከሰሜን ወሎ የማይጨው አውራጃን እንዳለ በመውሰድ ሰሜን ጎንደር ጠልምት ወልቃይት ጠገዴን፤አርማጭሆን እያጠቃለለ መተማን ሙሉ በሙሉ ካርታው ውስጥ ያስገባና ሽንፋና ቋራን ዘልቆ እስከ ጋምቤላና ቤንሻንጉል እየመረሸ ወለጋንም ሸረፍ በማድረግ በመውሰድ ”ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ” መገንባት ነው።ይህ ተግባር ባሳለፍናቸው የህወሃት 23ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል። አሁንም ዋናው ግብ እሱ በመሆኑ ሰላዮችን ካድሬውንና የህወሃትን የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በውጭ ያደራጁትን የህወሃት አባል “ከሱዳን ተመላሽ ወገን”በማለት እያሰፈሩ ይገኛሉ። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ይህን መሬት ለሱዳን ሰጥተውት የለም ወይ?የሚል ሊሆን ይችላል።አስቀድሞ ማለቅ ያለበት ተግባር ስለ አለ እንጅ በህወሃት ሰፍሳፋ ተፈጥሮ ይህን የመሰለ ለምና ውሃ ገብ መሬት ለሱዳን? እንዴት ብሎ? ወደ ፊት በሰፊው እናየዋለን።

አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም፦ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደማይወክልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ አለመሆኑ ግልጽ ቢሆንም ቢያንስ ሲወራ ሊሰማ ይችላል ብየ እገምታለሁ እዛው ከመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ በየሆቴሉ የቆሻሻ መጣያ የተጣለ ትራፊ ምግብ ለማግኘት የሚደክሙትን፤በየትምህርት ቤቱ በርሃብ ጠኔ የሚወድቁትንና መማር አልችል ያሉ ወጣቶች በሞሉባት አዲስ አበባ ፤ከሀገሪቱ ሕዝብ 1/3ኛው ቁጥሩ ከ30ሚሊዮን የማያንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በርሃብ አደጋ ላይ ያለ መሆኑን ዓለም አውቆትና የውጭ እርዳታ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት «በምግብ ራሳችን ችለናል» ብሎ መናገር ምንያል ቅጥፈት የተሞላበት ንግግር እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው?

አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም፦ ህወሃት/ ኢህአዴግና የፌደራል መንግሥትን ምንነት ገና የገባው አለመሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮችን ሲናገር ተስተውሏል።ከኤርትራ ጋር ስለሰላም ለመመካከር ዝግጁ መሆኑንና በሌላ ወገን ደግሞ ኤርትራን የአሸባሪዎች ደጋፊ ናት የሚል ክስ መስል ነገር ሲናግርም ተደምጧል ሁለቱ የሚቃረኑ ሃሳቦች መሆናቸውን መመርመር አልቻለም።መራሾቹ ነብሰ ገዳዮች ስብሃት ነጋ ፤ ስዩም መስፍን ፤ አባይ ፀሐየ ፤ አዲሱ ለገሰ ፤ ብረከት ስምኦን ፤ አርከበ እቁባይ ፤ሕላዊ ዮሴፍ፤ታደሰ ካሣ፤ ደብረጽዮንና ቴዎድሮስ አድሃኖም አንብብ ብለው የሚሰጡትን ጹሑፍ ከማንበቡ በፊት ቢያነበው ቢያንስ ለያዘው ሥልጣን የሚመጥን ሀሳብ ባገኘ ነበር ።ነገር ግን ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ አባላትና የጡረታ አማካሪዎቹ እሱን እያጋፈጡ የውስጥ ፍላጎታቸውንና የተነሱበትን ዓላማ እያስፈጸሙ ይገኛሉ። አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም የህወሃት ጠቅላይ ሚንስትር ሁሌ ስለአንተ የሚጻፉ ጹሑፎችን አንብባቸው አንድ ቀን ልብ ትገዛ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ስህተቱ ከምኑ ላይ ነው በሚል ርእስ የገባሁት ስህተት አልተናገረም ለማለት ሳይሆን ጹሑፌ ትኩረት እንድትስብ በማሰብ ነው እንጅ ስህተቱንማ ከቁመቱ በላይ በሚደርስ አዘቅት ተዘፍቆበታል። አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም ወደታች ወርዶ በቀበሌ የሚኖረውን የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ነዋሪ ኢትዮጵያዊ የሚያይበት እድል ቢኖረው ምን ሊለን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ዳሩ ግን እሱ ራሱ በግዞት ላይ ያለ እስረኛ ስለሆነ ያሳዝነኛል።

የህወሃት እንባ ጠባቂዎች በትክክል በልተው ያድራሉ ። ምክንያቱም ሕሊናቸውን ለሆዳቸው ሲሉ ሸጠውታልና።አባላቱ ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ስለሆነ ምን አጥተው? እንኳን ሦስት ጊዜ አስር ጊዜስ ቢበሉስ ምን ጎድሎባቸው? እላይ ያለው ቱባ-ቱባ ባለሥልጣን በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ከሚፈለገው በላይ የጠገቡና የጥጋብ ቁምጣናቸውን በአረቄ ለማወራረድ ሲደፈርሱ የሚያድሩ፤ ሰማይ ውረድ የሚሉ ጥጋበኞች፤ ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ፎቆች ያላቸው፤ሀብት ተብሎ የሚቆጠረው ሁሉ የነሱ ያደረጉ፤ መሬትን የነሱ ያደረጉ፤ የበርካታ ሆቴሎች ባለቤት፤ልጆቻቸው ከፍተኛ ወጭ እየተከፈለላቸው ውጭ አገር ተልከው የሚማሩ፤ የፓርቲ ልብስ የሚገዙት ውጭ አገር ነው፤ ጉንፋን በያዛቸው ቁጥር የሚታከሙትም ውጭ አገር በሚገኙ ሆስፒታሎች ነው።ይህ ሁሉ የሚደረገው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት እየተዘረፈ ነው።

የአቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም የግንቦት 20 ቆርፋዳ ንግግር ቢያንስ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ያለበትን ደረጃና ሁኔታ አለማወቅ ራሱን ችሎ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት ድናቁርቶች እየተመራች መሆኗን ከማሳየቱም በላይ አምራችና መሬት እንዳይገናኙ የተደረገበትን መሠረታዊ ምክንያት አለማወቁ የግለሰቡን ጥሬነት ያሳያል።ለባዕዳን የተሸጠው መሬት እንዳለ ሆኖ የቀረው መሬት ላይ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተሮችና አርሶ አደሩ ለማምረት እድሉ ቢፈጠርላቸው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ሌሎችን የጎረቤት አገሮች ሊመግብ የሚችል ምርት ማምረት ትችል ነበር።

አብዛኛው ከደቡብ እስከ ምዕራብ ያለውን የሀገሪቱን ክፍል ወስደን ብንመለከት ለም ድንግልና የተለያዩ አዝእርቶችን ሊያመርት የሚችል መሬት እንዳለ ይታወቃል።ከደርግ መውደቅ በኋላ ከ1985 እስከ 1987ዓ/ም በነበረው ወቅት የነበረውን የሕዝቡ ተነሳሽነትና በምእራብ ጐንደርና ምእራብ ጐጃም ብቻ የነበረው የምርት ውጤት ሲታይ ተስፋ ሰጭ ነበር። ሁመራና መተማ ተከማችቶ የነበረውን ማሽላ፤ ሰሊጥና ጥጥ ለማጓጓዝ የነበርውን የተሽከርካሪና የመደብር እጥረት አስታውሳለሁ።ያን ተነሳሽነት ግን ገዥዎቻችን ቀልጥፈው አጠፉት። የመሬት መጠቀሚያና የእርሻ ግብር ክፍያውን እላይ ሰቀሉት ኢንቨስተሩም የሥራ ፈቃዱን መመለስ ጀመረ። ህወሃትን እሰየው አሰኘ ታይቶ የነበረው ተስፋ ጨለመ።

አድንቁረህና አስርበህ ግዛው መሆኑንንም አሳዩን።ያን ተስፋ የተጣለበትን የደቡብ ምእራብና ሰሜን ምእራብ መሬትም ለሱዳን አስረክበው ዛሬ የሱዳን ገበሬዎች በህወሃት የመከላከያ ሠራዊት እየታጀቡ አባቶቻችን ደም አፍስሠው አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ያቆዩትን መሬት እያረሱት ይገኛል።አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም ለማወቅ የተሳነው እንዲህ አይነቱን ሀቅ ነው።በዚህ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመነ መንግሥት በነበረው ፓርላማ ውስጥ እንስጥ አንስጥ በሚል ሃሳብ ተነስቶ አብዛኛው የፓርላማ አባል ለዚህ ቆላማ መሬት ብለን ወዳጅነትን ከሱዳን ከምናጣ ይውሰዱት ሲል ጥቂት የፓርላማ አባላት በድርጊቱ ተቆጥተው ፓርላማው ውስጥ በወንበር መደባደብ እንደተጀመረና ወዲያውኑ ለሱዳን ይሰጥ የሚለው ውሳኔ ተሽሮ ድንበሩ እስከ አሁን የኛው ዘመን ድረስ በጦር ኃይል ሳይሆን በህዝብ የጎበዝ አለቆችና በራሱ ትጥቅ ተከብሮ የኖረ መሬታችን ነው ዛሬ ለሱዳን የተሰጠው።

አሁን ያለው ፓርላማ ፓርላማ ነው ለማለት እንደማይቻል ይታወቃል።የካድሬ ስብስብና እጅህን አውጣ ሲባል ብቻ እጁን እያወጣ ድምጽ የሚያስቆጥር እንጅ በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ወኔ ለሀገር የሚጠቅም ሃሳብ ያመነጫል ተብሎም ተስፋ የሚጣልበት ፓርላማ አይደለም። ለግልጥቅሙና ለሆዱ የተሰለፈውን ህወሃት ከየትም ለቃቅሞ የሰበሰበው ጥርቅም ነው። አንድ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ግን»- እንደ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት መርዙን የተከለ አልነበረም እሱ ወደ መጨረሻው ከተጓዘ በኋላም ዛሬ እየገዙን ያሉት እኩያን “ በመለስ ራእይ” ስለሆነ እነዚህን ስንኩሎች ነቅለን ካልጣልን እፎይ የምንልበት፤በኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚተከልበት፤የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት፤ኢትዮጵያውያን ተፋቅረውና ተከባብረው በጋራ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ማሰብ አይቻልም።

መፍትሔ አልባ የሚፈጠር ችግር የለም። እኛን ለገጠመን ድቅድቅ የጨለማ ዘመን ደግሞ መፍትሔ አለው ብየ አስባለሁ።”የፀደይ አብዮት”በመባል የሚታወቀው የሕዝብ አመጽ የቱኒዚያን፤የግብጽን፤የየመንን፤የሊቢያን፤የሶርያን አሁን ደግሞ የኢራንን መሬቶች እንዳንቀጠቀጠና እያንቀጠቀጠ እንደሚገኝ ይታወቃል።አዎ! ብዙ መስእዋትነት ተከፍሎበታል ቢከፈልበትም ትርጉም ያለው ውጤት ደግሞ አስገኝቷል።በእኛም አገር ትግሉ አፈና የበዛበት ቢሆንም አላቋረጠም።ዳሩ ግን የተከፈለው መስእዋትነትና የተገኘው ውጤት ሲመዘን ብዙ ጎደሎዎችን አሳይቷል።አንደኛ ትግሉ ከየግል ፍላጎት የሚነሳና የተናጠል መሆኑ ፤ሁለተኛ ሁሉንም የሕ/ሰብ ክፍል በአንድ ጊዜ ያነቃነቀ አለመሆኑ፤ሦስተኛ በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም አንድ ቀን ብቻ የሚደረግ ትእይንተ ሕዝብ እንጅ ቀጣይነት የሌለው መሆኑ፤አራተኛ በሕዝብ የሚደረጉት ትእይንተ ሕዝቦች ታክቲክ ለገዥው ቡድን የተጋለጡ መሆናቸው ነው።

የማይሳሳት ቢኖር የማይሰራ ወይም የማይንቀሳቀስ ብቻ ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን ህወሃትን ለማስወገድ በተመቸው መንገድ ሁሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ተጉዘናል።ስንጓዝ ደግሞ ስህተቶች ተፈጽመዋል ስለሰራን ተሳስተናል ትልቁ ጉዳይ ግን ከስህተት መማርና ከዚያ አደጋ የመውጣቱ ቅልጥፍና ጉዳይ ነው ወሳኙ።አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ከችግር ጋር ያጋፈጠንን ህወሃትን ጡንቻው እንዲያብጥና ጠንካራ ጠላታችን እንዲሆን አብቅተነዋል። ምክንያቱም የጠላትን ጠንካራና ደካማ ጎን መገምገም አልቻልንም። የህወሃት ጠንካራ ጎን እርስ በርሳችን እንድንባላ ማድረጉ ሲሆን ይህን አሜን ብለን ተቀብለነዋል።እስከ መቼ? ደካማ ጎኑ ህወሃት የማይወደው “ሕብረት ወይም አንድነት ስንፈጠር ነው”ካልተሳሳትኩ ቁልፉ እዚህ ላይ ነው ያለው።ወደዚህ እንዳንመጣ ያደረገው ደግሞ ከሥልጣን ጥማት ጋር የተያያዘና እኔ ከሁሉም የላቅሁ ነኝ የሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው። በዚህ ላይ የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚፈልገውን የመሾም የማይፈልገውን የመሻር ሥልጣኑን የማይቀበል አመለካከት ተሸክመን በመጓዛችን ምክንያት ነው።

ስለዚህ በኢትዮጵያ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ተቻችሎ አንድነትን መገንባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች በመተሳሰብ በፍቅር በጋራና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ራእይ ይዞ መታገል አግባብ ነው ብየ አስባለሁ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላዓለም ትኑር!!!

እያንዳንዳችን ራሳችን ነፃ ለማውጣት እንታገል!!

በቀጣዩ እስከምንገናኝ ለዛሬ ያለኝን እዚህ ላይ ጨረስኩ።

No comments:

Post a Comment