June23/2014
አዋሳ ሆይ እስከመቼ የዳንስ ከተማ ብቻ እንድትሆኝ ይፈረድብሻል? የፖለቲካ ከተማም ሁኝ እንጅ!!!የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ገፍቶ በወጣ ቁጥር የአምባገነኖች መደናበር ያይላል፡፡ ሲደናበሩም ህግ ይጥሳሉ፣ ህዝብ ያሰቃያሉ፣ ሀገር ይበድላሉ፡፡ ግን እድሜ ልክ ዕየተጨቆኑ መኖር አይቻልም፡፡ ‹‹ተቀምጦ ከመኖር ቆሞ መሞት ይሻላል›› እንዲሉ፡፡ ቆሜ መሞት ይሻለኛል የሚሉ ዴሞክራሲ ናፋቂዎች እየበረከቱ ነው፤ እምቢ ከፈለግህ ይሄው እሰረኝ! የሚሉ ትንታግ ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡
እንደዚህ እንድል ምክንያት የሆነኝ ‹በደቡብ ክልል› አዋሳ ከተማ አንድነት ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ነበር፡፡ ህጉንም ጠብቆ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቆም ነበር፡፡ ትናንት ይካሄድ ለነበረው የተቃውሞ ሰልፍም አዋሳ ካለው መዋቅር ጋር ተቀላቅለው ቅስቀሳ የሚያካሂዱ ትንታግ ወጣቶች ከአዲስ አበባ አዋሳ ገብተውም ነበር፡፡
ነገር ግን የአቶ ኃይለማርያምን በድጋፍ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በተለይ በደቡብ የገዥነት መጥፎ ስሜት የተጠናወታቸው የታች ባለስልጣናት ህግ በአደባባይ እየደፈጠጡ ነው፡፡ ስለዚህ በቅስቀሳ ላይ የነበሩትን አባላትና አመራሮች አሰሩ፡፡ ዴሞክራት ወጣቶች ግን በእስሩ አልተበገሩም ‹‹ህጉን ጠብቀን አሳወቅን፣ የእውቅናውን ደብዳቤ መስጠት ይህን ሊሰራ የተቀመጠው አካል ድርሻ ነው፡፡ እውቅና ወረቀቱን የሚሰጠው አካል ስራውን ስላልሰራ እኛ ስራ ማቆም የለብንም፡፡›› በማለት ስራቸውን እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋቸዋል፡፡ ይህ የሆነው ሐሙስ ነበር፡፡ አሳሪዎቹ ያለምክንያት ማሰራቸው ሲያስጨንቃቸው ማታውኑ ‹‹ነገ እንዳትቀሰቅሱ፣ ከቀሰቀሳችሁ እናስራችኋለን›› ብለው ይለቋቸዋል፡፡
ትንታጎቹ የዴሞክራሲ ናፋቂዎች ግን ህገ ወጡን ትእዛዝ አልተቀበሉም፡፡ ህገወጡን ትእዛዝ ከመቀበል መታሰር እንደሚሻል ወሰኑ፡፡ አርብ ጠኋትም ወደ ቅስቀሳቸው ገቡ፡፡ አሳሪዎችም ካቴናቸውን ይዘው መጡና አሰሯቸው፡፡ በአጠቃላይ በአዋሳ የሚገኙ አመራሮችንና አባላትን ከየቦታው ለቃቅመው አሰሯቸው፡፡ ሰልፉም በዴሞክራሲ ደፍጣጮች ጉልበት ለጊዜው ተስተጓጎለ፡፡
No comments:
Post a Comment