June 10/2014
አብርሃ ደስታ
በራያ ዓዘቦ ወረዳ ወራባዮ ቀበሌ ፈድሻ በተባለ መንደር ነው። ያከባቢው ኗሪዎች እንደማንኛውም የሌላ ወረዳ ኗሪዎች በሴፍቲኔትና አስቸኳይ እንደርታ (ህፁፅ ሓገዝ) ይተዳደራሉ። የሴፍቲኔት እርዳታ በሥራ የሚሰጥ ነው። መስራት የሚችሉ ጉልበት ያላቸው ግን ድሃ ገበሬዎች በሴፍቲኔት ታቅፈው ያለማሉ። ከዛ ለሰሩት ሥራ ይከፈላቸዋል። ክፍያው የሴፍቲኔት እርዳታ ነው። የሴፍቲኔት እርዳታ ለድሆች በነፃ ሊሰጣቸው የሚገባ ቢሆንም (ምክንያቱም እርዳታ ነው) በስራ ነው የሚሰጣቸው። ለልማት እስከሆነ ድረስ በሥራ መሆኑ ችግር የለውም።
ድሃ ሁነው የጉልበት ስራ መስራት ለማይችሉ የሚሰጥ እርዳታም አለ። "አስቸኳይ እርዳታ" (ህፁፅ ሓገዝ) ይሉታል። የሚቀመስ የሌላቸው በእርጅናም በሌላ ችግርም መስራት ለማይችሉ የሚሰጥ እርዳታ ነው።
አሁን በተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ያሉ በእርዳታ የሚተዳደሩ ድሆች በማልቀስ ላይ ይገኛሉ። ለምን? የህወሓት መሪዎች ድሆች እርዳታ የሚሰጣቸው ማዳበርያ መግዛት ሲችሉ ብቻ ነው ብለው ወሰኑ። የሴፍቲኔት እርዳታ ለመውሰድ የግድ የ1400.00 ብር ማዳበርያ ከፍለው መወሰድ አለባቸው። ግን የሴፍቲኔት እርዳታ በነፃ መሆን ሲገባው በሥራ ነው። በስራ መሆኑ አይደለም ችግሩ። ሰዎች የሴፍቲኔት እርዳታ ለማግኘት ጉልበታቸው ያፈሰሱ ቢሆንም የሥራቸው ለመውሰድ የግድ ማዳበርያ መግዛት አለባቸው። ማዳበርያ ካልገዙ የሰሩትን የሴፍቲኔት እርዳታ መውሰድ አይችሉም። የስራቸውን ዋጋ የከለከላቸው የግል ድርጅት ቢሆን መክሰስ ይቻል ነበር። ችግር እየፈፀመ ያለው መንግስት ሲሆንስ ለማን ይከሰሳል? ይሄ ነገር በትግራይ ሙሉ ያለ ችግር ነው። ማዳበርያ ሳትገዙ እርዳታ የለም ይባላሉ።
የማዳበርያ ዋስ የሆነው ለባለጉልበት ድሆች የሚሰጠውን የሴፍቲኔት እርዳታ ብቻ አይደለም። መስራት ለማይችሉ (አዛውንቶችና አካላቸው ለጎደሉ) የሚቀመስ የሌላቸው ድሆች የሚሰጠው የአስቸኳይ እርዳታ (ህፁፅ ሓገዝ) ጭምር ነው የማዳበርያ ዋስ የሆነው።
በጣም ድሃ ለሆኑና መስራት ለማይችሉ የሚሰጠው አስቸኳይ እርዳታ ለመውሰድ የማዳበርያ ገንዘብ መክፈል አለባቸው። እነኚህ ድሆች የሚበላ ስለሌላቸው አስቸኳይ እርዳታ አስፈለጋቸው። የህወሓት ሰዎች ግን አስቸኳዩ እርዳታ ለመውሰድ የማዳበርያ ብር 1400.00 መክፈል እንዳለባቸው ይነግሯቸዋል። ቆይ ግን እንዚህ የአስቸኳይ እርዳታ ተጠቃሚዎች የሆኑት ምንም ሃብት ስለሌላቸው አይደለምንዴ??? ለማዳበርያ መግዣ ብር 1400.00 (1600.00 ከነወለዱ) ቢኖራቸውማ መቼ ህፁፅ ሓገዝ (አስቸኳይ እርዳታ) የሚያስፈልጋቸው ተብለው ይለዩ ነበረ?
ምንም ሃብት የሌላቸው በሴፍቲኔትና ህፁፅ ሓገዝ (አስቸኳይ እርዳታ) የሚተዳደሩ አርሶአደሮች የማዳበርያ ገንዘብ ሳትከፍሉ አይሰጣችሁም ስለተባሉ ተጨናንቀዋል። ምክንያቱም የማዳበርያ ዋጋ መክፈል አይችሉም። ምክንያቱም ድሆች ናቸው፤ ምንም ገንዘብ የላቸውም። ገንዘብ ስለሌላቸውም ነው እርዳታ ያስፈለጋቸው። የማዳበርያ ገንዘብ ካልከፈሉ ደግሞ እርዳታው አይሰጣቸውም። በግዜው ስላልተረዱ ደግሞ በረሃብ ችግር እየተሰቃዩ ነው። አቤት ብለው የሚሰማቸው የለም።
በራያ ዓዘቦ ወረዳ ወራባዩ ቀበሌ ማህበር የሚገኙ 25 አዛውንቶች እርዳታው ስለተከለከሉ የሚበሉት አጥተው እየተሰቃዩ ነው። አሁን ልመና ጀምረዋል። እያለቀሱ ነው የሚውሉት። ለነሱ ተብሎ የተለመነ የእርዳታ እህል ግን ለማዳበርያ መግዣ ተብሎ በካድሬዎች ተይዞ ታሽጎ ይገኛል። በነሱ ስም ይለመናል ከዛ ለፖለቲካ ፍጆታ ይውላል።
በተያያዘ ዜና በ"ፈድሻ" ሰፈር (ራያ ዓዘቦ ወረዳ ወራባዩ ቀበሌ) የምትገኝ አንዲት ድሃ ነፍሰጡር እናት የሴፍቲኔት እርዳታ ይሰጠኛል ብላ ሲትጠባበቅ ለመዳበርያ ተብሎ ስለተያዘ በምግብ እጦት ስትሰቃይ ቆይታ በቂ ምግብ ሳታገኝ ወልዳለች። ከወለደች በኋላም ምግብ ፈለገች። እርዳታው እንዲሰጣት ጠየቀች። የማዳበርያ ገንዘብ መክፈል እንዳለባት ተነገራት። ገንዘብ የላትም። እርዳታውም አላገኘችም። አሁን የሚበላ አጥታ በረሃብ ምክንያት አብዳለች። ያሳዝናል። ካድሬዎቹ ግን የማዳበርያ ገንዘብ ለመሰብሰብ ህዝብ አስረው ሲያሰቃዩ ይውላሉ!
ከመቼ ጀምሮ ነው ማዳበርያ አለመውሰድ የሚያሳስር ወንጀል የሆነው? ከመቼ ጀምሮ ነው እርዳታ የሚያስከለክል ጥፋት የሆነው? መዳበርያ መግዛት'ኮ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም። እናቶች እስካሁን ድረስ እያነቡ ነው። የሚደርስላቸው ይሻሉ።
It is so!!!
No comments:
Post a Comment