Wednesday, June 11, 2014

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሠራተኛ በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው አለፈ

June 11/2014
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሠራተኛ በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው አለፈ
-በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ አልተያዘም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሠራተኛ ናቸው የተባሉት አቶ በላይነህ ዳምጠው፣ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን ቤላ አካባቢ በሚገኘው የባለቤታቸው ቤተሰቦች ቤት ውስጥ በአንድ ግለሰብ በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉ ታወቀ፡፡

ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት መሆናቸው የተነገረው አቶ በላይነህ፣ ከሰኔ 1 ቀን 1992 ዓ.ም. ጀምሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ይሠሩ እንደነበር፣ ሕይወታቸው ባለፈበት ዕለትም ቀን በሥራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩ የምክር ቤቱ ሠራተኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ በላይነህ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ሥራ ውለው ቤላ አካባቢ ወደሚገኘው የባለቤታቸው ቤተሰቦች ቤት መሄዳቸውን የገለጹት የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ምክንያቱን በማያውቁትና ባላሰቡት ሁኔታ ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ሥራ ሲገቡ የሥራ ባልደረባቸው መሞታቸውን መስማታቸውን አስረድተዋል፡፡

ግለሰቡ የተገደሉት በጥይት ተመትተው መሆኑንና ለመሞታቸውም ምክንያት የሆነችው አንዲት የፖሊስ ባልደረባ መሆኗን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የፖሊስ ባልደረባዋ፣ የሟች ባለቤት ቤተሰቦች ግቢ ውስጥ ተከራይታ እንደምትኖር የገለጹት ምንጮች፣ በዕለቱ እሷ ዘንድ የመጣ አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ ባልታወቀ ምክንያት እሷን እያባረረ ሟች ወደነበሩበት ክፍል ሲገባ፣ መጀመሪያ የሟችን ባለቤት ያገኛል፡፡ እሷን ሁለት እጆቿን በጥይት መትቶ ከጣላት በኋላ ወደ ውስጥ ሲዘልቅና ሟች ሲወጡ በመገናኘታቸው በተደጋጋሚ በጥይት ደብድቦ ሕይወታቸው እንዲያልፍ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪው በአካባቢው የነበሩትን ነዋሪዎች በማስፈራራት የያዘውን ተሽከርካሪ አስነስቶ ከነመሣሪያው መጥፋቱንም የአካባቢው እማኞች ገልጸዋል፡፡

የ44 ዓመት ጐልማሳ የነበሩት የአቶ በላይነህ የቀብር ሥርዓትም ሰኔ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በፈረንሳይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙ ታውቋል፡፡ የሟች ባለቤት በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እንደተደረገላቸውና ለደረሰው አደጋ ምክንያት ናት የተባለችው የፖሊስ ባልደረባ በቁጥጥር ሥር ውላ በምርመራ ላይ መሆኗም ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪ ገዳይም ለጊዜው ማምለጡ ተጠቁሟል፡፡ ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ ፖሊስ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

No comments:

Post a Comment