Wednesday, June 25, 2014

አብዛኛው ህዝብ ለመንግስት ጥላቻ አለው” ሲል አንድ ከኢህአዴግ የወጣ ሰነድ አመለከተ

June25/2014
በአማራ ክልል ለሚገኙ አመራሮችና አባላት የተደረገውን ስልጠና አስመልክቶ ከብአዴን ጽህፈት ቤት በቁጥር ብአዴን 145/10/ኢህ/06 ለኢህአዴግ ጽ/ቤት  አዲስ አበባ በሚል የተጻፈው ደብዳቤ “አብዛኛው ህዝብ አሁንም ለመንግስት ከፍተኛ ጥላቻ” ማሳየቱን ገልጿል።

የብአዴን አመራር እና አባላቱ ከሰላም የዘለለ የልማት ለውጥ አለመምጣቱን፣ ኢህአዴግ ቢቀጥል ባይቀጥል ግድ እንደሌላቸው፣  እንዲሁም መንግስትን በትክክለኛ ዋጋው ሳይሆን በፍርሃት እንደሚያመሰግኑ በሰነዱ ላይ ተዘርዝሮ ቀርቧል።

“የኢትዮጵያ ህዝቦችና አገራዊ ህዳሴያችን” በሚለው የማጠቃለያ ግምገማ ሰልጣኞቹ ” ስለአገራቸው ታሪክ ብዙ ትምህርት መቅሰማቸውን፣ የህዳሴውን ጉዞ ለማሳካት ድርጅቱ እየከፈለ ያለውን መስዋትነት፣ የኢትዮጵያ ገናና ስልጣኔ ለምን እንደወደቀ፣ የህዳሴ ጉዞውን ሊያሳካ የሚችል መንግስት ያለ መሆኑን፣ የብዝህነትና እኩልነት ሀገራዊ ጠቀሜታ ፣ የአማራ ገዢ መደብ ሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ብቻ ሳይሆን አማራውን ጭምር እንደጨቆነ” የሚያሳይ ትምህርት መውሰዳቸውን ሰነዱ ያመለክታል።
በስልጠናው የብአዴን ታሪክ አብሮ መቅረቡንና ሰልጣኞችም የብአዴንን ታሪክ በማወቃቸው መርካታቸውን ሰነዱ አክሎ ይዘረዝራል።

“ግልጽነት ያልተያዘባቸውና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ተከታታይ ውይይትና ስራ የሚጠይቁ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?” በሚለው ንጹስ ርእስ ስር ደግሞ ” አሁንም ድረስ ብአዴንን የማይቀበሉ እና ከ97 ጋር በተያያዘ በመንግስት ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ድምጾች አሉ፣ ነገር ግን የመንግስትን የሃይል እርምጃ ተከትሎ በፍራቻ እንዲኖሩ ማድረግ ተችሎአል።” ሲል አስቀምጧል።
“በውይይቱ ወቅት የታዩ የአመለካከት ችግሮች ምንድን ናቸው?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር በርካታ ችግሮች ተዘርዝረው ቀርበዋል። ” በ1989 ዓም የነበረው የመሬት ክፍፍል ለቢሮክራቶች ለምን 4 ቃዳ መሬት ተሰጠ? በአማራ ክልል ብቻ የአርሶ አደር መሳሪያ ለምን ተነጠቀ? ልማቱ ወደ ትግራይ ይሄዳል፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት አስመራንና አሰብን መያዝ ነበረብን” የሚሉት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰልጣኞች መቅረቡን ያወሳል።

ሰነዱ በስልጠናው የታዩ ደካማና ጠንካራ ጎኖችንም ይዘረዝራል። ሰልጣኙ እርስ በርስ በመተጋገዝ፣ በመማማር ተሞክሮውን በማካፈልና በመተራረም የነበረው ሁኔታ በሚለው ንጹስ ርእስ ስር ደግሞ ” አሁንም ለመንግስት ህዝቡ በአብዛኛው ጥላቻ ማሳየቱ” የሚል ሰፍሮአል።

የብአዴን አመራርና አባላት ” በአብዛኛው ከሰላም የዘለለ የልማት ለውጥ የለም ” ብለው እንደሚያምኑ፣ “ኢህአዴግ ቢቀጥል ባይቀጥል ደንታ እንደማይሰጣቸው”፣ እንዲሁም “መንግስትን በትክክል ዋጋ ሳይሆን በፍርሃት እንደሚያመሰግኑ” በሰነዱ ማብቂያ ላይ ተገልጿል።

ሰነዱን ለኢሳት የላኩትን የኢህአዴግን ከፍተኛ አመራሮች እንደወትሮው ሁሉ በህዝብ ስም ለማመስገን እንወዳለን።

 ኢሳት ዜና :

No comments:

Post a Comment