Tuesday, June 10, 2014

በሃረር በጅምላ የተቀበሩ ሰዎች መቃብር መገኘቱን ተከትሎ ግጭት ተነሳ

June 10/2014


ሰኔ ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቀበሌ 19 ልዩ ስሙ ሃመሬሳ ወይም መድፈኛ ጀርባ በሚባለው አካባቢ ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓም በቁፋሮ ላይ የነበረ አንድ የግሪደር ሹፌር የተከማቹ አስከሬኖችን አግኝቷል።

የ2ቱ አስከሬን ምንም አይነት የመበስበስ ምልክት አለማሳየቱን የገለጸው ወኪላችን፣ ግለሰቦቹ በቅርቡ የተገደሉ መሆናቸውን ያሳያል ብሎአል። አንደኛው ሟች እጆጁን ወደ ሁዋላ ለፊጥኝ ታስሮ የተገኘ ሲሆን ሌላው ደግሞ አይኖቹ በጨርቅ ተሸፍነዋል።

የአራት አስከሬኖች አጽምም እንዲሁ አብሮ መገኘቱን የገለጸው ወኪላችን ፣ ቀደም ብለው የተገደሉ መሆናቸውን መረዳት እንደሚቻል ገልጿል።

ህዝቡ አስከሬኖቹ እንዳይነሱ እና ምርመራ እንዲካሄድባቸው ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ፖሊስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አስከሬኖቹን በማንሳት ከዋናው ቦታ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቦታ ላይ እንዲቀበሩ አድርጓል። በቅርቡ የተገደሉትን የሁለቱን አስከሬኖች ማንነት ለማወቅ አልተቻለም።

የግሪደሩ ሾፌር አስከሬኖቹን እንዳየ ራሱን በመሳቱ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

ኢሳት  በሃረር ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የነበሩ ሁለት ወጣቶች አድራሻቸው መጥፋቱን መዘገቡ ይታወሳል።

ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት ደግሞ የአወዳይ ህዝብ ዛሬ  ሰኔ 3 ወደ አካባቢው በመኪና ተጉዞ ከደረሰ በሁዋላ ተቃውሞ አሰምቷል። የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ፖሊስ በጋራ በአስለቃሽ ጭስ እና በተኩስ ተቃውሞውን የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ ህዝቡ በወሰደው እርምጃ በርካታ ፖሊሶች ቆስለዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ሃይል ዋና አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ሳላሃዲን ግራ አይኑ አካባቢ በድንጋይ ተመትቶ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

አካባቢው በክልሉ የኢንዱስትሪ መንደር የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በአነስተኛ እና ጥቃቅን ስም ለተደራጁ የባለስልጣናት ዘመዶች መሰጠቱን የዘገበው ወኪላችን፣ ለግንባታ የሚውሉ እቃዎች የተጠራቀሙበት መጋዘን በህዝቡ እንዲቃጠል ተደርጓል።

የህዝቡ ጥያቄ “አስከሬን እንዴት የትም ይጣላል፣ ትክክለኛ ቦታ ተፈልጎ በክብር ሊያርፍ ይገባል” የሚል መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።

የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ተጉዘው ለማረጋጋት ሙከራ አድርገው ባለመሳካቱ ፖሊሶች ህዝቡን በሃይል ለመበተን መገደዳቸውን ወኪላችን አክሎ ገልጿል።

ሀመሪሳ ከአወዳይ ወደ ሃረር መግቢያ ሲሆን አካባቢው ጫካ እና ሜዳ ነው።

በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ፖሊስ ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።

No comments:

Post a Comment