Monday, June 9, 2014

የየመን መገናኛዎች ካሉት….. የኢትዮጵያዊውን ሬሳ አውጥተው የራሳቸውን ቀበሩ… 100 ኤርትራዊያን ባህር ላይ ሰመጡ

June 9/2014
በግሩም ተ/ሀይማኖት

ወደ የመን የሚገባው ሰደተኛ ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው፡፡ አሁን አሁን የኤርትራዊያኑም ስደተኞች ቁጥር እንዲሁ እየጨመረ ነው፡፡ በትላንትናው እለት ከኤርትራ ተነስቶ ወደ የመን እየተጓዘ የነበረ 60 ኤርትራዊያንን የጫነ ጀልባ ባብል መንደብ የሚባለው የየመን ድንበር አካባቢ ሰመጠ፡፡ የተጫኑት በሙሉ ማለቃቸውን የዛሬ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ ከሶስት ቀን በፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ ከኤርትራ የተነሳ እና ኤርትራዊያንን የጫነ ጀልባ ሰምጦ 40 ሰዎች መሞታቸውን ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ100 በላይ ኤርትራዊያ በጀልባ መስመጥ ምክንያት በሶስት ቀን መሞታቸውን የተለያዩ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡

አልዮም የመን Yemen Today የተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት በሁለት እትሙ ስለ ኢትዮጵያዊያን ስቃይ አስፍሯል፡፡ ሰሞኑን በነበረብኝ የልጄ መታፈን ችግር ምክንያት በሰዓቱ ተርጉሜ ለማቅረብ አልቻልኩም ነበር፡፡ ባብል መንደብ የሚባለው አካባቢ የመናዊያኖቹ የአንድ ኢትዮጵያዊ ሬሳ አውጥተው የራሳቸውን ሬሳ መቅበራቸውን ይፋ አውጥቷል፡፡ ይህንንም ሁኔታ በአካባቢው ያሉ ድርጊቱ ያሳዘናቸው የመናዊያኖች ማጋለጣቸውን ጭምር አስፍሯል፡፡ እዚሁ ባብል መንደብ አካባቢ በአንድ ወቅት ስሄድ ከ500 ሜትር ርዝመት በላይ ያለ ቦታ ላይ በየመንገዱ የሞቱ የኢትዮጵያዊያን ሬሳ ተቀብሮ ለማየት ችያለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሶማሊያዋ አነስተኛ ወደብ ቦሳሶ ተነስተው ወደ የመን ከገቡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ 50 የሚሆኑትን ባለፈው ሳምንት በፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡ ምክንያትም ሲሰጡ የአል-ቃይዳ ግሩፖች ይንቀሳቀሱብታል በሚባለው እና ዋና ቤዛቸው አቅራቢያ ስላገኙዋቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በእርግጥም ሶማሊያዊያኑ ህገ-ወጥ አጓጓዦች በጣም ችግር ባለበት ሸቡዋ በሚባለው ቦታ ነው ያወረዷቸው፡፡ የUNHCR ቢሮ ሰራተኞች ለስደተኞቹ ወደ ከተማ እንዲገቡ ለ20 ቀን የሚያገለግል የይለፍ ወረቀት የሰጧቸው ሲሆን ይህን ወረቀት ፖሊሶቹ ቀደው ስደተኞቹን እንዳሰሩ ነው ጋዜጣው የዘገበው፡፡ የመን አልዮም ጋዜጣ በዘገባውም ሲያክል የይለፍ ወረቀቱን የቀደዱት እና እነሱን በቁጥጥር ስር ያዋሉት ቦታው በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ አሸባሪዎቹ የአል-ቃይዳ ቡድኖች አፍነው ወደ እነሱ እንዳያስገቡዋቸው ሲሉ መሆኑን የሸቡዋ የፖሊስ ጣቢያ አዛዥ መግለጻቸውንም ጨምሮ አስፍሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከሶማሊያ የሚነሱት ስደተኞች የሚወርዱበት የየመን ድንበር ሸቡዋ የሚባለው በአል-ቃይዳ ሀይሎች ቁጥጥር ስር ስለሆነ ከዚህ ቀድሞ ችግር የገጠማቸው እንኳን መኖራቸው ባይሰማ ከዚህ በኋላ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ማሰቡ አይከብድም፡፡ እባካችሁ…..

No comments:

Post a Comment