Saturday, May 24, 2014

የአኖሌ ሃውልት ፖለቲከኞችንና ምሁራንን እያወዛገበ ነው

May 24/2014

ታሪኩ አፈ ታሪክ ነው፤ በደንብ ሊጠና ይገባዋል ተብሏል

በአፄ ምኒሊክ ዘመን ተፈጽሟል የሚባለውን ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ለማሳየት በኦሮሚያ አርሲ ዞን አኖሌ በተባለ ስፍራ የተገነባው ሃውልት፤ የታሪክ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን እያወዛገበ ሲሆን፤ የታሪኩ እውነተኛነትና የሃውልቱ አስፈላጊነት አከራካሪ ሆኗል፡፡

ተቃራኒ አስተያየቶችን ለአዲስ አድማስ የሰጡ ፖለቲከኞች፤ ታሪኩ እውነተኛ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጥያቄ አልተስማሙም፡፡ በአኖሌ ተፈጽሟል የተባለው ጡት እና እጅ የመቁረጥ ድርጊት በታሪክ ሰነዶች ያልተመዘገበና ያልተረጋገጠ አፈታሪክ ነው የሚሉ ፖለቲከኞች፤ ሃውልቱ ጥላቻና ቂም በቀልን የሚሰብክ ስለሆነ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ በአኖሌ ኢሰብአዊ ድርጊት መፈፀሙ እውነተኛ ታሪክ መሆኑን የሚያምኑ ፖለቲከኞች በበኩላቸው፤ ሃውልቱ  መገንባቱ ተገቢ የሚሆነው  ድርጊቱ እንዳይደገም መማሪያ ስለሚሆን ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር አቶ አበባው አያሌው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሴት ልጅ በጦርነት ጊዜ የተለየ ጥበቃ እንደሚደረግላት ጠቅሰው፤ በአኖሌ ጡት ተቆርጧል ለሚለው ማረጋገጫ የሚሆን የታሪክ ሰነድ የለም ብለዋል፡፡ አፈታሪኩ ከብሔርተኝነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው ያሉት አቶ አበባው፤ አፈታሪክን መነሻ አድርጐ ሃውልት መገንባት አይገባም፤ ከዚህ በተጨማሪ ሃውልቱ ጥላቻና ቂም በቀልን ከማንፀባረቅ የዘለለ ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡

የታሪክ ምሁሩና ፖለቲከኛው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ የሃውልቱን መገንባት እንደማይቃወሙ ገልፀው፤ ከአፈ ታሪክ የዘለለ ማረጋገጫ ሰነድ አልተገኘለትም፤ ነገር ግን ከታሪክ የመረጃ ምንጮች መካከል አንዱ አፈ ታሪክ በመሆኑ  በጉዳዩ ላይ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የሃውልቱ መገንባት ጥላቻና ቂም በቀልን ለቀጣይ ትውልድ ያስተላልፋል የሚለውን አመለካከት እንደማይቀበሉት የገለፁት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፤ የታሪኩን እርግጠኛነት ከዩኒቨርስቲ መምህራን መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሃውልቱም በትክክል ድርጊቱን ከማንፀባረቅና ለመማሪያ ከመሆን ባለፈ ጥላቻና ቂም በቀልን አያስተላልፍም ባይ ናቸው፤ አቶ ቡልቻ፡፡ የመድረክ አመራር የሆኑት አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ የሃውልቱን መገንባት የሚቃወሙ ሰዎችን አጥብቀው ኮንነዋል፡፡ ጡት እና እጅ የመቁረጥ ድርጊት ተፈጽሟል የሚሉት አቶ ገብሩ፤ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ይሄን ታሪክ ለማድበስበስ መሞከራቸው ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተችተዋል፡፡ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ሞጋ ፈሪሣ በበኩላቸው፤ ጥንት የተደረገ ታሪክ እየተመዘዘ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉን ይቃወማሉ፡፡ የአሁኖቹ ባለስልጣናት ሃውልቱን የማስገንባትም ሆነ ታሪኩን የመንገር የሞራል ብቃት የላቸውም የሚሉት ዶ/ር ሞጋ፤ ዛሬም ቢሆን የኦሮሞ ህዝብ በወገኖቹ እየተበደለ ነው ብለዋል፡፡ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ፣ የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪ እና የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራር ዶ/ር ሃይሉ አርአያ ሃውልቱን አጥብቀው እንደሚቃወሙ አመልክተው፤ የሃውልቱ መገንባት የፖለቲካ ሴራ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡ ከሣምንታት በፊት የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድርን ጨምሮ የኦህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣናት የመረቁት ይሄ አወዛጋቢ ሃውልት፤ ለግንባታው 20 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን በውስጡ የአካባቢውን ባህል የሚያንፀባርቅ ሙዚየምን ጨምሮ የባህል ማዕከልን እንደማያካትት ታውቋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment