Saturday, May 3, 2014

ኦሮሚያ ካለቀሰች በኋላ – ህዝብ ሃሳቡን ሊጠየቅ ነው

የኢህአዴግ ቴሌቪዥን የቅስቀሳ ዘመቻ ጀመረ
mothers
May3/2014


በአምቦ ህዝብ አዝኗል። የሟቾች ቁጥር ከ22 በላይ እንደሆነ ይገመታል። በድፍን ኦሮሚያ ከ36 ሰዎች በላይ ተገድለዋል የሚሉ መረጃዎች አሉ። ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ 11 ሰዎች መሞታቸውን አምኗል። ታዛቢዎች እንደሚሉት ኦሮሚያ እያነባች ነው። ህዝብ ለቅሶ ከተቀመጠ በኋላ ኢህአዴግ በቴሌቪዥን ቅስቀሳ ጀመረ።
አርብ ሚያዚያ 24፤2006 (2/05/2014) ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በትዊተር ባሰራጩት መረጃ በጉዳዩ ዙሪያ ህዝብ ሃሳቡን እንደሚጠየቅ አመላክተዋል። የዚሁ መነሻ እንደሆነ የተነገረለት የቅስቀሳ ዘመቻ ዛሬ በቴሌቪዥን ተላልፏል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኩማ የድንበር ጉዳይ እንደማይነሳ በመጥቀስ ተቃዋሚዎችን ወቅሰዋል።
ኦሮሚያን ልዩ ዞን ከአዲስ አበባ ጋር ያዋሀደው አዲሱ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንዲሆን እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ በክልሉ ከተካሄዱት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች የአምቦው በጉልህነቱ ይጠቀሳል። አምቦ ነዋሪው ግልብጥ ብሎ በመውጣት ተማሪዎችን ተቀላቅሏል። ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ “… በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ሁከት ወደ ከተማ በመዝለቁ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በአምቦና ቶኬኩታዮ ከተሞች የሰባት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ባንኩን ጨምሮ በበርካታ የመንግስትና የሀዝብንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል” በማለት ግድያውን ከንብረት ውድመት ጋር ለማያያዝ ሞክሯል። በመደ ወላቡ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን፣ በሌላም በኩል “በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሰላም የእግርኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ ወደ70 ያህል ተማሪዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል” ሲል በህይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት አስታውቋል።police12
ኢህአዴግ የሟችና የቁስለኞችን ቁጥር ዝቅ ቢያደርግም የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ኦ.ፌ.ኮን በመጥቀስ እንደዘገበው በአምቦ ለተገደሉት 17 ሰዎች ኢህአዴግን ተጠያቂ አደርጓል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ ደግሞ አመጹን ከኋላ ሆነው የመሩትን የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል። ክልሉ በመግለጫው ህይወታቸው ስላለፈ ዜጎች ያለው ነገር ስለመኖሩ የኢህአዴግ ቴሌቪዥን ያለው ነገር የለም። ግድያው ስለተፈጸመበት አግባብ የማጣራት ስራ እንደሚከናወን እንኳን አልጠቆመም።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትና የጎልጉል የኦሮሚያ ምንጮች እንዳሉት በሰሞኑ ተቃውሞ ከ36 ሰዎች በላይ ተገድለዋል። የሲኤንኤን አይ ሪፖረተር በአምቦ ብቻ 30 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን አመልክቷል። ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ታስረዋል። የቁስለኞች ቁጥርም ቀላል አይደለም። በዚሁ ሳቢያ የህዝብ ስሜት በቁጭት የተሞላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የክልሉ ምክር ቤት ግን ህዝብ ከጎኑ መቆሙን በመጥቀስ ምስጋናውን አቅርቧል።
በአምቦ ከደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በመቀጠል በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ወረወረው በተባለ ቦንብ አንድ ሰው መሞቱና 70 መቁሰላቸው አስደንጋጭ ዜና ሆኗል። ቦንቡን ማን ጣለው፣ ከየት መጣ? ማን፣ ለምን ዓላማ ተማሪዎች ላይ ቦንብ መወርወር ፈለገ? ተማሪዎችን መጨረስ ከፈለገ ከተጠቀሰው በላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማን ከለከለው? የሚሉትና ተመሳሳይ ጥያቄዎች እየተሰነዘሩ ነው። ምን አልባትም የተቀነባበረ ድራማ ሊሆን አንደሚችልና ጉዳዩን ከብሄር ጋር የማገናኘት ዓላማ ያለው እንደሚሆንእየተሰማ ነው።
ኢህአዴግ በቴሌቪዥን ባሰራጨው የቅስቀሳ ፕሮግራም “ኦሮሚያ መሬት ተቆርሶ ለአዲስ አበባ እንደማይሰጥ፣ ክልሉ ካልፈቀደ የሚሆን ነገር እንደሌለ፣ ክልሉ ቢፈቅድ እንኳን እንደ ቀድሞው ልዩ ዞኑ ውስጥ ያሉት ወረዳዎች በኦሮሚያ ስር እንደሚተዳደሩ፣ የመሬት ቆረሳው ተራ የጠላት ወሬና ፕሮፓጋንዳ” እንደሆነ አቶ ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ የተለያዩ ሃላፊዎች ሲናገሩ አሰምቷል።
በዚሁ የፕሮፓጋንዳ ስርጭት “የክልሎች ማንዴት በህገመንግሰት የታሰረ ዋስትና አለው” በማለት የኦህዴድ ሰዎች ሲናገሩ ታይተዋል። ስርጭቱ አዲስ አበባና የልዩ ዞኑ ከተሞች በተቀናጀ ልማት ተሳስረው “ሲያብቡ” የሚያሳይ ዲዛይን በተደጋጋሚ በማቅረብ “ለዚህ ልማት እንረባረብ” የሚል ጥሪ አሰምቷል።
ቪኦኤና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንደዘገቡት የኦሮሚያ ፌዴራል ኮንግረንስ ድርጊቱን ክፉኛ መቃወሙንና ለደረሰው የህይወት ኪሳራ ኢህአዴግ ተጠያቂ አድርጓል። በልማት ስም ከድሃ አርሶ አደሮች ላይ የሚወሰደው መሬት “የመሬት ቅርምት” ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል። ክልሎች ህገ መንግስታዊ መብትም ሳይሸራረፍ እንዲከበር አሳስበዋል።
dire dawa universityበተያያዘ ዜና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በሚወጡ ሰልፈኞች ላይ ፍጹም የሃይል ርምጃ እንዲወስዱ የታዘዙ የጸጥታ ሃይሎች ርምጃቸውን እንዲያለዝቡ መታዘዙ ታውቃል። በተወሰደው የሃይል ርምጃ ህዝብ ክፉኛ በመቆጣቱ የሚወሰዱ ርምጃዎች እንዲላዘቡ መታዘዙን ተከትሎ በዛሬው እለት አንዳንድ ከተሞች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸው በሰላም መበተናቸውቸው ሰምቷል። ቪኦኤ እንዳሰማው የድምጽ መረጃ “የነፍጠኞች ሃውልት ይፍረስ” የሚለው ጥያቄ አሁንም እየተስተጋባ ነው።
የኦፌኮው አቶ ገብሩ ገ/ማርያም እንዳሉት አማራውንና ኦሮሞውን ለማጫረስ እየተከናወነ ያለ ሴራ አለ። ለረዥም ዓመታት አብሮ የኖረን ህዝብ ለማናከስ የሚደረገውን ሴራ ድርጅታቸው እንደማይቀበለውም አመላክተዋል። ከዚሁ ነፍጠኛን ከማውገዝ ጋር በተያያዘ “የአዲስ አበባን መስፋፋትና ነፍጠኛነትን ምን አገናኛቸው?” በማለት የሚጠይቁ፣ “ያረጀውን የነፍጥ ታሪክ ከማውራት አሁን ነፍጥ አንስቶ ጥቃት እየፈጸመ ስላለው ህወሃት የሚባለው የአንጋች ቡድን መነጋገር አይሻልም ወይ” ሲሉ ይደመጣሉ። (ፎቶዎቹ ከፌስቡክ የተወሰዱ ናቸው – የየትኛውም ኢትዮጵያዊት እናት ለቅሶ የሁሉም መሆኑን እንዲያሳይ የተጠቀምንበት ነው)
 የጎልጉል

No comments:

Post a Comment