Sunday, May 25, 2014

የመጨረሻዉ ካርድ

May 25/2014

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ያለፈችበትን የግፍና የመከራ ዉጣ ዉረድ ወደ ኋላ መለስ ብሎ መመለክት መፈጠርን የሚያስጠላና ልብን የሚያደርቅ እራሱን የቻለ ሌላ በጭንቅና በመከራ የተሞላ ዉጣ ዉረድ ነዉና አለመሞከሩ ይመረጣል። ሆኖም አገራችንን ከዚህ ሳትወድ በግድ እጇን ታስራ ከገባችበት የጥፋት ቁልቁለትና የመከራ አዘቅት ዉስጥ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ጎትቶ ለማዉጣት የግድ እዘህ ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ እንዴት ገባች ብሎ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋልና ወደድንም ጠላን የሃያ ሦስቱን አመት ጉዟችንን ወደ ኋላ ዞር ብለን በጥሞና ማጤኑ አማራጭ የሌለዉ መንገድ ነዉ። የወያኔ ዘረኞች ፋሺስቱን ደርግ ጣልን ይበሉ፤ በ99.6 በመቶ ድምጽ ተመርጥን ይበሉ ወይም እድገት አመጣን ይበሉ የእነሱ ፍላጎት ምን ግዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ መግዛት ነዉ እንጂ ህዝብን በጨዋነት ማስተዳደር አይደለም። አንድን ህዝብ ረግጦ ለመግዛት የሚያስፈልገዉ ደግሞ ጠመንጃና ባዶ ጭንቅላት ብቻ ነዉ፤ ጠመንጃና ባዶ ጭንቅላት በገፍ የሚገኝበት ድርጅት ነዉና ወያኔ ደግሞ በዚህ በፍጹም አይታማም። የወያኔ ዘረኞች ፍላጎት የኢትዮጵያን ህዝብ ከጣሊያን ፋሺስቶች ባልተለየ መንገድ እየረገጡ መግዛት ቢሆንም አንድን ህዝብ ዝንተ አለም ረግጦ መግዛት አንደማይቻል በሚገባ ያዉቃሉ፤ ለዚህ ነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ኃይሉን እነሱ ላይ ለማሳረፍ በቆረጠ ቁጥር ህዝብን ከህዝብ የሚለያይና የሚያራርቅ ካርዳቸዉን እየመዘዙ ጸረ ህዝብና ጸረ አገር ጨዋታቸዉን የሚጫወቱት። በእርግጥም ወያኔዎች በስልጣን በቆዩባቸዉ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት የተለያዪ ካርዶችን መዝዘዋል – ፌዴራሊዝም እያሉ በፌዝራሊዝም ቀልደዉብናል፤ እድገትና ልማት እያሉ ጠብ ያለዉን ሁሉ እነሱ እራሳቸዉ እየዋጡ ሌሎቻችንን የበይ ተመልካቾች አድርገዉናል፤ በጎሳ ከፋፍለዉናል፤ በዘር አጥር አጥረዉናል። ዛሬ ደግሞ ለእነዚህ ተራ በተራ ለመዘዟቸዉ የክፋት ካርዶች አልታለልም ያለዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ካዝናቸዉ ዉስጥ የቀረችዉን የመጨረሻ ካርድ መዝዘዉ በጎሳና በዘር ከመለያየት አልፈዉ በዘር ለማጋጨትና ደም ለማፋሰስ ጉድ ጉድ እያሉ ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ማንም ኃይል በምርጫ ሥልጣን ያዝኩ ብሎ አፉን ሞልቶ ለመናገር ኦሮሚያና አማራ ክልል ዉስጥ ምርጫዉን ጉልህ በሆነ ብልጫ ማሸነፍ አለበት፤ ወይም አማራና ኦሮሚያ ዉስጥ ተሸንፎ ፓርላማ ዉስጥ አብዛኛዉን ወንበር ተቆጣጥሮ መንግስት መመስረት አይቻልም። ወያኔ ዛሬ ያንን የእንቅልፋሞች ፓርላማዉ ተቆጣጥሮ መንግስት ነኝ ብሎ የሚፏልለዉ ሁለቱን የአገራችንን ግዙፍ ብሄረሰቦች ለያይቶና አንዱ ሌላዉን በጥርጣሬ አይን እንዲመለከት አድርጎ ነዉ እንጂ ወያኔ በየቀኑ የሚያስራቸዉ፤ የሚደበድባቸዉ፤የሚያሳድዳቸዉና የሚገድላቸዉ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በፍላጎታቸዉ መርጠዉታማ አይደለም። ወያኔ ዛሬ ከሚታይበት የፖለቲካ ኪሳራና ህዝባዊ መተፋት አንጻር እንደቀድሞዉ ኦሮሞንና አማራን በመከፋፈልና በመለያየት ብቻ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል ስለተረዳ እነዚህ ሁለት የአገራችን ግዙፍ ብሄረሰቦች እርስ በርሳቸዉ ተጋጭተዉ እንዲተላለቁ የሚቻለዉን ሁሉ እያደረገ ነዉ። ወይም ቀለል ባለ አማርኛ ወያኔ ከጫካ ይዞት የመጣዉን የመጨረሻ ካርድ መዝዞ አገራችንን በቀላሉ ወደ ማትወጣዉ የዘርና የጎሳ ግጭት ዉስጥ ለመክተት ቁጭ ብድግ እያለ ነዉ።
ወያኔ የመሬት ባለቤትነትን ጉዳይ ህገ መንግስቱ ዉስጥ ሸንቁሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሬት የግል ንብረት የሚሆነዉ በእኔ መቃብር ላይ ነዉ ያለዉ አለምክንያት አይደለም። ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሬት የህዝብና የመንግስት ነዉ ይበል እንጂ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ትክክለኛዉ የመሬት ባለቤት ህዝብም መንግስትም ሳይሆን ህወሀት ወይም ወያኔ ነዉ። ይህንን ወያኔ የሚባል የዘረኞች ስብስብ ባስቸኳይ ጠራርገን በገዛ አፉ እንደተናገረዉ በወያኔ መቃብር ላይ የአገራችንን የተዛባና ጎታች የመሬት ይዞታ በፍጥነት ካልቀየርን ሁላችንም የወያኔ ገባር መሆናችን የማይቀር ነዉ:። ዛሬ ወደድንም ጠላን አገራችን ዉስጥ ልክ እንደፊዉዳሉ ዘመን መሬት እንደ ስጦታ ለዘመድና ለቤተዘመድ የሚሰጥ ደሃዉንና ሀብታሙን የሚለይ የመጨቆኛ መሳሪያ ነዉ። መሬት መብት መርገጫ ነዉ፤ መሬት አፍ ማስዘግያ ነዉ፤ መሬት ማማለያ መሳሪያ ነዉ፤ መሬት የማይወዱትናን የኛ አይደለም የሚሉትን ማግለያና መድረሻ ማሳጫ ነዉ። ባጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሬት የወያኔ ቂም በቀል መወጫ አይነተኛ መሳሪያ ነዉ። ወያኔ እኔን አይደግፈኝም ከሚለዉ ከማንም ሰዉ መሬት ቀምቶ ላሰኘዉ ሰዉ መስጠት ይችላል። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ብዙ መጓዝ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ አዳዲሶቹን የከተማ ቦታና ሰፋፊ የእርሻ መሬት ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ መመልከቱ ይበቃል።
በቅርቡ አምቦ ዉስጥ በግፍ የተጨፈጨፉት የኦሮሞ ተማሪዎች እንደዚህ አይነቱን አግላይ የሆነ የወያኔ የመሬት ፖሊሲ የተቃወሙ ተማሪዎች ናቸዉ። ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በልማት ስም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሞ ገበሬዎችን እያፈናቀለ መሬቱን ለራሱ ወገኖች መስጠቱን በመቃወም አምቦ፤ ጅማ፤ ወለጋ፤ አዳማና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚማሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ወያኔንና ደጋፊዎቹን ክፉኛ ያስደነገጠ ከፍተኛ የተቃዉሞ ሰልፍ ያደረጉትና ምትክ የሌለዉን ህይወታቸዉን የገበሩት ይህ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ የወያኔ የመሬት ፖሊሲ ስለገባቸዉ ነዉ። በዚህ በተለያዩ ቦታዎች በተካሄደዉ የተቃዉሞ ስልፍ ላይ የኦሮሞ ተማሪዎች ያነገቡት አንድ ጥየቄ ብቻ ነበር፤ እሱም ህዝብን ያላካተተ ልማት የለምና ወላጆቻችንን እያፈናቀላችሁ መሬታችንን መከፋፈል አቁሙ የሚል ጥያቄ ነበር። ለዚህ የኦሮሞ ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ ላቀረቡት ጥያቄ ወያኔ የሰጠዉ መልስ እንደተለመደዉ በአግአዚ ነብሰ ገዳዮች ወጣቶችን በየአደባባዩ በጥይት መጨፍጨፍ ነበር – አዎ! የወያኔ ስራ ጥያቄ ሲጠይቁት መግደል፤ ምርጫ ሲሸነፍ መግደል፤ ለምን ጻፍክ ብሎ መግደል፤ ለምን ተናገርክ ብሎ መግደል ነዉ።
ወያኔ በሃያ ሦስት አመታት የስልጣን ዘመኑ እንደ ዘንድሮ ተገፍቶ ተገፍቶ ዳር የደረሰበትና እንደ ዘንድሮ መዉጪያና መግቢያዉ ጠፍቶበት አያዉቅም። እኛ ብናምንም ባናምንም ወይም ብናዉቅም ባናዉቅም ወያኔ የተከበበ አዉሬ ሆኗል፤ ግን ከዚህ በፊት አንዳደረገዉ ሁሉ የከበቡት ኃይሎች ፊት ለፊት የሚተያዩና አብረዉ የሚሰሩ ኃይሎች ባለመሆናቸዉ ወያኔ ከበባዉን ጥሶ ለመዉጣት እየሞከረ ነዉ። ከላይ ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርነዉ ወያኔ እንደ ዘንድሮ ተዋክቦና እንደዘንድሮ የመጨረሻዉ ሸትቶት አያዉቅም። ሆኖም እንድ መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር ወያኔ ከገጠመዉ ህዝባዊ ቁጣ ለማምለጥና ስልጣን እንደጨበጠ ለመቀጠል እንደዛሬ የዘር መለያየትና ማጋጨት ሴራዉን ተግባራዊ ያደረገበት ግዜም የለም። እዉነቱን ለመናገር በአንድ በኩል ምንም ጥርጥር በሌለዉ መልኩ ወያኔ ተከብቦ ህልዉናዉ አደጋ ላይ ወድቋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ ከዚህ ተገፍቶ ከገባበት አደጋ ለመዳን አገራችን ዉስጥ ዘርና ጎሳ ለይቶ ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያባላ የእርስ በርስ ጦርነት ለመቀስቀስ ዝግጅቱን ጨርሷል።
የኦሮሞ ተማሪዎች ባካሄዱት የተቃዉሞ ሠልፍ ዉስጥ አልፎ አልፎ የተሰማዉ “የሚኒልክ ሃዉልት ይፍረስ” የሚለዉ ጩኸትና ጊምቢና በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች አማራ ይዉጣልን የሚለዉ ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ ሳይሆን ወያኔ ሆን ብሎ ከትኩቶ ባሳደጋቸዉ ካድሬዎቹ አማካይነት ህዝብ ዉስጥ ይዞት የገባዉ የእርስ በርስ እልቂት መቀስቀሻ ጥያቄ ነዉ። ሁለቱ ዝሆኖች ሲጣሉ የሚሰቃየዉ ሳሩ ነዉ እንደሚባለዉ ወያኔ የአማራንና የኦሮሞን ብሄረሰቦች በማጋጨት እነዚህ ሁለት የአገራችን ብሄረሰቦች እርስ በርስ ሲፋጩና የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሰቃይ እሱ የስልጣን ዘመኑን ማራዘምና የዘረፋ ተልዕኮዉን እንደገና ማደስ ይፈልጋል። ይህ “እኔ ከሞትኩ ስርዶ አይብቀል” አይነቱ የወያኔ ሴራ ለወደፊት ሊከናወን በዕቅድ የተያዘ ጥንስስ ሳይሆን ከአመታት በፊት ጫካ ዉስጥ ታቅዶ ዛሬ ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለ የወያኔ ተንኮል ነዉ።
ወያኔ የኦሮሞና የአማራ ብሄረሰቦች እጅ ለእጅ ተያይዘዉ ከተነሱበት የስልጣን ዘመኑ በቀኖች እንደሚቆጠር በሚገባ ያዉቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ አብዛኛዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ያቀፉት ሁለት ግዙፍ ብሄረሰቦች በመካላቸዉ ስምምነት ከሌለና አንዱ ሌላዉ ላይ በቂም በቀል ከተነሳ ማንም በቀላሉ ከስልጣን እንደማያባርረዉ ጠንቅቆ ያዉቃል፤ ለዚህም ነዉ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ እንዚህ ሁለት ብሄረሰቦች እንዲጋጩ ክብሪት የሚጭረዉ። አምቦ፤ ጊምቢ፤ አኖሌና ምስራቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደጋጋሚ የተጫረዉ የዘር ግጭት መቀስቀሻ እሳት ወያኔ አማራዉንና ኦሮሞዉን ለማጋጨት ሆን ብሎ የለኮሰዉ እሳት ነዉ። ዛሬ የኦሮሞን ተወላጆች ስልጣን መድረክ አካባቢ እንዳይቀርቡ አድርጎ የኦሮሚያን መሬትና የመሬት ላይና ዉስጥ ኃብት በገፍ የሚዘርፈዉና የአገሪቱን እስር ቤቶች በኦሮሞ ተወላጆች የሞላዉ ወያኔ ነዉ እንጂ ግዑዙና የማይናገረዉ የምኒልክ ኃዉልት አይደለም። ኦህዴድ የሚባል ተለጣፊ ባቡር ሰርቶ የኦሮሞን ህዝብ የሚገድለዉና በገዛ መሬቱ ላይ ባይተዋር ያደረገዉ ወያኔ ነዉ እንጂ ከመቶ አመት በፊት ሞተዉ የተበሩት ዳግማዊ ምኒልክ አይደሉም። ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ ከአማራዉና ከሌሎቹ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ሆኖ ማፍረስ ያለበት የምኒልክን ኃዉልት ሳይሆን ወያኔንና ወያኔ የፈጠረዉን ዘረኛ ስርዐት ነዉ።
ባለፈዉ ወር አምቦ ላይ ያየነዉ የአግአዚ ጭፍጨፋ ወያኔ ከደገሰልን ጥፋት ጋት ሲነፃፀር እጅግ በጣም ትንሽ ነዉ፤ ወያኔ እያንዳንዳችንን በተናጠል በመታና በገደለ ቁጥር ቁጣችንን የምንገልጸዉና የምንከላከለዉ በተናጠል ከሆነ ወያኔ እያንዳንዳችንን በተናጠል እየገደለም ሆነ እያሰረ ጭጭ የማስደረግ ኃይል አለዉ። ይብዛም ይነስ የወያኔን ጥቃት ተቋቁመን ወያኔን ማስወገድ የምንችለዉ በጋራ አንድ ሆነን ስንቆም ብቻ ነዉ። እያንዳንዳችን ሺ ጠመንጃ ይዘን ወያኔን በተናጠል ብንገጥመዉ አናሸንፈዉም፤ ሁላችንም ተባብረን እንደ አንድ ሰዉ መቆም ከቻልን ግን ወያኔን ለማሸነፍ ጠመንጃም አያስፈልገንም። ስለዚህ ዛሬ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን የትብብር ጥያቄ የትግል አማራጭ ሳይሆን በፍጹም ልናልፈዉ የማይገባን የህልዉና ጥያቄ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዉያን – ኑ አብረን እንታገል እያልን የትግል ጥሪ ስናስተላልፍ ወያኔ ደግሞ አገር እያፈረሰና ህዝብ እየገደለ ከሃያ አመት በላይ ተጉዘን ዛሬ ላይ ደርሰናል። የእኛ ጩኸት ከሃያ አመት በኋላ ዛሬም እንተባበር የሚል ነዉ፤ ሃያ አመት ሙሉ አገር ሲንድና ህዝብ ሲገድል የከረመዉ ወያኔ ግን ዛሬ የተቃወመዉን ሁሉ ቢቻል ለመግደል አለዚያም ለማሰር እየተንቀሳቀሰ ነዉ። እንደ አገርና እንደ ህዝብ በአንድነታችን ፀንተን ለመቀጠል ካሁን በኋላ ያለን ብቸኛ አማራጭ ጥቂቶች ታስረን፤ ጥቂቶች ተሰድደን ጥቂቶች ደግሞ ሞተን ወያኔን ማስወገድ ወይም በተናተል ሁላችንም ተራ በተራ መሞት ነዉ።
አባቶቻችን ያስተማሩንና እኛም በነጋ በጠባ እንደ ዳዊት የምንደግመዉ ይህንኑ ለእናት አገሬ እሞታለሁ የሚለዉን የአባቶቻችንን ትምህርት ነዉ።
ወገን ለኢትዮጵያ መሞት ካለብን ቀኑ ዛሬ ነዉ . . . . ኑና ለእዉነት ሞተን በህይወት እንኑር!

No comments:

Post a Comment