Sunday, May 4, 2014

ግብፅ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ የሚከታተል ሳተላይት ማምጠቋን ገለፀች


May 3/2014

ግብጽ 43 ሚሊዮን ዶላር ያወጣችበትንና የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የግንባታ ሂደት በአየር ላይ ሆኖ እየተከታተለ መረጃ የሚሰጣትን ወታደራዊ ሳተላይት ከሁለት ሳምንት በፊት ማምጠቋን በይፋ እንደገለፀች   አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡

ኢጂሳት የሚል ስያሜ የተሰጠው ሳተላይቱ፤ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቁመት፣ ውሃ የመያዝ አቅምና የሚለቀውን የውሃ መጠን የተመለከቱ መረጃዎችን እየተከታተለ የሚያቀርብ እንደሆነ የገለጹት የግብጽ ብሄራዊ የሪሞት ሴንሲንግና ስፔስ ሳይንስስ ባለስልጣን ምክትል ፕሬዚደንት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ሳተላይቱ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚከናወንበት አካባቢ በተጨማሪ፣ የአባይ ወንዝ በሚፈስባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በማተኮር፣ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ጠቃሚ ፎቶግራፎችን እያነሳ እንደሚልክ  ሰሞኑን በካይሮ በተካሄደ ሴሚናር ላይ ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ወራት ከሚቆይ የሙከራ ጊዜ በኋላ፣ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ መደበኛ ስራውን ይጀምራል የተባለው  ሳተላይቱ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከታተለ ለግብጽ ባለስልጣናት መረጃ ከማቀበል ባለፈ፤ የኮንጎ ወንዝን ተፋሰስ በመከተል በሚያነሳቸው ፎቶግራፎች፣ ወንዙን ከአባይ ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተረቀቀውን የፕሮጀክት ሃሳብ ውጤታማነት በተመለከተ የራሱን ፍተሻ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የግብጽ መንግስት ሳተላይቱ ከሚያቀርባቸው መረጃዎች የሚያገኘው ውጤት፣ ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ዙሪያ የጀመረው ክርክር ተጠናክሮ እንዲገፋ እንደሚያደርገው ያምናል ያሉት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ግድቡን ከታለመለት የሃይል ማመንጨት ስራ ውጭ ለማዋል በኢትዮጵያ በኩል ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ቢደረጉና ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ግልግል የሚያመራ ከሆነም፣ የግብጽ መንግስት ይሄንኑ የሳተላይት መረጃ ለክርክሩ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጠቀምበት አል አህራም ለተባለው  ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

አል አረቢያ ድረ-ገጽ በበኩሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የምታነሳቸውን ቅሬታዎች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማቅረብ ከወሰነች፣ ኢትዮጵያ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ባለፈው ሳምንት መናገራቸውን ዘግቧል፡፡

የግድቡ መገንባት የአባይን ወንዝ የውሃ መጠን በመቀነስ ተጎጂ ያደርገናል በሚል ተቃውሞአቸውን በተደጋጋሚ የገለፁት የግብጽ ባለስልጣናት፣ ሳተላይቱ የሚሰጣቸውን መረጃ መሰረት በማድረግ የሚደርሱበት ውጤት፣ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ክርክር ይዘውት የቆዩትን አቋም እንደሚያጠናክርላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡ የግብጽን ሳተላይት ማምጠቅ በተመለከተ፣ አንዳንድ ድረገጾች ቀደም ብለው መረጃ ያወጡ ቢሆንም፣ የአገሪቱ መንግስት ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ ሲሰጥና ድርጊቱን ሲያምን የአሁኑ የመጀመሪያው  ነው፡፡

No comments:

Post a Comment