May 13, 2014
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለመከታተል ኢትዮጵያዊው የህግ ባለሞያ ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ባለፈው ሳምንት ወደ ጄኔቭ-ስዊዘርላንድ ተጉዟል።
ሼክስፒር ፈይሳ የረዳት ፓይለቱን ጉዳይ ከሚኖርበት ከሲያትል ከተማ በቅርብ ሲከታተል ቆይቶ ነው ወደ ጄኔቭ ያመራው። ጄኔቭ እንደደረሰም የሃይለመድህን አበራን ጠበቃና ጉዳዩን ከሚከታተሉ አካላት ጋር በስፋት ተወያይቷል። በተለይ ከረዳት ፓይለቱ ጠበቃ ጋር ረጅም ሰዓታት በመውሰድ በበርካታ የህግና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በጥልቅ ተነጋግሯል።
ረዳት ፓይለቱ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ኢትዮጵያዊ የህግና እንዳስፈለጊነቱ የህክምና ባለሞያዎች ጋር እንዲገናኝም ዶ/ር ሼክስፒር ምክር ሰጥቷል።
የረዳት ፓይለቱ ጠበቃ የስዊስ መንግስት ሃይለመድህን አበራን ለኢትዮጵያ አሳልፎ እንደማይሰጥና ግዚያዊ የስደት ፈቃድ እንዲሰጠው ውሳኔ መተላለፉን ያረጋገጠ ሲሆን – ጉዳዩ በቅርብ ጊዜ በሚሰየመው ግልጽ ችሎት እልባት እንደሚያገኝ አመላክቷል።
የሃይለመድህን አበራን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በአቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራ ከፍተኛ የኢህአዴግ ቡድን ጄኔቭ፣ ከርሞ ጥያቄው በስዊዘርላንድ መንግስት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ቡድኑ የስዊስ ፌዴሬሽን የህግ አካላትን ለማሳመን ካቀረበው ምክንያት ዋነኛው፣ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአእምሮ በሽተኛ መሆኑን እና ይህንንም የራሱ ቤተሰብ አባላት እንዳረጋገጡላቸው ገልጸዋል። የስዊዝ መንግስት ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። ለዚህም የሰጠው ዋነኛ ምክንያት፤ የሞት ፍርድን ተግባራዊ ለሚያደርግ መንግስት ማንንም አሳልፌ አልሰጥም የሚል ሲሆን ይህ ባይሆንም፣ በስዊዘርላንድ እና በኢትዮጵያ መሃል ተጠርጣሪ እስረኛን የማስመለስ ውል የለም ብለዋል።
ረዳት ፓይለቱ ለግዜው ሰው ማግኘት እንደማይፈልግ የተነገረ ሲሆን: ወንድሙ ዶ/ር እንዳላማው አበራ እና በጀርመን የምትኖር እህቱ ሃይማኖት አበራ ጄኔቭ ድረስ በመሄድ ሃይለመድህን አበራን ከሚገኝበት እስር ቤት ጎብኝተውታል።
ወጣት ሃይለመድህን አበራ ባለፈው የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ቦይንግ 767 አግቶ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ላይ በማሳረፍ እዚያው የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁ ይታወሳል። የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ልዩ ክስተት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታና የአስተዳደር በደል አደባባይ በማውጣቱ የገዢው ፓርቲ አባላትን እጅግ እንዳበሳጨ ይነገራል።
አንዳንድ መገናኘ ብዙሃን እንደገለጹት የአጎቱ ድንገተኛ ህልፈት ርዳት ፓይለቱን አስቆጥቶት ነበር። የሃይለመድህን አበራ አጎት፤ ዶ/ር እምሩ ሥዩም ህይወት በድንገት ማለፍ ለብዙዎች ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ዶ/ር እምሩ ሥዩም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ።
በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቱ ፓይለት ሃይለመድህን አበራን መደገፋቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን በረዳት ፓይለቱ ስም የተከፈቱ ድረ-ገጾች እና የፌስቡክ መድረኮች ላይ አሁንም ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ በረዳቱ ጉዳይ ላይ ማንኛውንም ትብብር ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን የስዊስ ጠበቆችም በዚህ ከክፍያ ነጸ የሆነ ትብብሩ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment