May 9/2014
[ጭንጋፍ ወይስ ልጅ? ምስክርነት!]
የአንድን ድርጅት ማንነቱን ከማቅረብ በፊት ቀደም ብሎ የተፈጸመውን ስህተት፣ ቀጥሎም ኢህአፓን ለማጥፋት በህወሓት እና በሻእቢያ የደረሰበትን ጥቃት አጠር ባለ መልኩ ማቅረብ አስፈላጊ ይሆናል።
የስትራተጂ ስህተት ለከባድ ወድቀት ይዳርጋል
ኢህአፓ ትግሉን የጀመረው ገና በ1960 መጀመሪያ ነበር። አብዮቱ እየተቀጣጠለ ሃገር አቀፍ ሆነ። ዘውዳዊ ስርዓት ወድቆ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርእዮተ ዓለም የሚመራ ሶሻሊዝም የኢትዮጵያ ስርአት እንዲሆን ነበር። ይህ ግራ አክራሪ ስታሊኒዝም በቀ. ኃ. ሥ. ዩኒቨርሲቲ ይማሩ በነበሩ የተሰባሰበ ቡድን፣ የወቅቱ አብዮተኞች ተገቢውን መልክ የያዘ አደረጃጀት ያልነበረው፣ አብዮተኛ የሚል ስም በማግኘታቸው ብቻ “ዲሞክራሲያ” ተብሎ የሚታወቀውን የኢህአፓ ልሳን በየሳምንቱ በመበተን አሁን ኢትዮጵያ የደረሰባትና እየደረሰባት ያለው ከባድ ችግር የከፈተው እነ ዋለልኝ መኮንን እና የኢህአፓ ግብረአበሮቹ የስታሊን ደቀ መዛሙርት ኢትዮጵያን አደጋ ወስጥ ጣሏት። በዚህ ወቅት ሰፊውን ትኩረት የሰጡት፤
- በኤርትራ ጥቅያቄ ላይ ኢህአፓ ያለው አቋም ኤርትራ ከዚህ ቅኝ አገዛዝ ነፃ በመሆን ተገንጥላ ነፃ መንግሥት ማቋቋም ሙሉ መብቷ መሆኑን ያምናል፤
- ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ወህኒ ቤት እንደመሆኗ የኢህአፓ አቋም በዚሁ ጥያቄ ላይ ርቱእና ግልጽ ሲሆን፣ ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው በመወሰን እስከ መገንጠል መብታቸው ያልተገደበ ነው ይላል።
ይህ ትንታኔ ማንም ኢትዮጵያዊ በተጨማሪ ለማረጋገጥ ክፈለገ “ዲሞክራሲያ” ቅጽ 8 ቁጥር 1፣ የካቲት 23 ቀን 1973 የታተመውን ሙሉ ሃሳቡን በድጋሚ ጽፎታል፣ የቃላት ለውጥ በትንሹ ቢኖርበትም። ይህንን ጽሑፍ ለማግኘት EPRP በሚለው ድረገጽ በመግባት የዲሞክራሲያን እትም ከ1961 እስከ ዛሬ የሚለውን ፈልጋችሁ አንብቡ። ይህ ጽሑፍ የሚያሳዝነው ኢህአፓ አሲምባ እንደገባ ታጋዮቹ በፈጠሩት ጫና በሻእቢያ 1ኛ ጉባኤ 1969 መጨረሻ የአቋም ለውጥ በማድረግ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት፤ የኤርትራ ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ በመሆኑ ትግሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ስለሆነ ኤርትራም የዚሁ አካል እንጂ ቅኝ ተገዢ አይደለችም በማለት በጉባኤው የሰጠው ውሳኔ ቅጥረኛው ህወሓት ታህሳስ 1972 የኢህአፓ ተዋጊ ክንፍ ሰራዊት ከባድ መስዋእትነት ክፍሎ በወያኔ ተደመሰሰ። በውጭ ሃገር የሚኖሩ የኢህአፓ አመራር በየካቲ 1973 በዲሞክራሲያ ልሳን ያወጡት ጽሑፍ የኢህአፓው ተዋጊ ክንፍ ኢህአሠ ታጋይ ለናት ሃገሩ ኢትዮጵያ የከፈለውን መስዋእትነት ውድቅ ለማድረግ የታቀደ ነው፤ ለምን?
ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ነጥቦች የኢህፓ አመራር በዲሞክራሲያ ልሳኑ ደጋግሞ በመዘርዘር ጠባቦችና ጸረ ኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ሃይሎች እንዲፈጠሩ አደረገ።
ጠባብና ዘረኛው ጸረ-ኢትዮጵያ ሉአላዊነት፣ ጸረ-ሕዝብና አንድነት ማገብት – ማህበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ – ተሓህት የዛሬው ህወሓት ሊፈጠር ቻለ። ይህ የኢህአፓ ርእዮተ ዓለምና አቋም ኢትዮጵያና ሕዝቧን ለዛሬው ክፉ አደጋ ዳርጓት አልፏል።
የሻእብያው የበህር ልጅና በአምሳያው የተፈጠረው ህወሓት አረጋዊ በርሄ በዋና ፈላጭ ቆራጭነት እስክ 1977 መጨረሻ ሲመራው የነበረ ቡድን ተሰብስቦ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሳ፣ በቋንቋ እስከ መገንጠል ሃገርና ሕዝብን ለመበታተን ፕሮግራሙን አስተካክሎና ጽፎ በማዘጋጀት ደደቢት በረሃ ወረደ። ተሓህት፤ የዛሬው ህወሓት – ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ – ባረቀቀውና ባዘጋጀው ፕሮግራም እነሆ ዛሬ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት መከራና ችግር፤ ፈርሳ፤ ሕዝብ ተበታትኖ እየተገደለ ለስቃይና መከራ ተዳረገ። ኢትዮጵያን በህወሓት ፋሽስት ስርዓት ደም እያለቀሰች ትገኛለች። የወላድ መሃን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽኑ ኢትዮጵያዊነቱን ህወሓት በሃይል ነጥቆ በጎሳህ እመን ብሎታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓትን ዓላማ አንቀበልም፣ በኢትዮጵያዊነታችን እናምናለን በማለት በግለጽ እየተናገረ ይገኛል።
የኢህአፓ አመራር በኢትዮጵያ ፈጥሮት ያለፈው ግዙፍ ስህተቶች በርካታ ስለሆኑ ከላይ የጠቀስኩት መሰረታዊ ስህተት ሆኖ በራሱም ላይ ድክመቶቹ ለጥቃት ሊዳርገው ቻለ። በወቅቱ የተሰባሰቡት አመራር ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ በቅጡ ያልተገነዙቡ ጭፍን በሆነ አመለካከትበማርክሲዝም ሌሊኒኒዝም አብዮተኝነት ደንዝዘው መጥፎውን እና ደጉን ማየት የተሳናቸው ነበሩ። ከስህተታቸው መሃከል ሁለቱን አስፈላጊ ነገሮች እንመልከት።
- ማእከላዊ አመራር (central leadership) የዚህ አይነት የአመራር ስርአት ለአንድ ድርጅት ወሳኝ ነው። በወቅቱ ኢህአፓ ሙሉ እንቅስቃሴው በከተማ ውስጥ ስለነበር በምስጢር ቦታ አባላቱን አሰባስቦ በኮንፈረንስ ደረጃ ጊዜያዊ ማእከላዊ አመራር ለመስጠት ይችሉ ነበር። በዚሁ ጊዜ በአባላቱ የተመረጠው ማእከላዊ ኮሚቴም ተሰብስበው ድርጅቱን በሙሉ ሃላፊነት የሚመሩ ብቃት ያላቸው ሥራ አስፈዳሚ “ፖሊት ቢሮ” ይመርጣሉ። ከነዚህ ብቁ ናቸው የተባሉትን፣ የድርጅቱ ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር፤ ካስፈለገም በሶስተኛ ዋና ጸሃፊ መርጠው የቀሩትም ማ/ኮሚቴ በሥራ አስፈፋሚው በየቦታው መድቦ ያሰራቸው ነበር። ግን በወቅሩ የነበሩት የኢህአፓ አመራር የዚህ አይነት የትግል ጉዞ አይፈልጉም፤ አልተቀበሉትም። ይህ ኢህአፓን ለውድቀት ዳረገው።
- የተመረጡት የሥራ አሰፈጻሚ አባላት የድርጅቱ መሰሶ የሆኑትን ክፍሎች ይቆጣጠራል፣ ይመራል። እነዚህም፤ ወታደራዊ፣ ፕሮፓጋንዳ ቢሮ፣ ኢኮኖሚ ቢሮ፣ የገጠር የሕዝብ ግንኙነት፣ የከተማ ግንኙነት፣ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሲሆኑ፣ እነዚህን በበላይነት የሚመራው የሥራ አስፈጻሚው ነው። እንደ አስፈላጊነቱም ከማ/ኮምቴው ብቃት ያላቸው ታጋዮች በየዘርፉ ይመደባል። ትእዛዝ ከላይ ወደ ታች ሲተላለፍ ተግባራዊነቱን በመከታተል ከታች ወደ ላይ ይላካሉ። ይህ የድረጅቱ ጥንካሬና ብቃት ሆኖ ያድጋል። በጉባኤው ያልተመረጡት የኢህአፖ አመራር ይህን አይቀበሉትም። ይህን ባለመቀበሉ ኢህአፓ ለውድቀት ተዳረገ።
- ወታደራዊ እስትራተጂን በተመለከተ ሥራው ሁሉ የሚጠናቀቀው በሥራ አስፈጻሚው በኩል ነው። ወታደራዊ ተግባራት የሳይንስ ጥበብና እውቀት ይጠይቃል። በውስጡ ብዙ ዘርፎች በስትራተጂ ደራጃ፣ በታክቲክ ወይም ስልት ደራጃ ያቀፈ አሰራርና አጠቃቀሙ ብልህነትና አስተዋይነትን ይፈልጋል። ስለሆነም የአንድ ድርጅት እንቅስቃሴ ተግባራዊ ይሆናል። ይህን የማይቀበል ድርጅት ደግሞ በቀጥታ ለሞትና ለውድቀት አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ይህን በወቅቱ የነበሩ የኢህአፓ አመራር ወታደራዊ ጥበብን በንቀት ይመለከቱት ስለነበር፣ የኢህአፓ ተዋጊ ክንፉ ኢህአሠ በቀላሉ በህወሓት እንዲጠቃ አደረገው። የኢህአፓ አመራር ከብቃት አነስተኛነት አልፎ በወታደራዊ ስትራቴጂ እምነቱ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ውድቀት አስከተለለት።
ሌላው ቀርቶ ኢህአፓ ከተማን ለቆ ለትጥቅ ትግል ኤርትራ በረሃ ገብቶ ከሻእቢያ እንደተጥጋ ጉባኤ ጠርቶ የነበሩትን ደካማ አመራር አሰወግዶ ብቃት ባላቸው ታግዮች መለወጥ ሲገባው አላደረገውም። በወቅቱ የነበሩ የኢህአፓ አመራር ጉባኤ መጥራትን አይፈልጉትም፣ የፈሩታል። ምክንያቱም፣
- የነበረው ደካማ አመራር ተወግዶ በብቁ ታጋዮች ስለሚተካ፣
- ኢህአፓ ሃብታም ድርጅት እንድመሆኑ እያላገጡ መብላትና መዝረፍ የለመዱ በመሆናቸው ጥቅማችው እንዳይነካ ስለፈለጉ ነው።
ኢህአፓ እንደ ዲሞክራሲ አብይ ጉዳይ የሚከተለው የክልል ነፃ አስተዳደር “Regional autonomy” ነበር። ይህ ደግሞ ማእከላዊ አመራርን የሚጻረር፣ ትእዛዝ ተቀባይ የሌለው፣ ደፈጣ ተዋጊ ሰራዊቱን ለክፉ አደጋ አሳልፎ የሚሰጥ አደገኛ መንገድ ነው። ድርጅቱም ስርዓት የለሽ “anarchy” እንቅስቃሴ በቀጥታ የሚዳርገው ነው።
ህወሓት፣ ኢህአፓን ለማጥቃት ሃይሉን ማጠናከር የጀመረበት ወቅት
ኢህአፓ በትግሉ ወቅት ህወሓት ጠላቴ ነው ብሎ አልፈረጀውም። ይልቁንስ በአንድ ግንባር ተስልፈን ሃገራችን ኢትዮጵያን አሁን ካለው የደርግ ስርዓት ነፃ አውጥተን ሕዝባዊ መንግሥት እንድንመሰረት በአንድነት እንሰለፍ ከማለት በስተቀር። ደጋግም ኢህአፓ ለህወሓት አመራር በመቅረብ ቢጠይቅም በህወሓት አመራር የተሰጠው ምላሽ “ከአባይ ኢትዮጵያ” ተስፋፊዋ ኢትዮጵያ ታጋይ የሆንከው ኢህአፓ ግንባር አንፈጥርም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አደረጉት። ትንሽ ቆየት ብሎም ኢህአፓ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ በስብሃት ነጋ የተፈረመ ደብዳቤ ተላከለት። ኢህአፓም ትግራይ ኢትዮጵያ ስለሆነች አንወጣም፤ እናንተም ሸዋ፣ ጎጃም ወዘተ ቤታችሁ ነው፤ በምትፈልጉበት ቦታ ለመንቀሳቀስ መብታችሁ ነው የሚል መልስ ሰጠ። ይህ በኢህአፓ የተሰጠው ምላሽ ትክክል ነው።
ኢህአፓ በህወሓት ላይ ምንም የመተናኮስ ሥራ አልሠራም። የህወሓት አመራር ግን በኢህአፓ ላይ ብዙ መተናኮልና በተናጠል ግደያ ጀምረዋል። ቀስ በቀስም ኢህአፓን ለመደመሰስ ዝግጅቱ እየተጠናከረ መጣ። ይህ ሲሆን የኢህአፓ አመራር በተለያዩ መንገዶች መረጃ ሲደርሳቸው መደረግ የነበረበትን ሥራ አልሠሩም። አሲምባ የነበሩ አመራር በየቀኑ የሚደርሳቸውን መረጃ በንቀት ይሁን ወይም በትእቢት ግምት አይሰጡትም ነበር።
የኢህአፓ ተዋጊ ሰራዊት ኢህአሠ የከፈለው ከባድ መስዋእትነት
የኢህአፓ ተዋጊ ሰራዊት ኢህአሠ “የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ሠራዊት” ተብሎ የሚታወቀው ነው። ኢህአሠ በተለያዩ የሃይል ምድብ ተመድቦ አንድ ሃይል ከ150 ታጋዮች በላይ እንደሆነም የህወሓት አመራር ሲናገሩ ነበር። ከ12-14 ሀይሎች ብዛት እንዳለውም ተናግረዋል። በወቅቱ የነበረው ትጥቁ ዘመናዊ ክላሽንኮፍ የታጠቀ በአንድ ሃይል፤ ሶስት ዘመናዊ መትረየስም የታጠቀ በመሆኑ የህወሓት አመራር አረጋግጠው ተናግረዋል።
ኢህአፓ ከተለያዩ ግዛቶች የተሰባሰበ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችውን አጠናቅቀው በኢትዮጵያ ወስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመማር ላይ የነበሩ ስለሆኑ ንቁና የተማረ ታጋይ ነበር። ብቁ የኢህአፓ አመራር ግን አላገኘም።
ህወሓት ኢህአፓን እና ተዋጊ ክንፉ ኢህአሠን ለማጥቃት ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ አሲምባ የነበሩ የኢህአፓ አመራር አስተማማኝ መረጃ ቢደርሳቸውም ተገቢውን ጥንቃቄ ባለመፈጸማቸው በታሪክና በሕግ የሚይስጠይቃቸው ስህተት ፈጽመዋል።
- ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው ኢህአፓ በማእከላዊ አመራር ያልተጀመረ፣ በወቅቱ የነበሩ አመራር በመሰላችው መንገድ የሚጓዙ፣ ስርዓት የለሽ ነበሩ። እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመከላከል አመራሩ ተሰብስቦ ጊዜያዊ አመራር መርጦ ቢሰይም ሁሉንም እየተቆጣጠረ ድርጅቱን እና ታጋዩን ከጥቃት ያድኑት ነበር። አልተደረገም።
- ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚው ድርጀቱ በነፃ ክልል አስተዳደር የተበታተነው ታጋይ ነፃ ክልሉን አፍርሶ ሁሉንም የድርጅቱን እንቅስቃሴ በአንድ ማእከላዊ አመራር ይመራው ነበር።
ሀ. ኢትዮጵያ ሰፊ ሃገር እንደመሆኗ የድርጅቱን ሃብትና ንብረት ወደማይታወቅ ቦታ ወስዶ ከዘራፊውና ወንጀለኛው ህወሓት ይድን ነበር፤
ለ. ኢህአሠና ቀሪው የኢህአፓ ታጋይ ከሚከፍለው መስዋእትነት ለማዳን ጊዜያዊ አመራር፣ በጥናት የተመረኮዘ፣ ወደ ሚተማመንበት ቦታዎች በተለያየ አቅጣጫዎች ማፈግፈግ ይችል ነበር። ትግራይን ለቆ በመውጣት የታጋዩን ህይወት በማዳን እንደገና ተደራጅቶ በህወሓት ላይ ጥቃት የመሰንዘር ሰፊ እድል በመፍጠር ኢህአሠ ወያኔንም ሆነ ሻእቢያን ይደመስሳቸው ነበር። ምክንያቱም አሁን ስልታዊ ወታደራዊ ማፈግፈግ በሰፊዋ ኢትዮጵያ ስለሚንቀሳቀስ ብዙውን ወጣት ዜጋ ወደ ትግሉ ስለሚቀላቀሉ ሃይልና ግልበቱ ተጠናክሮ ስለሚወጣ ነው። ይህ መሆንና መደረግ ሲኖርበት፣ ደካማውና ብቃት አልባው የኢህአፓ አመራር አላደረጉትም።
ሀወሓት የኢህአፓውን ተዋጊ ሰራዊት ኢህአሠን ሌሎች ታጋዮችን ለማጥቃት ቀናት እንደቀሩት አሲምባ ውስጥ የነበርው የኢህአፓ አመራር ጓዛቸውን ተሸክመው ሶቦያ ወረዱ። መነኩሳይቶ ለነበሩ ጀብሃ – ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ – ጨለማን ተገን በማድረግ እጃቸውን ሰጡ። በነጋታው ደቀመሃሪ፣ ኤርትራ ወረዳ “ደርሆ ማይ” ወደ ተባለው ቦታ በሌሊት ወሰደው በመኪና ጭነው ሱዳን፣ ካርቱም አደረሷቸው።
የህወሓት አመራር የኢህአፓ ደካማ ጎኑን ለረጅም ጊዜ ያጠናው ስለነበር በተለያዩ የኢህአፓ ነፃ ክልል የተመደቡ ኢህአሠና ታጋዩ አመራሩ ቦታውን ለቆ ሌላውን መርዳት እንደማይፈቅድ ያውቃሉ።
የኢህአፓን ተዋጊ ክንፍ ኢህአሠን ለመደመሰስ የወጣው ፕላን
ጥቃቱ የተጀመረው ታህሳስ 1972 ሆኖ፣ የውጊያው ሁኔታ ከፋፍለው ያስቀመጡትን የህወሓት አመራር፣ ማለትም፣ አረጋዊ በርሄ ወታደራዊ አዛዥ፤ ስብሃት ነጋ የህወሓት ሊቀመንበር፤ መለስ ዜናዊ፤ አባይ ፀሃየ፤ ሥዩም መስፈን፤ አርከበ አቁባይ፤ አዋውአሎም ወልዱ፤ ጻድቃን ገብረተንሳይ፤ ስየ አብርሃ በዋናነት፤ ከህወሓት ተዋጊ አመራር፣ ሃየሎም አርአያ፣ ሳሞራ የኑስ ወዘተ ጋር በመሆን ጥቃቱ ተጀመረ።
የመጀመሪያው የጥቃት ኢላማ አጋሜ አውራጃ የሚንቀሳቀስ የኢህአሠ አሲምባ ሶቦያ አካባቢ በነበረው ላይ ጦርነቱ ተጀመረ። ረዳትና አስተባባሪ አመራር ሰጪ በማጣቱ፣ ለሶስት ቀን በመከላከልና በመልሶ ማጥቃት እንደቆየ ተጠቃ፣ ሊከፍለል የማይገባውን ከባድ የህይወት መስዋእትነት ከፈለ። ህወሓት የቆሰልውን ኢህአሠን ድገመው (አዳግመው) እያሉ ጨረሱት። የታጠቀውን ትጥቅ፣ ጥይት፣ ቦምብ፣ ራዲዎ መገናኛ የሞተውን እያገላበጡ ዘርፈው የኢህአሠን ትጥቅ ታጥቀው ፊታቸውን ወደ ሌላ ቦታ አዞሩ።
ለቀጣዩ ጦርነት በፍጥነት ፊታቸውን ያዞሩት ወደ መሃል ትግራይ ወደነበረው ኢህአሠ ገሰገሱ። በድንገት ገብተው የጥቃት እርምጃ መውሰድ ሲጀምሩ እንዳሰቡት በቀላሉ የሚጠቃ ባለመሆኑ ኢህአሠ የመከላከል ጥቃቱን ከፋፍሎ በሃውዜን፣ በነበለት፣ በፈረሰማይ ወዘተ ስለነበር፤ የህአሠ ተዋጊ ቦታውን በሚገባ ስለሚያውቀውና ከአካባቢው ህዝብም ጥሩ መተበባር ስለነበረው አስቀድሞ የውጊያ ቦታውን በመያዝ እንዳለ የህወሓት ሃይሎች ጥቃት ቢከፍቱም በኢህአሠ አጸፋዊ ጥቃትና መልሶ ማጥቃት ወያኔዎች ሊቋቋሙት አልቻሉም። የህወሓት ታጋዮች ሙትና ቁስለኛ ሆነ። ውጊያውን ይመራ የነበርው አመራር ከአቅሙ በላይ ስለሆንበት ሌላ ተጨማሪ ሃይሎች በማስመጣት እንደ አዲስ ጥቃት ከፍቶ ኢህአሠን አዳከመው። በኢህአሠ በኩልም ወልቃይት ፀገዴ ያለው የኢህአፓ አመራር እዛ ያለው የኢህአሠ ሰራዊት ለእርዳታ እንዲመጣለት ሲጠይቅ የተሰጠው መልስ ክልላችንን ትተን እናንተን ለመርዳት አንመጣም የሚል ነበር። ጥቂት ታጋዮች በረሃው ወደመራቸው አፈግፍገው ህይወታቸውን አዳኑ። ኢህአሠ በዚሁ ውጊያ በጀግንነት ተዋግተው ከባድ መስዋእትነት ከፍለዋል። ህወሓት ኢህአሠን አጥፍቶ በዘረፈው ትጥቅና ጥይት ትምበሸበሸ፣ ሙሉ ሰራዊቱን ክላሺንኮፍ አስታጠቀ።
ቀጥሎም ፊቱን ያዞረው ወደ ወልቃይት ጸገዴ ነበር። በዛ ክልል የነበሩ አመራር አስቀድመው ደብዳቤ ወደ ህወሓት በመላክ እጃችንን እንሰጣለን፣ ተቀበሉን በማለት ገና ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እጃቸውን ሰጡ። በአጠቃላይ ወደ 35 የሚሆኑ በቀጥታ በህወሓት ታጋዮች እየተመሩ ተምቤን ገቡ። ወያኔ ተቀበላቸው። የተቀበላቸው የድርጅቱ የስለላ ሃላፊ የነበረው ተክሉ ሃዋዝ ነበር። ሽሉም እምኒ በተባለችው ጎጥ እንዲያርፉ ተደረገ። በህወሓት ታጋዮች ጥብቅ ቁጥጥር እንደ ግዞተኛ ይጠበቁ ነበር።
ወልቃይት ጸገዴ አካባቢ የነበረው ኢህአሠ አምስት ሃይሎች ሲሆኑ ወያኔ ያለውን የሌለውን ሃይል ወየንቲ/ምልሻም/ ተጨምረው ጥቃት ጀመረ። ኢህአሠ አካባቢውን ስለሚያውቀው ካባድ መከላከል በማድረግ ቀላል የማይባል የህወሓት ታጋዮች ገድለዋል። ይህንን ጦርነት ሲመራው የነበረው ስብሃት ነጋ ለትንሽ ከእጃቸው አመለጣቸው። ብዙ የወያኔ ሃይል አመራር ተገድለዋል። ጦርነቱ ወያኔን ለከባድ ሽንፈት አድርሶት ነበር። ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው ሌላ ተጨማሪ ሃይል መጥቶ ውጊያው በክፉ መልኩ ቀጠለ። አርከበ እቁባይ የቀኝ እግሩ ቋንጃው ተመትቶ ስለቆሰለ በቃሬዛ ተሸክመውት ሸሹ። አሁንም ሌላ ተጨማሪ ሁለት ሃይሎች በበርሄ ሻእቢያና በታደሰ ወረደ የሚመሩ ተጨምረው ኢህአሠ የያዘው ጥይትና ቦምብ እያለቀ በመሄዱ ከባድ መስዋእትነት ከፍሎ በመጨረሻ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው የተወሰኑት ታጋዮች ከጦርነቱ ጉዳት ደህና የነበሩ ኢህአሠ ተመከካረው ወደ መተማ አቅጣጫ አፈገፈጉ። የወሰዱት እርምጃ ትክክለኛ ነበር። ህዝቡም በየሄዱበት በመተባበር አስፈላጊውን እርዳታም በማቅረብ ወደሚፈልጉት ቦታ ሸኛቸው።
ባጭሩ ለኢህአፓ የተሰለፈው ተዋጊ ሰራዊት ኢህአሠ ኢትዮጵያዊ ራእይ ያለው፣ የነቃና ብቃት የነበረው ቢሆንም “የአሳ ግማቱ ከአናቱ” እንዲሉ የኢህአፓ አመራር ደካማና ብቃት የሌለው ስለነበር ሠራዊቱን እንደ ወያኔ ላለ ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ህዝብ ሃይል አጋልጦ ለውድቀት ዳርጎታል።
በኢትዮጵያ አርበኝነት ከሚወሱት የኢህአሠ ተዋጊዎች በተቃራኒ ደግሞ፣ ሰራዊቱ ሲፈርስ እጃቸውን ለወያኔ የሰጡትና ዛሬ እራሳቸውን ብአዴን ብለው የሚጠሩት ግንባር ቀደም የወያኔ ስርአት አስፈጻሚዎች፣ ዋናዎቹ የኢህአፓ ጥፋትና ወድቀት ማስታወሻዎች ሆነው ይገኛሉ።
ኢህአፓ ጠንካራ ጎኖችም የነበሩት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ዘውዳዊው ስርዓት ተንኮታኩቶ እንዲወድቅ ማድረጉና መሬት ላራሹ የመጀመሪያ መፈክሩ ተግባራዊ መሆኑና ሌሎችም አሉት።
የብአዴን አፈጣጠርና አመጣጥ!! መሪዎቹስ እነማን ከየትስ ናቸው?
ሽብርተኛው “terrorist” ቅጥረኛ “mercenary” ህወሓት፣ ኢህአሠን ካጠፋ በኋላ ፊቱን ያዞረው እጃቸውን የሰጡት ወዶ ገቦችን አስልጥነን በፕሮግራማቸው ብሄረ አማራ የመሰሉ ነገር ግን ፀረ-አማራ ሆነው ኢንዲቆሙ ማድረግ አለብን ተብሎ በወቅቱ የነበሩ የህወሓት አመራር፤ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ አረጋዊ በርሄ፣ አባይ ፀሃይ፣ ስዩም መስፍን፤ አውአሎም ወልዱ፤ አርከበ እቁባይ፣ ስየ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ ጻድቃን ገብረተንሳይ፣ ዘርአይ አስገዶም፣ አስፍሃ ሃጎስና የህወሓቱ ም/ሊቀመንበርና የድርጅቱ ዋና አስተዳዳሪ ግደይ ዘርአጽዮን በዚህ አርእስት ላይ አጀንዳ ቀርቦ ሲወያዩ ም/ሊቀመንበሩ ግደይ ዘርአጽዮን ይህንን ሃሳብ አልቀበልም በማለት ራሱን አገለለ። የተቀሩት ውይይቱን ቀጥለው ስምምነት ላይ ደረሱ። የግደይን ስም ለማጥፋት በዚህ ጉዳይ ላይ የታሰፉ አመራር፣ ግደይ የድርጅቱን ሃሳብ በመቃወም ችግር እየፈጠረብን ነው በማለት በደፈናው የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፈቱበት።
ከላይ ከተዘረዘሩት የመጀመሪያዎቹ 12ቱ የህወሓት አመራር ተሰባስበው፣ ተወያይተው ስምምነት የደረሱበት አማራ ጠላት እንደመሆኑ በራሳችን ትእዛዝና እንቅስቃሴ የሚታዘዝ ድርጅት ከፈጠርን አማራው ህልውናው የሚጠፋበት አማራጭ መንገድ ከዚህ የበለጠ ስለሌለን ፕሮግራሞቹን ጽፈን ሙሉ ቁጥጥር እያደረግን እነዚህን የኢህአፓ ወዶ ገቦች እናደራጅ ተብሎ ውሳኔ ተላለፈ።
በዚህ ውሳኔ መሰረትም መለስ ዜናዊ፣ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃየ ለሚመሰረተው የአማራ ድርጅት ፕሮግራምና የቅድመ ሁኔታ ውይይት እንዲያዘጋጁ ሃላፊነቱ ተሰጣቸው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የህወሓት አመራር ያዘጋጁት ለህወሓት ፖሊት ቢሮ ስብሰባ ቀርቦ፣ እነ አረጋዊ በርሄና ስዩም መስፍን አንድ ላይ ሆነው የቀረበውን ጽሁፍ አንብበው ፕሮግራሙ ላይ ተስማሙበት። ይህም በዋናነት እጃቸውን የሰጡ የኢህአፓ አባላት ውይይቱን የሚመሩ ሶስት ሆነው ወዶ ገቦቹን አሳምነው መስራች ጉባኤ ተካሂዶ ፕሮግራሙን አምነው ተቀብለው በህወሓት እርዳታ የአማራ ብሄር ድርጅት ተመስርቶ እንዲቋቋም ተብሎ ተወሰነ።
በፕሮግራሙ መሰረት የመወያያ አርእስቶች
ውይይቱ የተጀመረው ግንቦት መጨረሻ 1972 ሲሆን፣ የውይይቱ መሪዎች መለስ ዜናዊ፣ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃየ፤ ሲሆኑ ተጠባባቂ ረዳቶች ደግሞ አውአሎም ወልዱና አርከበ እቁባይ ሆኑ። የመወያያው ር ዕስ፣
- ነፃ ሃገር የነበረችው ኤርትራ ዛሬ በኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ስር ወድቃ ህዝብ ለመከራና ለችግር ተዳርጓል። ከህዝባዊ ሓርነት ኤርትራ ጋር በመተባባር ኤርትራን ነፃ እናወጣለን፣
- ነፃ ሃገር የነበረችው ትግራይ፤ የራሷ መንግሥትና መስተዳድር የነበራት ሃገር፣ ከአፄ ዮሐንስ ሞት በኋል በምኒልክ ተወራ በአማራው ቅኝ አገዛዝ ቀንበር መውደቋ፣
- የአሁኗ ኢትዮጵያ የታሪክ ድሃና ታሪክ የሌላት ሃገር፣ በአፄ ምኒልክ የተመሰረተችና ከ100 ዓመታት ያነሰ ታሪክ ያላት ሃገር መሆኗን አምኖ መቀበል፣
- ምኒልክ ግዛቱን ለማስፋፋት በመነሳት ሳይወድ በግድ ኢትዮጵያዊነትህን ተቀበል ተብሎ በአማራው የመንግሥት ስርዓት በስቃይና በችግር የሚገኙት ብሄር በሄረሰቦች የራስን እድል በራስ በመወሰን እስከ መገንጠል አምኖ መቀበል። በዚህም ላይ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ወህኒ ቤት መሆኗን አምኖ መቀበል፣
- አማራ የሚባለው ጨቋኝ ፀረ-ሕዝብ መሆኑን አምኖ መቀበል።
እነዚህ ከተራ ቁጥር 1-5 የተጠቀሱት ዋናውና የሚፈጠረው የአማራ ድርጅት የሚመራበት ፕሮግራም ሆነው ለውይይት ቀረቡ።
ይህንን ውይይት የህወሓት አመራር አባይ ፀሃየ፣ ሊቀመንበር፣ መለስ ዜናዊ፣ ስብሃት ነጋ ሆነው በመቅረብ ከሰኔ ወር መጀመሪያ 1972 እስከ ህዳር መጨረሻ 1973 ለ6 ወር ተከታታይ ውይይት ሲካሄድበት፣ በዚህ ጊዜም አዳዲስ የኢህአፓ አባላትም ሲቀላቀሉ ነበር። አብዛኛዎቹ ይህ ፕሮግራም ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሉአላዊነትና ፀረ-ሕዝብ ነው ይሉ ነበር።
የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ሺህ ዘመናት የዳበረ ወንድማማችነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ በጋብቻ፣ በባህል፣ በእምነት በአንድነት ሆኖ ሃገሩን ኢትዮጵያን ከባእዳን ወራሪዎች ተከላክሎ ለኛ አስረክቦናል። በህዝባችን ያልነበረና ያልታየ ፕሮግራም ተሸክመን አንታገልም ሲሉ፣ ከፈቀዳችሁ ፕሮግራሙን ራሳችን ጽፈን ለአንዲት ኢትዮጵያ፣ ለአንድ ህዝብ እንዲታገል ፍቀዱ። አማራ የህዝብ ጠላት ነው የምትሉት እኛም አማራ ነን፡፡ ኩሩውን አማራ የኢትዮጵያ የህዝብ ጠላት ነው ብላችሁ አትፈርጁት፣ በማለት እልህና ንዴት እንዲሁም ብስጭት በተቀላቀለበት ለወራት ከተወያዩ በኋላ ተሰብሳቢው በሶስት ተከፈለ።
- በህወሓት ፖሊት ቢሮ ተረቆና ተዘጋጅቶ የቀረበውን ተቀብላችሁ ታገሉ የምትሉንን አንቀበለውም። በአማራው ህዝብ እውቅናም ውክልናም አልተሰጠንም። አማራውን ብቻ መነጠል ጠባብ አስተሳሰብነው፣ በዚህም ላይ አማራ ጠላት ነው እያላችሁን አማራውን ለክፉ ስቃይ አንዳርገውም። አማራ ኢትዮጵያዊ ነው፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ይታገል፣
- ጊዜ ስጡን፣ በረጋ መንፈስ አንብበን እና ተረድተን መልስ እንስጥበት የሚሉ፤
- በህወሓት የቀረበልን ፕሮግራም ለብዙ ወራት ገንቢ ውይይት ያካሄድንበት ትክክለኛ የአቋም ፕሮግራም መሆኑን ስለአመንበት ካለምንም ተቃውሞና ጥርጣሬ ተቀብለነዋል ያሉ ናቸው።
ከዚህ ተከትሎ ምን ተፈጠረ የሚለውን ባጭሩ እንመልከት። እንደሁኔታው ተራ ቁጥሩ ይለዋወጣል።
- ጊዜ ስጡን፣ በረጋ መንፈስ አንብበን መልስ እንሰጥበታለን ያሉት፣ ትንሽ ጊዜ ለማግኘትና ሕይወታቸውን ለማዳን የሚጠፉበትን እቅድ ማውጣት ላይ ተሰማሩ። ጋሻው ከበደ፤ አያሌው ከበደ፣ ምትኩ አሸብር ከማስታውሳቸውና ሌሎችንም ጨምሮ፣ የተወሰኑት ወደ ሱዳን፣ የተወሰኑት ደግሞ ለኢትዮጵያ መንግሥት እጃቸውን በመስጠት ሕይወታቸን አዳኑ። አሁንም በሕይወት አሉ።
- በህወሓት ፖሊት ቢሮ ተረቆ የተዘጋጀውን ፕሮግራም አንቀበልም ያሉት በህወሓት አመራር ላይ ጭንቀት ስለፈጠረበት የተወሰኑ አመራር ተሰብስበው፣ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃየ፣ ስየ አብርሃ፣ መለስ ዜናዊ፣ አውአሎም ወልዱ፣ አርከበ አቁባይ፣ ጻድቃን ገ/ተንሳይና ስዩም መስፈን ተሰብስበው እነዚህን የህወሓት ሃሳብ ያልተቀበሉትን አፈንጋጭ በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጡ። በውሳኔው መሰረት በስብሃት ነጋና አባይ ፀሃየ ሃላፊነት እንዲፈጸም ተወሰነ። በዚህ ጊዜ ሃለዋ ወያነ (06) በዙ እስረኞች ሞትን የሚጠባበቁ ስለነበሩ፣ የቦታው ርቀትን ጨምሮ ሃሳቡ ቀርቦ ከህዝብ ግንኙነት አባላትም ተጨምረው ግድያው እንዲፈጸም ተደረገ።
ግደያውን የሚያስፈጽሙት፣ ብስራት አማረና ሃሰን ሹፋ እንዲሆኑ ፖሊት ቢሮው ወሰነ።
1. ከወርዲ ሃለዋ ወያነ በአበበ ዘሚካኤልና ዘርአይ ይህደጎ የሚመሩ ተጨማሪ 5 ታጋዮች
2. ፃኢ ሃለዋ ወያነ በወልደሥላሴ ወልደሚካኤልና በተስፋየ መረሳ (ጡሩራ) የሚመሩ 5 ታጋዮች
3. ከህዝብ ግንኙነት
ለኡል በርሄ፣ አብያ ወልዱ፣ ሃይሉ በርሄ፤ ቢተው በላይና ወልደ ገብርኤል ሞደርን። ሁሉም ተሰብሰበው ተምቤን ውስጥ አምበራ መጡና ገቡ። ግደያውን የሚፈጽሙት ብስራት አማረና ሃሰን ሹፋም መጥተው ከእነ ታምራት ላይኔ ጋር ቆዩ። ስብሃት ነጋም መጣና ከነብስራት አማረ ጋር ተነጋገረ። እነታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምኦን ወዘተ ከነበሩበት ቤት ራቅ ባለ ቦታ የመረሸኛ ጉድጓድ ተቆፍሮ ተዘጋጅቷል። እነዚህ በህወሓት የተረቀቀውን ፕሮግራም አንቀበለም ያሉት ቁጥራቸው በርካታ ነው። ስብሃት ነጋ ለልዩ ስብሰባ ብሎ በሃለዋ ወያነ አባላት ታጅበው ሄዱ። አባላቱ እጃቸውን በገመድ ጠፍረው በማሰር ወደ ተዘጋጀው መግደያ ጉድጓድ ወስደው በጥይት ደብድበው ገደሏቸው። ሁሉም አማራ ሲሆኑ፣ ሃይላይ የሚባል አንድ የትግራይ ልጅ ከነሱ ጋር ነበር።
ይህ ፋሽስታዊ ተግባር እንደተፈጸመ በሶስተኛው ቀን በጣም አሳዛኝና አስደንጋጭ ወሬ በህወሓት ታጋይ ተናፈሰ። ወሬውን የበተኑት በግድያው የተሳተፉት የሃለዋ ወያነ አባላት እነ ሃሰን ሹፋ፣ አበበ ዘሚካኤል፣ ተስፈየ መረሳ ወዘተ ከህዝብ ግንኙነት ተመርጠው የመጡ ልኡል በርሄ፣ ቢተው በላይ በህወሓት ውስጥ ኦቦራ አስነሱ። የህወሓት ታጋይ ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ተናደደ፣ አበደ። በዚህ ጊዜ መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ ፈርተው ተደበቁ። እነብስራት አማረም ፈርተው ባኽላ ሄደው ተደበቁ።
በዚህ በተሰራጨው ወሬ ጠንከር ያሉ አመራር ስለነበሯቸው በተረጋገጠው ዜና የእንቅስቃሴው መሪዎች የነበሩ፣ ከልካይ ጎበና፣ አስራደው ዘውዴ፣ ዳኛቸው ታደሰና ሃይላይ፣ አክራሪ አማሮች፣ የነፍጠኛ ልጆች የተባሉ በነበሩበት ወቅት በፋሽስት ህወሓት አመራር ለህልፈት በቅተዋል።
በህወሓት የተረቀቀውን ፕሮግራም አምነን ተወያይተን ገምቢ ፖሊሲውን ተቀብለናል ያሉት እነዚህ ናቸው፣
- ሙሉአለም አበበ፣ አማራ 7. ህላዊ ዮሴፍ፣ ኤርትራ
- ሃይለ ጥላሁን፣ ትግራይ፣ እድገቱ ጎጃም 8. ተፈራ ዋልዋ፣ ሲዳማ
- ታምራት ላይኔ፣ ከንባታ 9. ታደሰ ካሳ፣ ትግራይ
- ዮሴፍ ረታ፣ ትግራይ፣ ኤርትራ 10. መለሰ ጥላሁን፣ አማራ፣ ትግራይ
- በረከት ስምኦን፣ ኤርትራ 11. ሲሳይ አሰፋ፣ ትግራይ
- አዲሱ ለገሰ፣ ሂርና ሃረር 12. ኢያሱ በላቸው፣ ትግራይ፣ አማራ
ማሳሰቢያ፣ ከላይ የተጠቀሱትን ትወልድ ቦታቸውን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖብኝ ለዓመታት ብቆይም፣ ዛሬ ግን ከሚያውቋቸው ሰዎች ጠይቄና አፈላልጌ ትክክለኛውን የትውልድ ቦታቸውን በማያያዝ ይህን ጽሑፍ አቅርቤአለሁ።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ናቸው የአማራ ህዝብ ድርጅትን ለመመስረት ህወሓት ያዘጋጀው። ህዋሓት ሲፈጠር በሻእቢያ ነበር። ያደረገው ነገር ድርጅቱ በኤርትራውያን እና ከትግራይ የተፈጠሩ ባንዶች በማቀናጀት ህወሓትን ፈጠረ። ለምን ይህ ነገር ተደረገ የሚል ጥየቄ ከተነሳ፣ ሻእቢያ የትግራይና አማራውን ህዝብ ስለሚጠላ ህወሓት በህዝቡ ላይ ጥቃት ይፈጽማል በሚለው ፖሊሲ መሰረት ነው። ህወሓት በወቅቱ ተሓህት ገና ከመፈጠሪያ ትግሉ መነሻ ጀምሮ በትግራይና በአማራው ህዝብ ላይ የፈጸመው ግድያና እልቂት የአማራውን እና የትግራይ ህዝብ ያውቀዋል። ከዚህ በመነሳት ህወሓት የፈጸመውና እየፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል የዓለም ህዝብ ያወቀው እውነት ነው። አሁን ደግሞ ብአዴን በአማራው ላይ የሚፈጽመው ወንጀል አደባባይ የወጣ ሃቅ በተግባር እየታየ ነው።
ከዚህ ከአፈጣጠሩ ተነስተን ብአዴን ማን ነው? እውነትስ የአማራውን ህዝብ ይወክላል? ለሚሉት መልስ ለመስጠት እነማን ናቸው የአማራ መሪ ድርጅት ብለው የሰየሙት? ከየትስ መጡ? ብዙ ጥያቄ ሊነሳ ይገባል። ለዚህ ሁሉ መልስ ግን ይህ ጽሑፍ ሙሉ መልስ የሚሰጥ ነው። በእርጋታና በጥሞና አንብቡት። የአማራው ህዝብም ብአዴን አማራን አትወክልም፣ አናውቃትም በማለት እምቢ አልገዛም ማለቱ ትክክለኛ የትግል መስመር ነው። ቀሪው ኢትዮጵያዊም ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ኦጋዴን፣ ደቡብ ህዝብ፣ የሁላችንም መልስ አንድ ነው። ህወሓት ዘረኛና ፋሽስት ነው፣ አጋር ድርጅቶችም የህወሓት ተግባር አስፈጻሚ ናቸው።
ህወሓት ምን መብትና ሃላፊነት አለው ለአማራ፣ ለኦሮም፣ ለደቡብ፣ ለአፋር ወዘተ? ድርጅት የሚመሰርተውስ ህወሓት ራሱ ማን ነው? በቅጥረኝነት የተፈጠረ የባንዳ ስብስብ የተለያዩ ድርጅቶች መስርቶ ኢትዮጵያን ሊበትን የመጣ መብቱን ማን ሰጠው? ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ከነዚህ የቀን ጅቦች የሚገላግለው ራሱ ነው።
ሐምሌ 1973 የህወሓት ፖሊት ቢሮ ያዘጋጀው የኢህዴንን ፕሮግራም በመያዝ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ አርከበ እቁባይ አምቦራ መጡ ልዩ ስሙ ሸሉም እምኒ ቁሽት በመሄድ ቀኑም የተቆረጠ ስለነበር ከኢህዴን አባላት ጋር ተገናኙ። በፕሮግራሙ ላይ ለአጭር ጊዜ ከተወያዩ በኋላ የብአዴን ፕሮግራም መሆኑን በድጋሚ ባማረጋገጥ ተቀበለው። የኢህዴን መስራች ጉባኤ እንዲመሰረት ተደረገ። በዚህ መስራች ጉባኤ አምስት ሰዎች ብቻ ስለሚፈለጉ በእቅዱ መሰረት ምርጫው ተካሄደ። በምርጫውም ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ህላዊ ዮሴፍና ተፈራ ዋለዋ ሲመረጡ፣ ሊቀመንበሩ ታምራት ላይኔ ሆነ።
መስራች ጉባኤ እየተባለም እስከ 1975 ቆየ። ለዚህ ምክንያት ካለ 12ቱ የኢህዴን ሰዎች ማንም ከትግሉ የሚቀላቀል አልተገኘም። ኢህዴን ወይም የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እየተባለ የመጣው ዋና ዓላማው የኢትዮጵያ ታጋይ እየተባለ ድጋፍና ታጋይ ወጣቶች ከአማራውና ከሌላውም ለማግኘት ህወሓት ያቀደው ዓላማ ነበር። ቢሆንም፣ አንድም አልተገኘም፣ ድጋፍም አላገኘም።
ህወሓት በኢህዴን ተስፋ በመቁረጥ ከራሱ 50 የህወሓት ታጋይ ጨመረለት። እነዚህ ደግሞ 12ቱን ግዞተኞች የሚከታተሉና የህወሓት ታጋዮች በሚሉት ስለሚመሩ መብት አልነበራቸውም።
የህወሓት አመራር የኢህዴን 1ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የት ይደረግ የሚለው ሃሳብ ከተወያየ በኋላ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ሐምሌ 1975 ዋግ አካባቢ እንዲሆን ሲወሰን ህወሓት ደግሞ ሙሉውን የጉባኤ ወጪ ሸፍኖ እንዲዘጋጅ ተደረገ። በዚሁ ጉባኤ የህወሓት አመራር ትኩረት የሰጠው እነማን ጉባኤውን ይምሩት በሚለው ላይ ነበር። በህወሓት ውሳኔ መሰረት በሊቀመንበርነት ጉባኤውን የሚመሩ መለስ ዜናዊ፣ ሊቀመንበር፣ አባይ ፀሃየ፣ ከህወሃት፣ ህላዊ ዮሰፍ፣ ብአዴን ተብሎ ተወሰነ።
በፕሮግራሙ መሰረት በመለስ ዜናዊ ሊቀመንበርነት የኢህዴን ጉባኤ ተጀመረ። ለአንድ ቀን በተለያዩ ጉዳዮች ከተወያዩ በኋላ በሁለተኛው ቀን 1ኛው የብአዴን አማራውን የሚወክል አርማና ባንዲራ ማጽደቅ፣ 2ኛ የብአዴን አመራር መምረጥ ሲሆን በአንደኝነት የተጠበቀው አልተዘጋጀም ተብሎ ለ2ኛ ጉባኤው ሲተላለፍ፣ መረጣው ግን ቀጠለ። ከዚህ በታች የሚታየው ስም ዝርዝር የአማራ ህዝብ አመራር ናቸው። ከአማራው ህዝብ አብራክ የተወለዱት አማሮች እንደመሆናቸው አማራውን ይመሩታል በማለት በህወሓት የማጭበርበር ዘዴ መለስና አባይ እየተቀባበሉ ተናግረው ምርጫው ቀጠለ።
ተ.ቁ
|
ስም ከነ አባት
|
የትውልድ ቦታ
|
ሃላፊነቱ
|
1 | ታምራት ላይኔ (ጌታቸው ማሞ) | ከንባታ | የብአዴን ሊቀመንበር |
2 | በረከት ስምኦን | ኤርትራ | ም/ሊቀመንበር |
3 | አዲሱ ለገሰ | ሂርና፣ ሐራር | |
4 | ተፈራ ዋለዋ | ሲዳማ | ፕሮፓጋንዳ ቢሮ |
5 | ዮሴፍ ረታ | ኤርትራ | |
6 | መለሰ ጥላሁን | አማራ፣ ትግሬ | |
7 | ህላዊ ዮሴፍ | ኤርትራ | የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ |
ተ.ቁ |
ተለዋጭ ማ/ኮሚቴ ስም ከነአባት
|
የትውልድ ቦታ
| |
1 | ታደሰ ካሳ | ትግራይ | |
2 | ሙሉአለም አበበ | አማራ |
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በጉባኤው ተመረጡ። ኢህዴን የሚለው ስም ተለውጦ ብአዴን (ብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ተብሎ ተሰየመ። የአማራ መሪ ድርጅት ሆነ። ቀደም ብለው የተነሱ ጥያቄዎች ብአዴን ማን ነው? ከየትስ መጡ? እነማንስ ናቸው? ወዘተ ለሚሉትጥያቄዎች መልሱ ይህ ነው። እውነትስ ብአዴን የአማራውን ሕዝብ ይወክላል? መልሱ ፈጽሞ አማራውን የሚወክል ድርጅት አይደለም ነው።
ህወሓት ለራሱ ትግል የተነሳው ኤርትራን አስገንጥሎ የትግራይ መንግሥት እናቋቁማለን ብሎ ነው ፕሮግራሙን አዘጋጅቶ የካቲት 1967 ደደቢት በረሃ የወረደው። በምን መልኩ ነው ደመኛ ጠላቴ ለሚለው አማራ ድርጅት ብአዴንን ሊፈጠርለት የቻለው? ህወሓት ምን መብትና ሃላፊነት አለው? ማንስ ሰጠው? ህወሓት ይህን ሁሉ የፈጠረው የአማራውን ህዝብ ከዘር ማንዘሩ ሊያጠፋልኝ ይችላል ብሎ ነው የብአዴንን ቅጥረኞች “mercenary” የፈጠረው። ሌላውም ህወሓት ለአማራ ድርጅት መፈጠር ቅንጣት የምታክል መብት ፈጽሞ የለውም። ስለዚህ ብአዴን ፀረ- አማራ ቅጥረኛ ድርጅት ነው።
እነዚህ ወዶ ገቦች ብአዴን ከህወሓት እንደተቀላቀሉ በተግባር ያሳዩትን ግፍ ባይናችን አይተናል። የኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች እያሉ በወልቃይት፣ በፀገዴ፣ በጸለምት መሪ ሆነው ለህወሓት በመጠቆም ስላማዊ ዜጋውን አማራ አስጨርሰዋል። ንብረቱ በህወሓት እየተወረሰ ተገድሏል። ህፃን፣ ሽማግሌ፣ ሴት ሳይለይ እነበረከት ስምኦን በነስብሃት ነጋና አርከበ እቁባይ ትብብር ሙሉ ቤተሰቦች በሚኖሩበት የሳር ቤት እያስገቡ በላያቸው ላይ እሳት ለኩሰው አቃጥለው አስገድለዋል። በተመሳሳይ መንገድ ታምራት ላይኔ፣ ታደሰ ካሳ፣ መለሰ ጥላሁን እና ህላዊ ዮሴፍ ህዝቡን ቤት ውስጥ በማስገባት በእሳት በማቃጠል ጨርሰዋል። የወልቃይት ከሞት የተረፈው የፀገዴና ጸለምት ህዝብ ላይ የተፈጸመበትን ግፍ ይውጣና ራሱ ይመስክር። ምስክርነትህን ጮክ ብለህ አሰማ።
ብአዴን ከ1972 መጨረሻ ጀምሮ በአማራው ላይ አሰቃቂ ግፍ እየፈጸመ የመጣ ፀረ-አማራ የሆነ ቅጥረኛ “mercenary” ድርጅት ነው።
አዲሱ ለገሰ ወያኔ ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረ በተወለድኩበት ለዘመናት የቆዩትን አማሮች ዘር እየለየ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማራዎችን አልገድልክም? አፈናቅለህ አላባረርክም? በምን መልኩ ነው አንተ ወንጀለኛና ፋሽስት አማራውን የምትወክለው? ብአዴን ሁላችሁም ግፍ የፈጸማችሁና በደም የታጠባችሁ ናችሁ።
ብአዴን የአማራውን ህዝብ ባህልና ወግ የማያውቅ ስለሆነ የአማራ መሪ ድርጅት የመሆን መብትና ሕጋዊነት የለውም። በአንጻሩ ብአዴን ፀረ-አማራና አማራውን ለማጥፋት በህወሓት የተፈጠረ ነው።
የብአዴን 2ኛው ጉባኤ በ1981 ዋግ አውራጃ አውሰን ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲካሄድ፣ ብአዴን ያሳየው እድገት አልታየም። ሐምሌ 1975 የተመረጠው አመራር በድጋሚ ተመረጡ። አሁንም 12 ሰዎች ናቸው።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ሀገራችን ወደ ጨለማ ጉዞ እያዘገመች ነበረች። ትናንትና ደህና የነበረው፣ ዛሬ አስደንጋጭ ሁኔታ ይዞ ብቅ ይላል። ደርግ ትግራይን ለቆ በመውጣቱ ህወሓት ትግራይን የመቆጣጠር እድል ስላገኘ፣ የአሜሪካ የስለላው ማእከል CIA ባለሥልጣናት መቀሌ ድረስ በመሄድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስተካከል ተባበሩት። ህወሓት ትግራይን ነፃ ለማውጣት በተላበሰው አልባሳት ላይ ሌላ ካባ ደረበበት። መስከረም 1982 እንደርታ አውራጃ ሰምረ ወረዳ ባኽላ ቁሽት ግዞተኛ የነበረው ብአዴን አመራሩ በሙሉ ተጠርተው መቀሌ ገቡ። የመጡበት ምክንያት ለስብሰባ መሆኑ ተነገራችው።
ስብሰባው ሁሉም የህወሓት የፖሊት ቢሮ አባላት፣ መለስ ዜናዊ፣ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃየ፣ ሥዩም መስፍን፣ ስየ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አለምሰገድ ገ/አምላክ፣ አበበ ተ/ሃይማኖት፣ አርከበ እቁባይ፣ አረጋሽ አዳነ፣ አውአሎም ወልዱ፣ ክንፈ ገ/መድህን እና ጻድቃን ገ/ተንሳይ ሲሆኑ፤ በብአዴን በኩል ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋለዋ፣ ዮሴፍ ረታ፣ መለሰ ጥላሁን፣ ህላዌ ዮሴፍና ተደሰ ካሳ ናቸው። በዋናው አጀንዳ ከተነጋገሩ በኋላ በመጨረሻ ብአዴን የህወሓት አጋር ደርጅት መሆኑ ተገለጸላቸው። በዚህ መሰረትም ህወሓትና ብአዴን በመሆን ኢህአዴግ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ተብለው እንደሚጠሩ ተወሰነ። የቀኑ ውሎ ሁኔታ እንደመግቢያ ተደርጎ “ድምፂ ወያነ” ልክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በይፋ ታወጀ፣ በጽሑፍም ተበተነ።
እኔ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በወቅቱ የነበርኩት አዲስ አበባ ስለሆነ በጊዜው የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓት በትግራይ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በየሰዓቱ በሚስጥራዊ ሥራው ይከታተለው ስለነበር ከላይ ያስቀመጥኩት ሁሉ በተገኘው የስለላ መስመር ሁሉም በዝርዝር ተነገረኝ። ዛሬ ማታ በ12 ሰዓት በድምፂ ወያነ እንድከታተለው ተነገረኝ። ጠቅላላ የመረጃውን ጽሑፍ እንዳነበው ተሰጠኝ። አንብቤም አንዳንድ ነጥብ በማስታወሻ እንድጽፈው ፈቃድ ስጠይቅ ይቻላል፣ ምንም ችግር የለውም ተባልኩ። አስፈላጊውን ወሰድኩ። ቤቴ ሂጄ ልክ በ12 ሰዓት ድምፂ ወያነን ከፍቼ አዳመጥኩ። የደህንነቱ የመረጃ ክፍል ያነበብኩትና የነገሩኝ ሁሉ በትክክል ቃሉ ሳይዛነፍ ድምፂ ወያነ ሴኮ በሚባል ሰው አዋጁን አስነበበ።
የደርግ መንግሥት የደህንነትና የመረጃ ሥራ በጣም ረቂቅና የተደራጀ መሆኑን ያደነቅሁት በዚህ ጊዜ ነበር። ለነገሩ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት የተማሩ ምሁራን መሆናቸውን አውቃለሁ።
የህወሓት ፋሽስት አመራር ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ለማጥፋትና ለመበታተን በፕሮግራሙ ያስቀመጠው ኢህአዴግ በሚል ስም ግንቦት 20 ቀን 1983 ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ስርዓቱ እንደተቆጣጠረ 12ቱም ብአዴን “ብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ”ን አጋር ድርጅት ብሎ የሰየመው ህወሓት አቅፎት አብረው አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ህወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ አደናግሮ ፋሽስትና ሽብርተኛ ስርዓቱን በመላ ሃገሪቷ ዘረጋ።
ፋሽስቱ ህወሓት በሽግግር መንግሥት ስም ስርዓቱን እንደ ዘረጋ፣ ቀዳሚ ትኩረቱ ያደረገው የአማራውን ህዝብ ዘሩን ለማጥፋት ተግባራዊ እርምጃ በቅጥረኛው “mercenary” ብአዴን ታምራት ላይኔ ጠ/ሚኒስትር ሆነ። የብአዴኑ መሪ የከንባታው ተወላጅ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ፀረ-አማራ ንግግር በተደጋጋሚ በመናገር ተስፋፊ፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ አማራን ማጥፋት አለብን በማለት የዘር ማጥፋት ወንጀሉን ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጀ።
በ1983 ከሰኔ ወር ጀምሮ በህወሓት ፋሽስቱ መሪና የህወሓት አመራር በሙሉ በሚያምኑበትና በተሰጠው ቀጭን መመሪያ በአማራውን ህዝብ በየአለበት በታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ፣ በተፈራ ዋለዋ፣ በመለሰ ጥላሁን ወዘተ የብአዴን አመራር መሪነት የህወሓት የታጠቁ ሃይሎች በማሰለፍ በየቦታው ዘምተው በአማራ ህዝብ ላይ አሰቃቂ ግድያ በመፈጸም ዘሩን ለማጥፋት ዘግናኝ እርምጃ ወስደዋል። በአርባ ጉጉ፣ በደኖ፣ ቦረና፤ ጉጂ፤ ጋምቤላ ወዘተ የነበረውን አማራ ሙሉ በሙሉ ገድለው አጠፉት። ከሞት እንደ ምንም ብሎ የዳነውን፣ ውጣ አንተ ተስፋፊ፣ ትምክህተኛ ተብሎ በመፈናቀል በረሃ ላይ ወደቀ። ከህፃናት እስከ ሽማግሌ፣ ወንድና ሴት ሳይለይ፣ እርጉዝ ሴቶችን ጨምሮ በረሃ ተጥለው ለአራዊት ምግብ የተዳረገው፣ ለመጥፎና አሰቃቂ መከራ የተዳረገው፣ በህወሓትና ብአዴን የአማራው ህዝብ ነው።
በረከት ስምኦን ባደገበት ወሎ አካባቢ በሱ የሚመራው የህወሓት ታጣቂ ገዳዮች በመያዝ በአማራው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ግድያ የፈጸመው የብአዴን መሪ ቅጥረኛ ኤርትራዊ ነው።
አዲሱ ለገሰ በተወለደበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩትን አማሮች በአሰቃቂ ግደያ አጥፍቷቸዋል። ከንብረታቸው አፈናቅሎ ለመከራና ችግር የዳረጋቸው የብአዴን መሪ ነው።
መለሰ ጥላሁን ባደገበት የአማራው ቦታ በህወሓት የታጠቁ ሃይሎችን በመምራት በአማራው ላይ አሰቃቂ ግፍ የፈጸመ የብአዴን መሪ ነው። የብአዴን መሪዎች ሁሉም በአማራው ህዝብ ላይ ፋሽስታዊ ግፍ ፈጽመዋል። ታድያ እነዚህ የብአዴን አምራር ፀረ-አማራ ሆነው ተፈጥረው አንተን በምርኮኛነት እየተቆጣጠሩህ የአማራ ህዝብ መሪዎች ናቸው? መልሱ፣ አይደለም ነው።
በኢሳት ሚዲያ የተሰራጨውን ዘገባ የሰማነው በትክክል ኤርትራዊው ቅጥረኛ በረከት ስምኦን የብአዴን ሥራ አስፈጻሚና መሪ የአማራ ሕዝብ ተነስ ስንለው ይነሳል፣ ተኛ ስንለው ይተኛል፣ አድርግ ስንለው ያደርጋል በማለት የተናገረው የአማራው ህዝብ ለ23 ዓመታት እንደ ባርያ እየገዙት፣ መብቱ እየተረገጠ፣ እንዴት በእነዚህ የብአዴን ቅጥረኞች ዘሩ እየጠፋ፣ ከየቦታው እየተፈናቀለ፣ እየተገደለ ሊኖር ነው? መልስ የሚሰጠው የነፃነት ግዴታው የሆነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።
አለምነው መኮንን የተባለው ቅጥረኛ ባንዳ ህወሓት በአማራው ላይ የሚከተለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ፖሊሲ ፈጻሚና አስፈጻሚ በመሆን የሚሰራው የብአዴን መሪና ሥራ አስፈጻሚ በብአዴን የካድሬዎች ስብሰባ በአማራው ህዝብ ላይ ያወረደው አስጸያፊ ስደብ በጣም ያሚያሳዝን ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሚገባ የተከታተልው ስለሆነ ይህንን ዘግናኝና አጸያፊ ስድብ እዚህ ባላነሳው ይሻላል። አለምነው መኮንን የተፋው ስድብ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነው የሰደበው። ሲናገርም፣ ይህ የተናገርኩት ጉዳይ የድርጅቴ ብአዴን/ኢህአዴግ አቋምና እምነትም ነው፣ በማለት በድጋሚ አረጋግጦታል።
ደመቀ መኮንን የብአዴን ሥራ አስፈጻሚ መሪ ነው። ቅጥረኛው ባንዳ በጸረ አማራነቱ የተሰለፈ በመሆኑ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የሚገኝ ነው። በአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከመነሻ ጀምሮ ከነበረከት ስምኦን፣ ህላዌ ዮሴፍ፣ ታደሰ ካሳ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋለዋ፣ ታምራት ላይኔ ወዘተ በመተባበር አማራውን ከየቦታው በማፈናቀል ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ተስፋፊ በማለት ግፍ የፈጸመ ወንጀለኛ ሲሆን፣ በተጨማሪም ክህወሓቱ መሪ መለስ ዜናዊ ጎን በመቆም የሱዳን መንግሥት መሬቴን ባለፉት መንግሥታት የኢትዮጵያ መሪዎች ስለተቀማሁመልሱልኝ በማለታቸው በአማራው ክልል ያለው የሱዳን መሬት ነው ብለህ ፈርም ተብሎ ካለምንም ማቅማማት ፈርሞ የሰጠ ፀረ-ኢትዮጵያ ሉአላዊነት ባንዳ ነው።
ብአዴን የህወሓት ተግባር ፈጻሚ ባንዳና ቅጥረኛ በመሆኑ በአማራው ላይ ያደረሰው ጥቃትና መፈናቀል ባጭሩ እንመልከት፤
- በቀጥታ በህወሓት የሚፈጸሙት ግድያዎች ዘር ማጥፋት ብአዴን በዋናነት በመሰማራት ግፍ የፈጸመ፣
- ከህፃናት ጀምሮ እስከ 45 ዓመት ክልል ወስጥ የሚገኙትን አማራዎች የዓይን ትራኮማ መድሃኒት ነው በማለትና ሽፋን በመስጠት የማምከኛ መርፌና ኪኒኒ ለወንዱም ለሴቱም በመስጠት የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸሙና እያስፈጸሙ የሚገኙት የብአዴን አመራር በሙሉ ናቸው፣
- ከመሬቱ የተፈናቀለው አማራ ተፈናቅሎና ተበታትኖ በየቦታው እያለቀ፣ ረሃብና በሽታ በላዩ ላይ ወርዶ የሚፈጸምበት ያለ ህዝብ ነው። ይህንን ሁሉ በሰው ልጅ ላይ እየፈጸመ ያለው ቅጥረኛው ባንዳ ብአዴን ነው። ለምሳሌ ደመቀ መኮንን እና ግብረአበሮቹ እነ በረከት ስምኦን ሁሉ የብአዴን መሪዎች ከየአካባቢው ክልሎች አመራር ውስጥ ልወስጥ በምስጢር ተነጋግረው ከቤኒሻንጉል፣ ጉራ ፈርዳ፣ ወዘተ ትምክህተኛውና ተስፋፊው አማራን ከየክልላቸሁ ባሃይል አስወጡት በማለት የአማራው ህዝብ ተፈናቅሎ እንዲበታተን ያደረጉ፣ በአማራው ህዝብ ጉያ መሽጎ ያለው ብአዴን ነው። ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ሚና ተጫውተዋል። አማራው ለዚህ አስከፊ ሰቃይ የዳረገው የአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን ነው። ባነተ ስም ግን ይነግዳል፣ ይሾማል፣ የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራል። ይህንን የሰጠው ህወሓት አንተን ድርሻህን አጥፍቶ ለስደትና ለክፉ ሞት ስለዳረገህ ህወሓት ከመደሰቱ የተነሳ ነው። ታዲያስ አሁን በቃኝ ብለህ አትነሳም? ለማኝና ባሪያ ሆነህ እስከመቼ ትኖራለህ?
በአማራው እየደረሰ ያለው ሰቆቃ፣ ግድያና ማፈናቀል በአማራ ብቻ አልተወሰነም። የህወሓት ፋሽስት ሰርዓት በሌሎች ኢትዮጵያውያንም ላይ እየፈጸመው ነው። የኦሮሞ ህዝብ በኦህዴድ፣ የደቡብ ህዝብ፣ በደህዴን፣ በትግራይ ወዘተ ከባድ ወንጀል እየተፈጸመበት ይገኛል። የዚህ ወጀል ፈጻሚዎች ቅጥረኛ ባንዳዎች ኦህዴድ፣ ደህዴን በሌላ ቦታዎች፣ ራሱ ህወሓት በቀጥታ በመግባት ግድያ፣ ዘር ማጥፋት፣ ማፈናቀል ከግብረአበሮቹ ጋር ሆኖ እየፈጸመው ይገኛል። ይህም የሚያበቃው ኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የተባበረ ክንዱን ሲያሳርፍበት ብቻ ነው!! የኢትዮጵያ ህዝብ ተነሳ! ፍርሃትህን አስወግድ!!
1ኛ. የህወሓት ሽብርተኛው ስርዓት በምንም ተአምር በሰላማዊ መንገድ ከስልጣኑ አይወርድም። ይወርዳል የሚል ካለ በጭልምተኝነት ማእበል የሚንሳፈፍ ኢትዮጵያዊ ፍጡር ነው። ህዋሓት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመጣ ሳይሆን ወራሪና ቅኝ ገዢ ነው። ይህን አምባገነን ፋሽስት ቅጥረኛ የሚወርደው በህዝባዊ አመጽ በተባበረ ክንድ ተደምስሶ መቃብር ውስጥ ሲገባ ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ ብቻ የወያኔ ስርዓት ያከትማል።
2ኛ. አንድ አንባገነን ፋሽስት ስርዓት እውነተኛ ምርጫ የሚባል ነገር አያውቅም። ፀረ-ዲሞክራሲ ስርዓት ያለበት ሃገር ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ቦታ የለውም። ይህም በ1997፣ በ2002 ያየነው ነው። በህወሓት የተዘረፈው ምርጫ አስተምሮናል። በእነዚህ ሁለት ምርጫዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አልመረጠውም። አሁንም የምርጫ ኮሚሽኑ ህወሓት፣ አስመራጭ ህወሓት፣ የምርጫ ሳጥን አቅራቢና ተቆጣጣሪ ህወሓት ነው። ተቃዋሚ ሃይሎች ከነተመራጮቻቸው በአካባቢው እንዳይደርሱ ተደርጎ እውነተኛ ምርጫ ሊከናወን አይችልም።
ለሚመጣው 2007 ምርጫ ምን መተማመኛ አለን? በሚቀጥለው ምርጫ አንድነት ለፍትህና ዲሞክራሲ (አንድነት) አሸናፊ ሆኖ እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም። ይህ ቢሆንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር የላቸውም። በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ እየተከተለው ያለውን መንገድ፣ የፋኖ ጉዞውን፣ አቁሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መተባበር አለበት። ካላደረገ የወያኔን እድሜ እያራዘመ ነው። በትግራይ አረና ሙሉ በሙሉ አሸናፊ ነው። የትግራይ ህዝብ ወያንኔ ህወሓትን አይመርጥም። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ይመረጣሉ። ይህንን ድል ለመቀናጀት ግን ምን ዓይነት የምርጫ አካሄድና ዘዴ “Mechanism” ተዘጋጅቷል? ጥያቄው ይህ ሆኖ፣ ገለልተኛ ወይም ነፃ የምርጫ ኮሚሽን፣ ከውጭ የሚመጡ ገለልተኛ ታዛቢዎች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ሃገር ኤምባሲዎች ምርጫውን በታዛቢነት እንዲከታተሉ መገኘት፤ የወያኔም ሆነ የወያኔ አጋር ደርጅቶች ወይም ተለጣፊ የጎሳ ፓርቲዎች፣ ድህንነቶች፣ ፖሊሶች፣ የወያኔ ደጋፊዎች በምርጫ ቦታዎች እንዳይታዩ ማሳገድ ወዘተ የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ለማቀነባበር ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ጊዜው አሁን ነው። ወያኔ ህወሓት ደግሞ ግርግር ፈጥሮ እንደማይቀበል የታወቀ ቢሆንም በስፋት ደግሞ እንደገና ይጋለጣ፣ እድሜው ግን ይራዘማል።
ለማጠቃለል፣ ይህ ጽሑፍ ትኩረት የሰጠው በአማራው ህዝብ ላይ ብአዴን “ብሄረ አማራ ዴሞራሲያዊ እንቅስቃሴ” ከመነሻውና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ፀረ-አማራ ሕዝብ ሆኖ የተፈጠረ፤ ትወልዳቸው ከአማራ ውጭ የሆኑ ብአዴን እና ህወሓት ሃገር እንደተቆጣጠሩ በገንዘብ የተገዙ ባንዳዎች ለመሆናቸው ምስክርነቴን ለመስጠት ነው። የብአዴን አመራር ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮቹና ባንዳዎቹ እነ ደመቀ መኮንን፣ አለምነው መኮንን፣ ጌዱ አንዳርጋቸው፣ አያሌው ጎበዜ፣ ተፈራ ደርቤ፣ ብናልፈው አንዱአለም፣ አህመድ አብተው፣ አምባቸው መኮንን ወዘተ ከነ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሰ ካሳ፣ ህላዌ ዮሴፍ፣ በህወሓት መሪነት በአማራው ላይ የከፋ ግፍና ሰቆቃ ፈጽመዋል። አማራው ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር ሆኖ፣ ለካስ እነዚህ ናቸው የኔ መሪዎች ብሎ በማሰብ፣ የገደሉትን፣ ዘሩን ያጠፉትን ሆዳሞች ሁሉ በጠንካራው ክንዱ ተባብሮ የማያዳግመውን ክንዱን እንዲዘረጋባቸው ነው። ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራው ላይ ብቻ ሳይወሰን ኦሮሞ፣ አፋር፣ ኦጋዴን፣ ድቡብ ህዝቦችም ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ተገድለዋል፣ ዘራቸውን ለማጥፋት በየወህኒ ቤቱ ታስረው በውስር እየተገደሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ በግፍ እያለቀ ነው። ከመሬቱ ተሰዶ፣ ካደገበት ተፈናቅሎ ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ እየደረሰበት ነው። ተባብሮ በመነሳት ህወሓት ወያኔን በህዝባዊ አመጽ ካልደመሰሰው ኢትዮጵያኝ ህዝቧ በህወሓት ሴራ ለክፉ አደጋ ይዳረጋሉ። በህዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል በከፋ መንገድ ከመቀጠሉ በፊት በህዝባዊ አመጽ ህወሓትን ማንበርከኪያ ጊዜው አሁን ነው።
(ገብረመድህን አርአያ – አውስትራሊያ)
No comments:
Post a Comment