Sunday, May 11, 2014

መድረክ በግጭቱ ከ45 በላይ ሰዎች ሞተዋል አለ

May 11/2014
ሰሞኑን ከጋራ ማስተር ፕላኑ ጋር በተገናኘ በተነሣው ሁከት በዩኒቨርሲቲዎች እና በኦሮሚያ ከተሞች የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ በአጠቃላይ ከ45 ሰዎች በላይ መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ መታሠራቸውን ምንጮች አረጋግጠውልኛል ሲል መድረክ አስታወቀ፡፡ በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ሃዘኑን የገለፀው መድረክ፤ ክስተቱ ገዥው ፓርቲ ለጉዳዩ ወቅታዊ እና ህገ - መንግስታዊ መፍትሔ ለመስጠት ባለመቻሉ የተፈጠረ መሆኑን ጠቁሞ፤ ይሄም ኢህአዴግ ሀገሪቱን እየመራ ያለው በስሜታዊ የሃይል እርምጃ እንጂ በሠለጠነ አግባብ አለመሆኑን ያመለክታል ብሏል፡፡ የችግሩ መነሻ የጋራ ማስተር ፕላኑ ለየከተማዎቹ ነዋሪዎች ቀርቦ ግልፅ ውይይት ባለመካሄዱ የተፈጠረ የአረዳድ እና የትርጉም መዛባት ነው ያለው ፓርቲው፤ በቀጣይ ችግሩን በአስቸኳይ ለማስወገድና ሠላም እንዲሰፍን መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች ያላቸውን ዘርዝሯል፡፡

የጋራ ልማት ሥራዎች በጋራ ውይይትና መግባባት የዜጐችንና የክልሎችን መብቶችና ጥቅሞች ባከበረ መልኩ እንዲካሄዱ ማድረግ፣ ዜጐች በሚያደርጉት የተቃውሞ ሠልፎች ላይ የሃይል እርምጃ ከመውሰድ መታቀብና ሙሰኛ ባለስልጣናትን በአግባቡ መቆጣጠር እንዲሁም ዜጐች ከመሬታቸው ሲፈናቀሉ፣ ተገቢውን ካሣ መክፈል …የሚሉት ይገኙበታል፡፡ “የብሔር ግጭት በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሠላማዊ ተማሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል” ያለው ፓርቲው፤ የፀጥታ ሃይሎች ባሉበት ሁኔታ ግድያና ድብደባ መፈፀሙ አሣፋሪ ነው ብሏል፡፡ በድርጊቱ የተሳተፉ ደብዳቢዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ፓርቲው ጠይቆ፤ የተበተኑ ተማሪዎች ተሰባስበው በሠላማዊ መንገድ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል ብሏል፡፡ ለዜጐች ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል መንግስት ሃላፊነት ወስዶ እንዲክሣቸው፣ የታሠሩት ዜጐችም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ የታሠሩ 35 የኦፌኮ (መድረክ) የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ፓርቲው ጠይቋል፡፡

በነገው እለት ጥያቄውን በሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ አቅዶ የነበረው መድረክ፤ ከእውቅና ሠጪው አካል ጋር በቦታ መረጣ ላይ ባለመግባባቱ፣ የተቃውሞ ሰልፉ ለግንቦት 10 እንደተላለፈ የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጥላሁን እንደሻው ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል በሰዎች ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ተቃውሞን ለመግለፅ የሚደረገውን ሙከራ ያወገዘው ኢዴፓ፤ መንግስት ህግና ስርዓት እንዲከበር የማድረግ ሃላፊነትና ግዴታ ያለበት መሆኑን ጠቅሶ፤ በአመፅ መልክ በሚገለፁ ተቃውሞዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ጥንቃቄ የተሞላበትና በተቻለ መጠን በሰዎች አካልና ህይወት ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆን እንደሚገባው ገልጿል፡፡ ፓርቲው በተጨማሪም ስለ ደረሰው የሰው ህይወት ጥፋትና ንብረት ውድመት ተጠያቂው በገለልተኛ አካል እንዲጣራና እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡

የችግሩ ምንጭ፣ ማንነትን መሠረት ያደረገው የፌደራል ስርአቱ ነው ያለው ፓርቲው፤ መፍትሔው የፌደራል አደረጃጀቱና ፖሊሲዎች ለአገር አንድነትና ለጋራ ልማት በሚበጅ መልኩ እንዲሻሻሉ ማድረግ እንደሆነ ጠቁሟል። መንግስት ባለፈው ሣምንት ባወጣው መግለጫ፤ በሁከቱ በድምሩ 11 ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶች ቆስለው፣ ንብረትም እንደወደመ ማስታወቁ ይታወሳል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ታሳሪያዎቹን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እስረኞቹ በምርመራ ወቅት ከህግ አግባብ ውጪ ድብደባና ስቃይ እየተፈፀመባቸው መሆኑ እንዲሁም ጉዳዩን አስመልክቶ ከመንግስት ይፋዊ መግለጫ አለመሰጠቱ እና ባለስልጣናት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ምላሽ እየሰጡ መሆናቸው ያሳስበኛል ብሏል፡፡ ስለ ጋዜጠኞቹ እና ብሎገረቹ መንግስት የጠራ መረጃ እንዲሰጥ የጠየቀው ማህበሩ በእስር ቤት ያለው የአያያዝ ሁኔታም በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment