Friday, May 30, 2014

ግንቦት 20…ከአንድ አምባገነን ወደ ሌላ አምባገነን!

May 29/2014
 ነገረ ኢትዮጵያ

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ዓለም በቴክኖሎጅና በኢኮኖሚው በእጅጉ የተለወጠበት፣ ለሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ መከበር በር የተከፈተበት፣ በሉላዊነት ምክንያት የዓለም ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሳሰሩበትና ለመተሳሰርም እድል የተገኘበት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ነጻነታቸውን ካገኙ 20 አመት ያልበለጣቸው አገራትም ነጻነታቸውን በአግባቡ ተጠቅመውበት ህዝባቸውን ለመቀየር ችለዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ደቡብ አፍሪካን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ1991 የራሷን አስተዳደር የመሰረተችውና ዓለም እውቅና ያልሰጣት ሶማሊ ላንድ እንኳ በፍትሃዊ ምርጫ፣ በሰላም መሪዎቿን በመምረጥ በአፍሪካ ቀንድ ብቸኛዋና በዓለም መንግስታት በአገርነት እውቅና ላገኙትም በምሳሌነት እየተጠቀሰች ትገኛለች፡፡

በሌላ በኩል አገራችን ኢትዮጵያ ረዥም የነጻነትነት እድሜ ያላት ብትሆንም አሁን ላይ ቀደም ብላ ከቅኝ አገዛዝና ጭቆና ነጻ እንዲወጡ ካገዘቻቸው የአፍሪካ አገራት ባነሰ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለዚህ ኋላ ቀርነቷ ደግሞ ባለፉት 23 አመታት ያገኘቻቸውን አጋጣሚዎች ገዥዎቹ መጠቀም ባለመቻላቸው እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ስልጣን ላይ የሚገኘው ህወሓት/ኢህአዴግ መጀመሪያ ላይ የዓለምን ማህበረሰብ ቀልም ለመሳብ መሰረታዊ ለውጦችን አድርጎ የነበርና እነዚህንም በህገ መንግስቱ ላይ ያስቀመጠ ቢሆንም ሲተገብራቸው ግን አልታየም፡፡ በተለይ ስልጣን ከያዘ ከአራትና አምስት አመት በኋላ ወደ ነበረበት ‹‹ግራ ዘመምነት›› በመመለስ በህገ መንግስቱ የፈቀዳቸውን መብቶች እንደገና በግልጽ ሲደፈጥጥ ተስተውሏል፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ የህትመት ሚዲያዎች ፈቃድ አግኝተው ለህዝብ መረጃ በማድረስ ላይ የነበሩ ቢሆንም ሚዲያ ህዝብን ማንቃቱን ያልወደደው ገዥው ፓርቲ እየቆየ አፈናውን ተያይዞታል፡፡ በመሆኑም በርካታ ሚዲያዎች ወደ አደባባዩ ወጥተው እንደገና ለመዘጋት ተዳርገዋል፡፡ ጋዜጠኞች ታስረዋል፤ እየታሰሩም ነው፡፡ በጫናው ምክንያት ተሰደዋል፤ እየተሰደዱም ይገኛሉ፡፡ በተለይ ህወሓት/ኢህአዴግ የደነገጠበት የ1997 ምርጫን ተከትሎ በርካታ የህትመት ሚዲያዎች ሲዘጉ፣ ጋዜጠኞች በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰው ዘብጥያ ወርደዋል፡፡ በርካቶቹ ተሰደዋል፡፡ ይህን ሁሉ ጫና ችለው ለህዝባቸው መረጃ ለማድረስ የጣሩት እንደ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙና ውብሸት ታየ ያሉት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ‹‹አሸባሪ›› ተብለው እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ ከዞን ዘጠኝ አባላት ጋር የታሰሩት ሶስት ጋዜጠኞች ስርዓቱ ባለፈው 23 አመት ያደበረውን የአፈና ባህል አጠናክሮ እንደቀጠለ የሚያሳይ ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሌሎች መብቶች ባለፈው 23 አመት ህገ መንግስቱ ላይ ከሰፈረው በተቃራኒ እየተደፈጠጡ ቀጥለዋል፡፡ በአንድ ወቅት ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳጣ በግልጽ ሲናገር የነበረው ገዥው ፓርቲ ከ1997 በኋላ ለተቃዋሚዎች መፈናፈኛ ላለመስጠት በርካታ ፀረ ህገ መንግስታዊና አፋኝ አዋጆችን አጽድቆ በህግ መሳሪያነት እየገዛ ቀጥሏል፡፡ ባለፉት 8 አመታት ህገ መንግስቱ የፈቀደው ሰላማዊ ሰልፍ በገዥው ፓርቲ ተከልክሎ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተቃዋሚዎች ግፊት የተጀመሩ የተቃውሞ ሰልፎች በገዥው ፓርቲ የደህንነትና የፖሊስ ኃይል የሚጠበቅባቸውን ያህል ሚና እንዳይወጡ ተከልክለዋል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህጋዊ በሆነ መንገድ የስብሰባ አዳራሽና ሌሎቹንም ለትግሉ ሊያገኙዋቸው የሚገቡ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ገዥው ፓርቲ ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ እንዲቆርጡና ሌሎች ሰላማዊ ያልሆኑ አማራጮችን እንዲከተሉ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በተጨማሪ ሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም ለህዝብ ጥቅም የሚቆሙ የህዝብና የመንግስትን ተቋማት አንድም ለራሱ መጠቀሚያ ማድረጉ ከዚህም በተጨማሪ ስራቸውን እንዳይተገብሩ መሰናክል መፍጠሩ ህዝብ ድምጹን የሚያሰማበት መድረክ እንዲያጣ ተደርጓል፡፡

ሚዲያ፣ ተቃዋሚዎችና ተቋማት በመዳከማቸው ገዥው ፓርቲና ፖለቲከኞቹ ያለምንም ተጠያቂነት የአገሪቱን ሀብት ተጠቅመውበታል፡፡ በመሆኑም ባለፉት 23 አመታት ከአገርና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ግለሰባዊ፣ የፓርቲና ቤተሰባዊ ጥቅምን ማጋበስ የስርዓቱ ባህሪ እንደሆነ ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝብ ከአገሩ ኢኮኖሚ የሚገባውን እንዳያገኝ ተደርጓል፡፡ በሙስና፣ በስርዓቱ ደጋፊነትና በመሳሰሉት ካልሆነ ህጋዊ መንገድን የያዘ ዜጋ ስራ መስራት ባለመቻሉ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳታገኝ ተደርጋለች፡፡ ምሩቃን፣ ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ምሁራንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ህጋዊ በሆነው መንገድ ጥቅም ባለማግኘታቸው ለስደት፣ ለድህነት ተዳርገዋል፡፡

በተቃራኒው ግን ይህ ያፈጠጠ እውነታ ተገልብጦ የግንቦት 20 ፍሬዎች እየተባለ ህዝብ ባዶ ፕሮፖጋንዳ ይጋታል፡፡ በመሆኑም ገዥው ፓርቲ እንደሚለው ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን ያገኘበት ሳይሆን ከአንዱ አምባገነን ስርዓት ወደ ሌላ መልኩን የቀየረ አምባገነን ስርዓት የተሸጋገርንበት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እናም ያለንበትን ትክክለኛ መልክ ሸፋፍኖ ስለሌለ ለውጥ ህዝብን በፕሮፖጋንዳ ከማደንቆር ይልቅ ወደ ትክክለኛ የህዝብ ተጠቃሚነትና ነጻነት የሚያደርሰውን መንገድ ይዞ ለአዲስ ለውጥ መታገል እንደሚገባ መገንዘብ ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment