Wednesday, April 30, 2014

የግሉ ፕሬስ ፈተናዎች የፕሬስ ነፃነትን እየተፈታተኑ ናቸው!

April 30/2014

የፊታችን ቅዳሜ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 ቀን 2014 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ይዘከራል፡፡ ‹‹የሚዲያ ነፃነት ለተሻለ መፃኢ ጊዜ-የድኅረ 2015 የልማት አጀንዳን ለመቅረፅ›› በሚል መሪ ቃል በመላው ዓለም የሚዘከረው ይህ ቀን፣ የፕሬስ ነፃነት በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ምን ዓይነት ገጽታ እንዳለው ያሳየናል፡፡ እኛም እግረ መንገዳችንን አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች የሚታዩ የግሉ ፕሬስ ፈተናዎችን እንቃኝበታለን፡፡

 የፕሬስ ነፃነት ቀን በሚታሰብበት ዋዜማ ላይ ሆነን ሰሞኑን በአገራችን ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችና ጦማሪያን (Bloggers) በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ፍርድ ቤት ቀርበውም የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡ በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ ለጊዜው በዝርዝር የምናነሳው ጉዳይ ባይኖርም፣ የፕሬስ ነፃነትን ከሚጋፉ ወይም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከሚገዳደሩ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የጋዜጠኞች እስራት እንደሆነ ግን የምናልፈው ጉዳይ አይሆንም፡፡ በአንድ ጊዜ በርካታ ጋዜጠኞች ታሰሩ ሲባል ድባቡ ደስ አይልምና፡፡ እስቲ በአገራችን የፕሬስ ነፃነትን የሚጋፉ ዋነኛ የግሉ ፕሬስ ችግሮችን እንቃኝ፡፡

የሙያ ክህሎት ችግር  

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የፕሬስ ጉዞ አንድ ክፍለ ዘመን ያህል አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና ባለመታደል በአገራችን አሁን ያለው የግል ፕሬስ ሥራ ላይ ከዋለ ገና የ22 ዓመታት ዕድሜ ነው ያስቆጠረው፡፡ እነዚህ ሁለት አሥርት ዓመታት የሚያሳዩን የፕሬስ ሙያ ገና በጨቅላ ዕድሜ ላይ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ለጋነትና የልምድ አናሳነት በግሉ ፕሬስ የዕለት ተዕለት ሥራ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር እየጋረጠ ነው፡፡ የግሉ ፕሬስ ከሚፈታተኑት ዋነኛ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ የሚባለው የሙያ ክህሎት (Professionalism) የሚባለው ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተምረው የሚያወጡት የሰው ኃይል የገበያውን ፍላጎት የሚመጥን አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ማግኘት አዳጋች ሆኗል፡፡

የፕሬስ ተቋማት አቅም ውስንነትና ደካማነት ተባብረው ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራት አልተቻለም፡፡ በቂ የሆነ የሙያ ክህሎት ሥልጠና ባለመኖሩ ምክንያት በሚያሳዝን ሁኔታ የሙያ ሥነ ምግባር የለም የማይባልበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ የሙያ ሥነ ምግባር ባለመኖሩ ምክንያት የግሉ ፕሬስ ከምርመራ ዘገባ ይልቅ በአመዛኙ የግል አስተያየትና ሐተታ ውስጥ ተሰማርቷል፡፡ በተለይ ቁጥራቸው በማይናቅ የፕሬስ ውጤቶች ውስጥ ጋዜጠኝነትና የፖለቲካ አቀንቃኝነት ተደበላልቀው ይታያሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በዜና ዘገባና በግል አስተያየት መካከል ያለው ድንበር ባለመታወቁ የሙያውን ሥነ ምግባር ማስጠበቅ አልተቻለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በጋዜጠኝነት ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ስያሜውን ከመያዛቸው ውጪ እዚህ ግባ የሚባል ሚና የላቸውም፡፡ ፈተናው ግን እየከበደ ነው፡፡

አንድ ሐኪም የተሰማራበት የሙያ ሥነ ምግባር ከሚጠይቀው ውጪ የእምነት ወይም የፖለቲካ ሰባኪ መሆን እንደሌለበት ሁሉ፣ ጋዜጠኛም የሲቪል ማኅበረሰቡን ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሥራ ተክቶ መሥራት የለበትም፡፡ መሐንዲስ መንገድ፣ ድልድይ ወይም ግድብ ሲገነባ ከሙያ ሥነ ምግባር ወጥቶ አላስፈላጊ ድርጊት ቢፈጽም የሚያደርሰው አደጋ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን፣ ጋዜጠኛው የሙያ ሥነ ምግባሩን ባለመከተሉና ሙያውን በብቃት ባለመወጣቱ ምክንያት የከፋ አደጋ ይፈጥራል፡፡ ይህም በተለያዩ አገሮች ውስጥ በተፈጸሙ ዘርን ማዕከል ያደረጉ ግጭቶችና ውድመቶች ታይቷል፡፡ ስለዚህ የሙያ ክህሎት ችግር የዘመናችን የግሉ ፕሬስ ፈተና ሆኗል፡፡

የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ

በኅብረተሰባችን ዘንድ ያለው የፕሬስ ሙያ ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ መረጃን ሙያዊ ሥነ ምግባር ተላብሰው ከሚያቀርቡ ጋዜጦች ይልቅ ለፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ዓይነት ውጤቶች ትኩረት ሲሰጥ ይታያል፡፡ ጋዜጠኝነት ራሱን የቻለ ሙያ፣ በሥነ ምግባር ደንብ የሚመራና በዚህም ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ የተቸረው ሙያ ነው፡፡ በኅብረተሰባችን ዘንድ ግንዛቤው አነስተኛ በመሆኑ፣ ለሙያ ሥነ ምግባር ጥሰት የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ ጋዜጠኛው ሙስናን በተጨባጭ እንዳያጋልጥ፣ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን እንዳይጠቁም፣ ለዲሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር እንቅፋት የሚሆኑ ኃይሎችን ተቋቁሞ ዘገባዎችን እንዳይሠራ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር የራሱን አስተዋጽኦ እንዳያደርግ እንቅፋት እየተፈጠረ ነው፡፡ በተቃራኒው ጋዜጠኞች ከሙያ ሥነ ምግባራቸው እያፈነገጡ የፖለቲከኞችን ሚና ሲተኩና የሙያው ሥነ ምግባር አቅጣጫውን ሲስት በኅብረተሰቡ ዘንድ በቀና መታየቱ የግሉን ፕሬስ ሚና ፈተና ውስጥ ከቶታል፡፡ በተለይ ምሁራን ይህንን የተደበላለቀ አካሄድ ከማቃናት ይልቅ ዝም ብለው ማየታቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡ 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ያልተገባ አካሄድ

ጋዜጠኝነት በገለልተኝነት መርህ የሚከናወን የተከበረ ሙያ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ በአገራችን ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተላላኪ ሲያደርጉት ይታያሉ፡፡ ጋዜጠኝነት ለማኅበረሰቡ መረጃ የመስጠት ሚናው እየተንኳሰሰ የፖለቲካ ጽንፎች ውስጥ እንዲሸጎጥ ይፈለጋል፡፡ ገዥው ፓርቲ በቁጥጥሩ ሥር ያሉ የመንግሥት ሚዲያዎችን በራሱ አምሳያ ቀርፆ እንደፈለገው ሲጠቀምባቸው፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የግሉ ፕሬስ የእነሱ አፈ ቀላጤ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ሁለቱም ኃይሎች ጋዜጠኞችን እንደፈለጉ በማሽከርከር የፖለቲካ አቋማቸው ማስፈጸሚያ እንዲሆን በሚያደርጉት ጥረት ሙያውን በአሳዛኝ ሁኔታ እየፈተኑት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የግሉ ፕሬስ ነፃነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ በመደረጉ ፈተናው ከብዷል፡፡

የመንግሥት ግዴለሽነት

የቀድሞው የፕሬስ ነፃነት አዋጅ 34/85 ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት አሥርት በሥራ ላይ ያለው የግሉ ፕሬስ የመንግሥት ድጋፍ ሊያገኝ ቀርቶ በቀና ዓይን እየታየ አይደለም፡፡ መንግሥትና የግሉ ፕሬስ የሚተያዩት በበጎ ዓይን ባለመሆኑ ምክንያት ግንኙነቱ የሻከረ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ከገበያ ወጥተዋል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች ተሰደዋል፡፡ በእስር ላይ ያሉም አሉ፡፡ የመንግሥትና የግሉ ፕሬስ ግንኙነት ተበላሽቶ ለዓመታት ቢዘልቅም መንግሥት ግዴለሽነት ነው የሚታይበት፡፡ በግሉ ፕሬስና በመንግሥት መካከል መተማመን የለም፡፡ ይህ ያለመተማመን መንፈስ ሁለቱን ወገኖች እንደ ጠላት እንዲተያዩ አድርጓቸዋል፡፡ ውጤቱንም እያየነው ነው፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎች ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የግሉን ፕሬስ ገበያ ውስጥ ይወዳደራሉ፡፡ የግሉ ፕሬስ እንደ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ከቀረጥ ነፃና ማበረታቻ አለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ በማተሚያ ቤት የተጋነነ የሕትመት ዋጋ ሲጎሳቆል፣ በሕትመት መጓተት ሲንገላታ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ የሕትመት አገልግሎት ሲከለከል ጠያቂ የለም፡፡ ተጠያቂም የለም፡፡ የግንኙነቱ መበላሸት የግሉን ፕሬስ ፈተና አክፍቶታል፡፡ የነገውን ብሩህ ቀን ለማሰብም ከብዷል፡፡

የግሉ ፕሬስ ባለ ክህሎቶችን እያጣ ነው

የግሉ ፕሬስ ፈተናዎችና ውክቢያዎች ሲባባሱ ወደ ግሉ ፕሬስ መምጣት የሚገባቸው ባለ ክህሎት ወጣቶች እየሸሹ ናቸው፡፡ ሙያውንና የሥነ ምግባር ደንቡን በሚገባ ተረድተው የሚሠሩ ትጉህ ጋዜጠኞች እየተሸማቀቁ ወደ ሌላ የሥራ መስኮች እየተመሙ ናቸው፡፡ ጠንካራ የግል ሚዲያ ለመፍጠር መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ እነዚህ ባለ ክህሎቶች በሸሹ ቁጥር የግሉ ፕሬስ የፖለቲካ አቀንቃኞችና ፕሮፓጋንዲስቶች ሰለባ ይሆናል፡፡ ከሁሉም የሚያሳስበው ግን ወጣቱ ትውልድ በዚህ ደስ የማይል ድባብ ምክንያት ሙያውን እየፈለገው ለመሸሽ ተገዷል፡፡ ይህ በራሱ አስከፊ ፈተና ነው፡፡

የግሉ ፕሬስ ኢንቨስትመንት መሳብ አልቻለም

አሁን ባለው ደስ የማይል ድባብና የጥላቻ ስሜት የተከበበው የግሉ ፕሬስ በመስኩ ሊሰማሩ የሚችሉ ኢንቨስተሮች ጭምር እየሸሹት ነው፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እየታገዘ በሙያ ሥነ ምግባር ተገርቶ ሥራውን የሚያከናውን የግል ፕሬስ በመዋዕለ ንዋይ መደገፍ ሲገባው ከአነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች ባልተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ተፈጠረ ብለን መኩራራት ሲገባን ከሱቅ በደረቴ ጋር የሚወዳደር ይመስላል፡፡ የግሉ ፕሬስ በአመርቂ ኢንቨስትመንት እየታገዘ የራሱ ማተሚያ ቤት፣ የቢሮ ሕንፃና የበርካታ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት መሆን ሲገባው፣ ህልውናው ሳይቀር አስተማማኝ ያልሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ራሱ ትልቁ ራስ ምታትና ፈተና ነው፡፡

ምን ይደረግ?

በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ፣ አስተማማኝ፣ በሙያ ሥነ ምግባር የዳበረና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በሙሉ አቅሙ መግለጽ የሚችል የግል ፕሬስ መኖር አለበት፡፡ መንግሥት የግሉ ሚዲያ ዲሞክራሲያዊት አገር እንድትመሠረት ሚና እንዳለው ይቀበል፡፡ ዕውቅና ይስጥ፡፡ የግሉን ፕሬስ በሚመለከት አሁን ያለው የመንግሥት ፖሊሲ መለወጥ አለበት፡፡ በመንግሥትና በግሉ ሚዲያ መካከል ጥሩ ስሜት ስለሌለ በግልጽ የሚታየው አድልኦ በአስቸኳይ ይገታ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የግሉ ፕሬስ ውጤቶች ዋጋ የሕዝቡን የመግዛት አቅም የሚፈታተን በመሆኑ ከውጭ በሚገባ የወረቀት ምርት  ላይ የተጣለው ታክስ ይነሳ፡፡ ለግሉ ፕሬስ ከቀረጥ ነፃና የታክስ ማበረታቻ ይደረግ፡፡ በግሉ ፕሬስ ላይ የሚደረገው ተፅዕኖና ውክቢያ ይቁም፡፡ ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ ይሰጥ፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መብቶች ይከበሩ፡፡ በተለይ የፕሬስ ነፃነትን የሚመለከተው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንቀጽ 19 (Article 19) ሙሉ በሙሉ የተቀዳው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ድንጋጌ ይከበር፡፡ ሕግ ሲከበር የፕሬስ ነፃነት ይከበራል፡፡

በሌላ በኩል ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አቀንቃኞች የግሉን ፕሬስ በመቀላቀል ጽንፍ ውስጥ አይክተቱት፡፡ ጋዜጠኝነት ራሱን የቻለ ሙያ ነው፡፡ የራሱ የሥነ ምግባር ደንብና ደረጃ አለው፡፡ ጋዜጠኝነት በገለልተኝነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ለማንም ሳያዳላ ማንንም ሳይፈራ የሚከናወን ሙያ በመሆኑ የፖለቲካ መሣሪያ አይሁን፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ስንዘክር በፕሬስ ነፃነት ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን እያሰብን ነው፡፡ ስለሆነም ለፕሬስ ነፃነት የሚታገሉ ወገኖች ሁሉ ይህንን ነፃነት የወረሩ ፈተናዎችን ሊረዱ የግድ ይላል፡፡ የግሉ ፕሬስ ፈተናዎች ከራሱ ጀምሮ ውጭ ድረስ የተንሰራፉ በመሆናቸው ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ነፃ ፕሬስ፣ ነፃ ሐሳብ፣ ነፃ መንፈስ ስንል የግሉ ፕሬስ የነፃነት አየር ይተንፍስ ማለታችን ነው፡፡ ይህ ነፃነት ደግሞ በኃላፊነት ስሜት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የሚመለከታቸው ሁሉ አፅንኦት ሊሰጡት ይገባል፡፡ የግሉ ፕሬስ ፈተናዎች የፕሬስ ነፃነትን እየተፈታተኑ ናቸው!        

No comments:

Post a Comment