Thursday, April 24, 2014

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ባቀረቡት ሪፖርት ያስገረሙኝ

April 24/2014

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለምክርቤት ዛሬ ሐሙስ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አቅርበው ጨረሱ።ከቤቴ ጀምሮ ትራንስፖርት እየሄድኩ በሞባይሌ ከአዲስ አበባ ኤፍ ኤም ላይ እየተከታተልኩ ነበር።ብዙ የሚባሉ ነገሮች ነበሩት።ነገር ግን ሁሉንም ለማንሳት ጊዜ የለኝም።ከእነኝህ ውስጥ ግን ያስገረሙኝን ብቻ ላንሳ።ቀድመው ወደስልጣን ሲመጡ የፎከሩበት ሙስናን አድበስብሰው ማለፋቸው አንዱ ነው።የዋናው ኦዲተር መስርያቤት ''ሀገር ተዘረፈ ለኢትዮጵያ ድረሱላት'' የሚል ሪፖርት ለምክርቤቱ ካቀረበ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑ ነው።ሪፖርተር ጋዜጣም ዘግቦታል።ጉዳዩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦዲተር መስርያቤቱ ምን ያህል ነፃነት እንዳለው እያደነቁ በመንገር ሊሸውዱን መሞከራቸው አስገርሞኛል።እንደሳቸው ቀጥታ አባባል ''ማሳጅ'' ያልተደረገ ሪፖርት በማለት ጠርተውታል።የሪፖርቱን ታማኝነት በሌላ በኩል አረጋገጡ ማለት ነው። ሆኖም በጠራራ ፀሐይ አሰራር እና መመርያ ያልገደባቸው ሌቦች እንዴት ሀገር እንደሚዘርፉ እና የችግሩ ምንጭ እራሱ የመንግስታቸው እና የኢህአዲግ የሰው ኃይል በሙስና የተጨማለቀ መሆኑን ግን ለመንገር አልደፈሩም።

ሌላው ብድር የተበደርነው ''አበዳርዎቻችን ስለሚያምኑን ነው'' የሚል አባባል መጠቀማቸው ነው።እውን ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ባለንበት ዓለም ሃገራት ብድር የሚሰጡት ተበዳሪው ሀገር የመክፈል አቅም አለው በሚል ብቻ ነው? ለእዚህ ነው አበዳሪ ሃገራት ብድር ለሕንድ ከመስጠት ይልቅ ለመካከለኛው አፍሪካ ብድር የሚፀድቀው? የብድር ዓላማ አንዱ የመመለስ ዕድሉ ቢሆንም ሌላው የሃገራትን ፖሊሲ እጅ መጠምዘዣ መሳርያ ስለሆነም ጭምር ነው።አቶ ኃይለማርያም እየነገሩን ያሉት  ''የመመለስ አቅማችን ስላደገ ብቻ ነው'' የሚለው አባባላቸው አይዋጥልኝም።ይልቁን ከ 5 ቢልዮን ዶላር በላይ ብድር ተበድረን ለምን ለሙሰኛ እና ለሌባ ሲሳይ እንደሚደረግ ቢነግሩን ደስ ይል ነበር። መድበለ ፓርቲ በተመለከተ ያሉት ''ልብ ውልቅ'' ነው።ያደክማል።

''ኢንቨስተር የሀገር ሉዓላዊነትን አይነካም በተለይ በጋምቤላ የእዚህ አይነቱ አደጋ የለም''ላሉት።ኢንቨስተር በእራሱ ጠላት አይደለም ግን የሉአላዊነት አደጋ የመሆን አጋጣሚዎች ግን አሉ።በተለይ ኢንቨስተር ተቀባዩ ሀገር እና መንግስት እንደ እኛ በሙስና የተጨማለቀ ከሆነ የከፋ ነው።ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ኢንቨስተሮቹ መሬት ብቻ ሳይሆን ወንዞችን የግላቸው እያደረጉ ከመሆናቸው አንፃር ብቻ ስናየው ብዙ ነገሮች ይከሰቱልናል።ሲመጡም ውሃ ከሀገራቸው በሃይላንድ እያመጡ ልያጠጡ አይደለም የመጡት ወንዞቻችን እና ዝናማችንን ነው የፈለጉት።ኢንቨስተር የሀገር ሉዓላዊነትን የመዳፈር አጋጣሚ መኖሩን ለማየት ወደ ኃላ ታሪክ ቢመለከቱ አሰብ ላይ ጣልያን እግሯን የተከለችው ከአንድ ሱልጣን በገዛችው ቁራሽ መሬት (በኢንቨስተር ስም) መሆኑን ከእርስዎ አይሰወረም። ለመሆኑ 'የልማት ጥናት' ትምህርት እራሱ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች multi-national corporations (MNC) በሀገሮች የውስጥ ጉዳይ እየገቡ ለብዙ ሃገራት የፀጥታ ችግር መሆናቸውን ያስተምር የለም እንዴ? በእዚህ ዙርያ በዓለማችን በርካታ ድርሳናት ለመፃፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን አላነበቡም? በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረ ቀጥሎ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ ሰው የአንዲት ሀገር ሉዓላዊነት አደጋዎች የመምጫ አቅጣጫዎችን አያውቅም ብሎ ማለት ይከብዳል።ግን ሃገሩ ኢትዮጵያ ሆነ እና ጠያቂ ጠፋ።

ጉዳያችን 

No comments:

Post a Comment