Sunday, March 30, 2014

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት… የህወሃት ሰዎች ጉድ!

March 29/2014

በዝርፊያ ወንጀል ተጠርጥረው በተከሰሱ የደኅንነት ሠራተኞች ላይ ምስክሮች ተደመጡ



















በውጭ ዜጋ ላይ ዝርፊያ በመፈጸም ወንጀል ተጠርጥረው በተከሰሱ የደኅንነት ሠራተኞች ላይ ምስክሮች መደመጥ ጀመሩ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአገር ውስጥ ደኅንነት ሠራተኛ በሆኑት አቶ ዮሐንስ ኪሮስ አብዩና በአቶ በኩረ ጽዮን አብረሃ ዜና፣ እንዲሁም ሾፌር መሆኑ በተገለጸውና ተባባሪ ነው በተባለው የኑስ አብዱልቃድር መሐመድ ላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ምስክሮች መስማት የጀመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው፡፡

ክሱ እንደሚለው፣ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከአሥር ወራት በፊት ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ሲሆን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19 ልዩ ቦታው ደንበል ሲቲ ሴንተር ሕንፃ አካባቢ፣ ሚስተር ካሊድ አዋድ የተባሉ የሳዑዲ ዓረቢያ ዜግነት ያላቸውን ግለሰብ ያገኟቸዋል፡፡

ግለሰቡን ሲፈትሿቸው 1,200 ዶላርና 1,600 የሳዑዲ ሪያል አግኝተው ከወሰዱ በኋላ፣ ወደ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው እንዳሳደሯቸው ክሱ ያስረዳል፡፡ በማግሥቱ ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የግል ተበዳይን ቤታቸው በመውሰድ ቤታቸውን በመበርበርና የተቆለፈ ሳምሶናይት በመስበር 8,000 የሳዑዲ ሪያልና 2,000 ዶላር፣ በድምሩ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲቀየር 106,880 ብር ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውንም በክሱ ተጠቁሟል፡፡

ሾፌር መሆኑ የተገለጸው የኑስ አብዱልቃድር የተባለው ተርጣሪ ደግሞ ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር፣ የግል ተበዳይ የሆኑትን የሚስተር ካሊድ አዋድን ቦታና እንቅስቃሴ በመጠቆም፣ እንዲሁም የተሽከርካሪ አገልግሎት በመስጠትና በወንጀሉ ተሳትፎ በማድረግ 13,000 ብር ለግል ጥቅሙ ማዋሉን ክሱ ያብራራል፡፡

የደኅንነት ሠራተኞቹ የግል ተበዳይን በቁጥጥር ሥር ባዋሉበት ዕለት በግምት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ሲሆን፣ የተበዳዩ ሠራተኛ መሆናቸው ለተገለጸ ግለሰብ ስልክ ደውለው 100 ሺሕ ብር ካልሰጧቸው ተበዳዩ እንደማይፈቱ መግለጻቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ፈጸሙት በተባለው ገንዘብ ወስዶ መሰወርና ጉቦ መጠየቅ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ የሚያስረዱለትን ሦስት ምስክሮች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

የዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ምስክር ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ሾፌሩ ስልክ ደውሎላቸው 100 ሺሕ ብር ካልሰጧቸው ተበዳዩን እንደማይለቋቸው እንደገለጹላቸውና በድጋሚ ከደኅንነት ሠራተኛው በኩረ ጽዮን ጋር በመሆን የተጠየቀውን 100 ሺሕ ብር ወደ 80 ሺሕ እና 50 ሺሕ ብር ዝቅ በማድረግ እንደተደራደሯቸው መስክረዋል፡፡

ሁለተኛው ምስክር የግል ተበዳዩ ሲሆኑ፣ በክሱ ላይ የሰፈረውን ቃል በቃል አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀሪ ምስክር ለመስማት ለሚያዝያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

EMF

No comments:

Post a Comment