Thursday, March 6, 2014

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን በማጣቱ የትምህርት ክፍሉ አደጋ ላይ መውደቁን እያሳዘናቸው መሆኑን የታሪክ መምህራንና ተመራማሪዎች ገለፁ

March 6, 2014

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን በማጣቱ የትምህርት ክፍሉ አደጋ ላይ መውደቁን እያሳዘናቸው መሆኑን የታሪክ መምህራንና ተመራማሪዎች ገለፁ። ሀገሪቱ ጥንታዊና መካከለኛ ታሪኮች ባለቤት ብትሆንም በአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የታሪክ የትምህርት ክፍል ሊዘጋ መቃረቡ እያነጋገረ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል የሚያስተምሩ መምህራንና የታሪክ ተመራማሪዎች “ታሪክ ዳቦ አይሆንም” በሚል የተሳሳተ አመለካከትና የ70/30 የትምህርት ፖሊሲ የፈጠረው ችግር መሆኑን በመግለፅ አሰራሩን አምርረው ተችተዋል። ከታሪክ በላይ ዳቦ የሚሆን የለም። ታሪክ የአንድ ሀገር የማንነትና የእውቀት መሠረት መሆኑ እየታወቀ የትምህርት ክፍሉ በተማሪ እጦት በአደጋ ላይ መገኘቱ እንደሚያስቆጣቸው መምህራኑና የታሪክ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። ሰሞኑን ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ትምህርት የተከፈተበትን 50ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት በ2006 ዓ.ም አንድም የታሪክ ተማሪ ያልተመዘገበበት መሆኑ አሳፋሪም አሸማቃቂም መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያዎቹ ችግሩን ለማስተካከል ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ፕሬዝዳንት ዶ/ር በለጠ ብዙነህ ስለጉዳዩ ተጠይቀው የታሪክ ትምህርት ክፍሉ እየተዳከመ መምጣቱን አምነዋል። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው ምክንያት በታሪክ ትምህርት የሚመረቁ ተማሪዎች በመስኩ ስራ አናገኝም በሚል አመለካከት ዲፓርትመንቱን ባለመምረጣቸው ነው ብለዋል። ከዚህ ባለፈ በታሪክ ትምህርት የተመረቁ ተማሪዎች የታሪክ መምህር የመሆን ፍላጎት ባለማሳደራቸው ወደ ሌሎች ትምህርቶች እያተኮሩ በመሆኑ ነው ብለዋል። ዩኒቨርስቲው በ70/30 ፕሮግራም መሰረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጠቅላላው በማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በ2006 የትምህርት ዘመን ወደ 600 ብቻ ተማሪ መመዝገቡን ያስታወሱት ዶ/ር በለጠ እነዚሁ 600 ገደማ ተማሪዎች በሶሻል ሳይንስ ለ20 ዲፓርትመንቶች መከፋፈላቸውን ነው ያስረዱት። ከዚህም ውስጥ ተማሪዎቹ የተሻለ የሥራ ዕድል ወደሚያስገኝላቸው የትምህርት አይነት ነው የሚያተኩሩት ብለዋል።


የታሪክ ትምህርት መዳከም እንደ ሀገር ስለሚያመጣው ተፅዕኖ የተጠየቁት ዶ/ር በለጠ፤ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ መሆኑን ይስማሙበታል። ነገር ግን በመላው ሀገሪቱ በቅርቡ በተከፈቱ 32 ገደማ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ወደ 17 ዩኒቨርሲቲዎች የታሪክ ትምህርት ስላላቸው በዘርፉ የሚመረቁ ተማሪዎችን ቁጥር በአንፃራዊነት ሊደግፈው እንደሚችል ተናግረዋል። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሁኔታ ግን የታሪክ ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ማነስ ግን አስጊ መሆኑ ተናግረዋል። ሁኔታውም በዚሁ ከቀጠለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የታሪክ መምህራን ላናገኝ የምንችልበት አደጋም ይታየኛል ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የታሪክ ትምህረት እንደ አንድ የትምህርት አይነት እየተሰጠ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የታሪክ ተማሪዎች እጥረት መታየቱ ወደፊት የታሪክ መምህራን ላናገኝ እንችላለን ሲሉም ዶ/ር በለጠ ስጋታቸውን ገልፀዋል።


ከአመለካከት ጋር በተያያዘ “ታሪክ ዳቦ አይሆንም” የሚለው አተያይ ችግር መፍጠሩን የጠቀሱት ዶ/ር በለጠ የታሪክ ትምህርት ከገበያና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ብቻ የተያያዘ በመሆኑ ይሄንን አመለካከት ለመለወጥ ብዙ መስራት እንዳለብን እንረዳለን ብለዋል። በቀጣይም የክፍለ ትምህርቱን ህልውና ለማስቀጠል የmajor/miner ፓኬጅ ማጠናቀር እንደሚገባ ጠቅሰዋል። ለምሳሌ ታሪክን በዋናነት ተምሮ ጋዜጠኝነት ወይም ቋንቋን በሁለተኛ ደረጃ እንዲማር በማድረግ የስራ አማራጭን ለመፍጠር መሞከር አለበት ብለዋል። አሁን ባለው የካሪኩለም ሁኔታ የmajor/miner ፓኬጅ አለመኖሩ ለተማሪዎቻችን አማራጭ እንድንሰጣቸው አላደረገም ብለዋል።


የሀገሪቱ ታሪክ በአግባቡ ባልተጠናበትና ባልተተነተነበት ሁኔታ የታሪክ ትምህርቱ መዳከሙ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ገዢው ፓርቲ ከሚመራበት ልማታዊ አቅጣጫም ጋር በማያያዝ የታሪክ ትምህርት መዳከሙን የሚተቹም አካላት አሉ።

No comments:

Post a Comment