March 25/2014
አገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም መብቶች ያለምንም ገደብ የሚከበሩበትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ላለፉት ዓመታት በርካታ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ ዜጎች የመደራጀትና ሀሳባቸውን የመግለጽ ህገ-መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ጧት ማታ በመንግሥት ብዙሀን መገናኛዎች ቢለፈፍም፤ ሁሉም ነገር የይምሰልና የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ስልት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልፅ ነው፡፡
ከሕግ በላይ የሆነ አገዛዝ ባለበት አገር በየስፍራውና በየክልሉ የሚገኙ ካድሬዎችና የስርዓቱ ባለሟሎች እራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው ቢቆጥሩ የሚገርም አይደለም፡፡ በዚሁም ምክንያት በገዢው ፓርቲ ተቋማት፣ ኃላፊዎችና ባለስልጣናት የሚፈፀመው ኢ-ሰብአዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች እጅግ እየከፋ መጥቷል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በፓርቲያችን በአንድነት የተሰጣቸውን የተለያዩ ተልዕኮዎችን ለለማስፈፀም ወደ ደቡብ ክልል በተንቀሳቀሱት የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ም/ኃላፊው አቶ ዳንኤል ሽበሺ ላይ እና ከ32 በሚበልጡ የወላይታ ዞን አመራሮች ላይ መጋቢት 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም መንግስታዊ ውንብድና ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በወላይታ ዞን ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ላሊሼ ኦሌ የሚመሩና የደህንነት ሰዎችን ጨምሮ ከ8-1ዐ የሚሆኑ መንግስታዊ ወሮበሎች የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላት የተሰበሰቡበትን ግቢ በሀይል ሰብረው በመግባት የፓርቲ ሰነዶችን፣ ሁለት ሳምሰንግ ጋላክሲ ስልኮችን ጨምር በድምሩ ከ2ዐ የሚበልጡ የሞባይል ስልኮችን ዘርፈው ሄደዋል፡፡
ወሮበሎቹ ታርጋ የሌላቸው ሞተር ሳይክሎችን በመጠቀም አመራሮቻችንን ወደ ፖሊስ ጣቢያ አስገድደው ወስደዋል፡፡ ከፓርቲያችን አመራሮቻችን የተነጠቁ ስልኮች በዞኑ ፖሊስ አዛዥ ቢሮ ውስጥ ፈሳሽ ውስጥ በመጨመር ከጥቅም ውጭ በማድረግ ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮችና የዞኑን ም/ቤት አመራሮች ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርገዋል፡፡ አመራሮቹን አፀያፊ በሆነ ማጎሪያ ውስጥ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6፡30 አስረው ማደሪያ ሊያገኙ በማይችሉበት ሰዓት ለቀዋዋቸዋል፡፡ ይህ አይነቱ ከመንግስታዊ አካል የማይጠበቅ ውንብድና በሚሊዮኖች ድምጽ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ወቅት ሐምሌ 5 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በዚሁ ዞን ተፈፅሞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የጠራነውን ሕዝባዊ ስብሰባ ለማደናቀፍ ታርጋ የሌላቸውን ሞተር ሳይክሎች በመጠቀም በቅስቀሳ ላይ የነበሩ አባላትን በመደብደብና በመዝረፍ እንዲሁም የተከራየነውን አዳራሽ ጥበቃዎች ዘግተው እንዲሄዱ ከመደረጉም ባሻገር ከግለሰብ የተከራየነውን ሞንታርቮ ዘርፈው እስከ ዛሬም አልመለሱም፡፡
ምንም እንኳ የአንድነት ከፍተኛ አመራርና አባላት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን በሚካሄደው ትግል ውስጥ መንገላታት፣ መደብደብ፣ መታሰርና ሞትም ካለ አይናቸውን ሳይጨፍኑ አፍጠው ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም ይህን አሳፋሪ ድርጊት በቸልታ የማንመለከተውና አስፈላጊውን ነገሮች አጣርተን ተገቢውን ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ የምንወስድበት ጉዳይ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡
ሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈረውን የመደራጀት መብትና እና በተሻሻለው በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2ዐዐዐ አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ‹2› የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ከዕለት ተግባሮችን ስር ፤ የሕዝቡን ፖለቲካዊ ግንዛቤ ማዳበር፣ የፓርቲውን ዓላማ ለሕዝቡ ማስረጽ፤ ዜጎች በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መቀስቀስ፣ በሕዝቡና በመንግሥት ተቋማት መካከል ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረግ የሚሉ ግልጽ ድንጋጌዎች ሰፍረዋል፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዛ አባሎቻቸው ጋር በማንኛውም ጊዜ መሰብሰብ እንደሚችሉ እየታወቀ በመንግስትና በገዢው ፓርቲ የሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባሮች በየእለቱ ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ሕግ ማክበርም ማስከበርም ያልቻለው ኢህአዴግ ሠላማዊ ትግሉን የሚደፈጥጡ ድርጊቶች ፈፃሚና አስፈፃሚ ካድሬዎች እና ሕገ አስከባሪ የተባለው የወላይታ ዞን ፖሊስ አዛዥ አይነት ግለሰቦችን በማበረታታት ሕጋዊና ሠላማዊ ትግሉን ወደ ጠርዝ እየገፋ ይገኛል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮችና ለወላይታ ዞን የወረዳ አመራሮችና አባላት ያለንን ክብር እየገለፅን፣ በወላይታ ሶዶ በአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና የፓርቲያችን የዞኑ ምክር ቤት አባላት ላይ የተፈፀመው መንግስታዊ ውንብድና ስርአቱ የወረደበትን የዝቅጠት ደረጃ አመላካች እንደሆነ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment