Saturday, March 29, 2014

ኢህአዴግ የእምነት ተቋማትን በጥብቅ የሚቆጣጠርበት ህግ ሊያጸድቅ ነው

March 29/2014

ህጉ ጣጣ እንዳያመጣ የሰጉ ኢህአዴግን እየመከሩ ነው
religions


ኢትዮጵያን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ እየገዛ ያለው ኢህአዴግ የሃይማኖት ተቋማትንና ምዕመናኑን በጥብቅ የሚቆጣጠርበትን ህግ ለማጽደቅ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰማ። የህጉ ረቂቅ የደረሳቸው ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ኢህአዴግን አበክረው እየመከሩና በሚያመጣው አጠቃላይ መዘዝ ዙሪያ እያስጠነቀቁ ነው።
ጎልጉል ከዲፕሎማት ምንጮቹ ባገኘው መረጃ መሰረት ኢህአዴግ በእምነት ተቋማት ላይ ቁጥጥሩን የሚያጠብቅበትንና ከሃይማኖት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውጭ መሰብሰብን፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግንና የተቃውሞ ድምጽ ማሰማትን የሚከለክል ህግ አዘጋጅቷል።
የዜናው ምንጮች ዝርዝር ህጉን ለጊዜው ይፋ ከማድረግ እንደሚቆጠቡ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ የሚደነገገውን አዲስ ህግ ጥሰዋል በሚል የሚከሰሱ ምዕመኖች እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ የሚያዝ አንቀጽ አለበት። አዲሱ ህግ ከሽብርተኞች ህግ ጋር የሚጣቀስ እንደሆነም የጠቆሙት ክፍሎች ኢህአዴግ “ከእምነት ነጻነት” ጥያቄ ጋር በተያያዘና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ውስጥ ውስጡን እየነደደ ያለው ችግር ስላስጨነቀው ይህንን ህግ ለማውጣት መገደዱን አስረድተዋል። በሌላ በኩልም እስካሁን መፍትሔ ያላገኘው የሙስሊሞች ጥያቄ ከዚያም ጋር ተከትሎ የተከሰተው ደም መፋሰስ ወደፊት ሊያመጣ በሚችለው ጉዳይ ላይ ኢህአዴግን በብርቱ አሳስቦታል፡፡
ኢህአዴግ ከቀን ወደ ቀን ቀውስ እየተደራረበት እንደሆነ የተረዳችው አሜሪካ በከፍተኛ ባለስልጣኖቿ አማካይነት ኢህአዴግን እየመከረች እንደሆነ ከዲፕሎማቶች የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከፖለቲካው ቀውስና በቀጠናው ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ አሜሪካ በተደጋጋሚ የህወሃትን ሰዎች በተናጠል እያነጋገረች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። ዲፕሎማቶቹ እንደሚሉት አሜሪካ መለስ “ከተሰዉ” በኋላ አገሪቱን ማን እየመራት እንደሆነ በቅጡ ለመረዳት በሚያስቸግር ሁኔታ የስልጣን መዛነፍና ደረጃን የጠበቀ የስልጣን ተዋረድ አለመኖሩም አሳስቧታል። ኢህአዴግ ለህልውናዬ ያሰጋኛል በሚል መንግሥታዊ ባልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች /መያዶች/ ላይ ያወጣውን አፋኝ ህግም ጠቅሰዋል። ዲፕሎማቶቹ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ወቅቱ አሁን እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ጎልጉል

No comments:

Post a Comment