Thursday, March 27, 2014

“ኢህአዴግ ከምሆን ሞቴን እመርጣለሁ” – ኢ/ር ዘለቀ ረዲ (ቃለምልልስ ከሎሚ መጽሔት ጋር)

March 27/2014



ኢ/ር ዘለቀ ረዲ ከወራት በፊት በተዋቀረውና አዲስ አመራሮችን በመረጠው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል፡፡ የሎሚ መፅሔት እውነትን ለህዝብ ለማድረስ ካለባት የሞያ ግዴታ አንፃር በኢ/ር ዘለቀ ዙሪያ በሚነሱ ሀሳቦች ላይ ተንተርሶ የሎሚ ም/አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ያደረገውን ቆይታ የመጀመሪያ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሎሚ፡- አዲሱ የአንድነት ካቢኔ ሥራዎች እንዴት እየተከናወኑ ነው?

ኢ/ር ዘለቀ፡- በጣም ጥሩ ነው፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ አዳዲስ ሰዎችን ነው ያመጣው፡፡ ከዛ አኳያ ጠንካራ ወይም ለቦታው ይመጥናሉ የተባሉ ሠዎች ናቸው የተመረጡት፡፡ ከዚህ ቀደምም ጠንካራ ሠዎች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ጠንካራ ሆነው ሊሠሩ የሚችሉ ሠዎች ናቸው የተመረጡት፡፡ እንደሚታወቀው አንድነት መሬት የረገጠ ፓርቲ ነው፡፡ ዝም ብሎ አየር ላይ የተንጠለጠለ ፓርቲ አይደለም፡፡ ከዛ አንፃር ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ ነው፡፡ አሁን ያለው አሠራር በዚሁ ከቀጠለ ጥሩ ውጤት ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሎሚ፡- በርካቶች ግን አዲሱን የአንድነት ካቢኔ አወቃቀር አልወደዱትም ይባላል፤
ኢ/ር ዘለቀ፡- ከምን አንፃር?…ግልፅ አድርግልኝ?

ሎሚ፡- አንተን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሶስት ሰዎችን ማካተቱ ትክክል አይደለም የሚሉ ሂሶች ተሰንዝረዋል፡፡ ለምሳሌ፡- አንተን ከፓርቲው ለረጅም ጊዜ ርቆ ነበር፤ ራሱንም ማግለሉንም ተናግሮ ነበር፡፡ ቀደም ሲል በአመራርነት በነበረበት ጊዜ ድክመት ታይቶበት ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ያሉበት ሠው እንዴት በአመራር ደረጃ ሊመረጥ ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ፤

ኢ/ር ዘለቀ፡- አንዳንድ ነገሮችን ግልፅ ላድርግልህ፡፡ በመጀመሪያ ከፓርቲው ርቆ ነበር የሚለው ስህተት ነው፡፡ የፓርቲው አባል ነኝ፤ ከፓርቲውም ራሴን አላገለልኩም፤ ከስራ አስፈፃሚነት ራሴን አግልዬ ነበር፤ ከፓርቲው ግን አላገለልኩም፡፡ በብሔራዊ ም/ቤት ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ በአባልነትም ቢሆን እሰራ ነበር፡፡ ሁልጊዜ ከፓርቲው ጋር እሰራ እንደነበር ነው የማስበው፡፡ ከፓርቲው ርቆ ፓርቲውን ለቆ ተመልሶ ወደ አንድነት መመለስ ትንሽ ከባድ ነው፡፡ አንድነት እንደ ሌሎች ፓርቲዎች አይደለም፡፡ አንድነት በጣም በነፃነት የሚሰራበት ፓርቲ ነው፡፡ እውነት ነው የምነግርህ፤ እኔ አንድነትን ለማስተዋወቅ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኢ/ር ግዛቸው ዛሬ ተነስቶ እኔ መስራት አይችልም ቢል ለምን የሚል ጥያቄ እንኳን አይቀርብበትም፡፡ እሺ ነው የሚባለው፡፡ ከአንድነት ሥራ አስፈፃሚው እለቃለሁ ሲል ለምን ትለቃለህ ብሎ የሚጠይቅ አልነበረም፡፡ መብትህ ነው፡፡ ማንም ሰው ከአባልነት እለቃለሁ ካለ የመልቀቅ ሙሉ መብት አለው፡፡ እመለሳለሁ ካለም ደግሞ ትቀበለዋለህ፡፡ ከፓርቲው ርቆ የነበረ ሰው ድጋሚ ልመለስ ቢል ትንሽ ከባድ ነው፡፡ አባላቱ ከባድ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ም/ቤቱም እንደዚህ እንደምንገምተው አይደለም፡፡

ሎሚ፡- ከዚህ ቀደም ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጠኸው ቃለ ምልልስ ከስራ አስፈፃሚነት በራስህ ፍቃድ መልቀቅህን ተናግረህ ነበር፡፡ የፓርቲው ሊ/መንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደግሞ አንተን ከቦታው ያነሱት እርሳቸው መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሄን ነገር እንዴት ተመለከትከው?

ኢ/ር ዘለቀ፡- በዚህ ጉዳይ ምንም ባልል ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በእናንተ መፅሔት ላይ እርሳቸው ያሉትን አይቼዋለሁ፡፡ የመፅሔታችሁ ደንበኛ ነኝ፡፡ እርሳቸው እኔ ነኝ ያነሳሁት ብለዋል፡፡ ጥሩ፤ እርሳቸውም ያባሩኝ እኔም ልልቀቅ ችግር የለውም፡፡ አንድነት በነበሩበት ጊዜ ስለሰሩት በጎ ነገር አውርተዋል፡፡ ከበጎ ነገሮች አንዱ ደግሞ እኔን ማባረር ነው፡፡ ከዚህ ላይ ሊያገኙት የሚችሉት ትርፍ ምንድን ነው? እኔን የመሰለ ሠው፣ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ፣ የራሱ ሥራ ያለው፣ ፓርቲውን ሊደግፍ የሚችል ሰው ማባረራቸው ነው ውጤታማ ሥራቸው? በጣም በርካታ ሠዎችን አስገብተው እነገሌን አምጥቻቸዋለሁ ማለት ነው የሚሻለው ወይስ ኢ/ር ዘለቀን አባርሬዋለሁ?! እሺ እርሳቸው አባረሩኝ ብዬ ልውሰድ፤ ሰንደቅ ጋዜጣ በገዛ ፈቃዴ መልቀቄን ተከትሎ ጠይቋቸው ነበር፡፡ ያኔ “ኢ/ር ዘለቀ አለቀቀም፤ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ነው የምናውቀው፡፡ አልሄደም አለቀቀም” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በርሳቸው ዕድሜ ያለ ሰው ያንን ምስክርነት መካድ ይችላል?…ያኔ የተናገሩት ነገር መረጃ ነው፡፡ ወደኋላ ተመልሰው እኔን አባረውኝስ ቢሆን? መናገራቸው ምንድነው ትርፉ? እኔና እርሳቸው በዕድሜ በእጥፍ እንለያያለን፡፡ በዕድሜያቸው ብዙ ችሎታ አላቸው፤ ብዙ ለፍተዋል፡፡ ውጤት ማምጣት አለማምጣት የራሱ ጉዳይ ሆኖ ማለት ነው፡፡ እኚህ ሠው እኔ እንኳን በጣም መጥፎ ሠው ሆኜ ባስቸግር እንኳን መልሰው በጣም መጥፎ ሰው ነበር፤ እኔ ነኝ ያስተካከልኩት ቅርጽ ያስያዝኩት ቢሉ ነበር የሚሻለው፡፡ ኢ/ር ዘለቀን ያባረርኩት እኔ ነኝ ማለት ጀብደኝነትም አይደለም፡፡

አንድ ሰው ሊቀ-መንበር የሚሆነው ሰዎችን ለማባረር አይደለም፡፡ ደካማውን ማጠንከር ይጠበቅበታል፡፡ ማንም ሠው ደካማ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ ደካማ አይደለሁም፡፡ ደካማ ብሆን ኖሮ አሁን ያለሁበት ቦታ ላይ አልገኝም ነበር፡፡ በትንሹ 150 ሠራተኞችን በስሬ አስተዳድራለሁ፡፡ ከ40 በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉኝ፡፡ ከ200 ሺህ ብር በላይ የወር ደመወዝ እከፍላለሁ፡፡ ይሔን ሁሉ የሚሰራ ሰው ደካማ ነው? ቤተሰቤንም ሆነ ሌሎች ሠዎችን ማስተዳደር የምችል ሠው ነኝ፡፡ ደካማ ብሆንም ከዶ/ር ነጋሶ የምጠብቀው “እንደዚህ ያለ ደካማ ነበር፤ እኔ ነኝ ጠንካራ ያደረግኩት” የሚል ምላሽ ነበር፡፡

ሎሚ፡- የአንድነት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሊቀጣህ የነበረበትና እንዲቀጣህ መመሪያ የተላለፈበት ሁኔታ ነበር?…

ኢ/ር ዘለቀ፡- ዶ/ር ነጋሶ ያላወቁት ነገር ሰው ወንጀለኛ ነው ጥፋተኛ ነው ተብሎ ሊከሰስ እንደሚችል ነው፡፡ አንድ ሌባ ፍርድ ቤት እስከሚፈርድበት ድረስ ተጠረርጣሪ እንጂ ወንጀለኛ አይባልም፡፡ ፍ/ቤቱ ትክክለኛ ውሳኔ እስከሚሰጠው ማለት ነው፡፡ የኔ ጉዳይም በዲሲፕሊን ያስቀጣል አያስቀጣም የሚለውን ማየት የነበረበት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ነው አይደል? ያንን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ደግሞ ማጠናከር የነበረባቸው ዶ/ር ናጋሶ ናቸው፡፡ እርሳቸው ያዳከሙትንና እርሳቸው የሌላቸውን ዲሲፕሊን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ሊሰራው አይችልም፡፡ መጥተው ማቋቋም ይችላሉ፤ በሩ ክፍት ነው፡፡ እመጣለሁ ሲሉ አንድነት ይቀበላል፤ እሄዳለሁ ሲሉ ደህና ሁኑ ይላል፡፡ ጥፋት ኖሮብኝ ቢሆን ኖሮ እቀጣ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ውጭ ሆነው ይቆጫቸዋል፡፡ የኔ አለመቀጣት ትርፉን አላውቀውም፡፡ ፍ/ቤትም አለ እኮ፤ ከዛ ባለፈም እኔን መክሰስ ይቻላል፡፡ እኔ በእውነቱ የዲሲፕሊን ግድፈት አልነበረብኝም፡፡ ም/ቤቱ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ይየው ብሏል አይደል? ይሄ ማለት ደግሞ ዘለቀ የዲሲፕሊን ግድፈት አለበት ማለት አይደለም፡፡ ዲሲፕሊን ኮሚቴውን አጠናክሮ እኔን ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ማቅረብ የነበረባቸው እርሳቸው ነበሩ፡፡ እውነት ለመናገር በእናንተ መፅሔት ላይ እንዳየሁት እኔ በፓርቲ መቀጠሌ ደስተኛ አላደረጋቸውም፡፡ እኔ ለቅቄ እወጣላቸዋለሁ፤ ችግር የለውም፡፡ ውጭ ሆኜ ፓርቲዬን መርዳት እችላለሁ፡፡ ዋናው ግን የሚያገኙት ትርፍ ምንድነው የሚለው ነው፡፡

ከመንግስት በኩል ብዙ ጫና አለብኝ፡፡ የኮንስትራክሽን ድርጅቴ ስምንት ዓመት ሆኖታል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ከመንግስት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የስራ ዕድል ያገኘሁት፡፡ ማንኛውም ኮንትራክተር የኮንደሚኒየም ሥራ የሚሰጠው ተጠርቶ ነው፡፡ የእኔ ድርጅት ግን ኮንዶሚኒየም ላይ አንድ ጠጠር አልጣለም፡፡ ለምን ቢባል ሊያዩኝ ስላልፈለጉ ነው፡፡ የኔ አንድነት ውስጥ መቀጠል ለምን ዶ/ር ነጋሶን ያበሳጫቸዋል? የሶስት ወር ጊዜ ነው የተሰጠን፡፡ አቅም ከሌለኝ የአንድነት ድርጅት አመንክም አላመንክም በሶተኛው ወር ዘለቀ አቅም የለውምና ይውጣ ይላል፡፡ ያንን ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ከኢህአዴግ ጎራ የወጡ ሰዎችን የዲሞክራሲው ትግል አጋር ማድረግ ነበረባቸው፡፡ እንጂ እኔም ላግዝ ብሎ የመጣውን የኔ ዓይነት ሰው አባረርኩት ማለት አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡

ሎሚ፡- የአንድነት ፓርቲ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ነህ፡፡ ቦታው ትልቅ ነው፤ ይህንን ትልቅ ቦታ ያገኘኸው ደግሞ ፓርቲያችሁ አንድነት የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት የሚለውን እንቅስቃሴ ባዘጋጀበት ወቅት የገንዘብ ልገሳ ስላደረገ ለውለታው የተሰጠው ነው እንጂ ለቦታው የሚመጥን ሆኖ አይደለም ሲባል ነበር፤

ኢ/ር ዘለቀ፡- በርግጠኝነት ይሄን የሚሉ አዕምሮ ያላቸው ሠዎች ይኖራሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ይሄ አንድነትን መናቅ ነው፡፡ አንድነት የት ቦታም እንዳለም አለማወቅ ነው፡፡ እውነቴን ነው የምነግርህ አንድነት ለብር ብሎ በህልውናው ላይ የሚደራደር ፓርቲ አይደለም፡፡ ይሄ የአዕምሮ ማነስም ጭምር ነው፡፡ ይሄ ማለት ዘለቀ አንድነትን በብር ይገዛዋል ብሎ ማሰብ ነው፡፡ አንድነትንም ማናናቅና መወንጀልም ጭምር ነው፡፡ የአንድነት ም/ቤት በሃገር፣ በህዝብ፣ በህልውና ላይ የማይደራደር ም/ቤት ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ሊቀ-መንበር በነበሩበት ጊዜ በአብላጫ ድምፅ የሚወሰነውን ነገር የመስራት ግዴታ አለባቸው አይደል? የራሳቸውን ልዩነት ግን በጋዜጣ ሁሉ ያራግቡ ነበር፡፡ ስለመድረክ ጉዳይ ልዩነት አለኝ ብለው ይፅፋሉ፡፡ ልዩነታቸውን እየፃፉ በአብላጫ ድምፅ ለመገዛት ደግሞ ህጉ ያስገድዳቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ዘለቀ ለሚሊዮኖች ድምፅ ገንዘብ ስላወጣ ነው የተመረጠው ብሎ አንድነትን መናገር አሳፋሪ ነው፡፡

ሎሚ፡- ኢ/ር ዘለቀ የኢህአዴግ መልዕክተኛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ለዚህ አባባላቸው ደግሞ ካሉት ሶስት ም/ጠ/ሚኒስትሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሙክታር ከድር የቅርብ ወዳጅና ከወዳጅነትም በላይ በአንድነት ውስጥ የማዳከምና የአንድነትን እቅስቃሴ ለመቅጨት ሰርጎ እንዲገባ የተደረገ መልዕክተኛ ነው ይባላል፡፡ አንተስ ሰምተሃል? ምንስ ትላለህ?

ኢ/ር ዘለቀ፡- በመሠረቱ እነዚህን ነገሮች በሁለት ከፍዬ ማየት ነው የምፈልገው፡፡ እኔ የሙክታር ከድር ወዳጅ ብሆን እፈልገው ነበር፡፡ ለምን መሰለህ ሙክታርን እያነጋገርኩኝ መንግስት ያለውን አቋም ማወቅ እችል ነበር፡፡ እውነት ለመናገር እንደዚህ ያሉ ሠዎችን አጥተን ነው እንጂ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ጓደኛ ብንሆን እኮ ብዙ ነገር ታወራለህ፡፡ ድክመቱንም የምታገኘውም በዛ ነው፡፡ ኢህአዴግ እኮ ደርግን ያሸነፈው በደህንነቱ በእነ ተስፋዬ ወ/ስላሴ አማካይነት ነው፡፡ ቁልፍ ሰዎችን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ብንይዛቸው ደግሞ ይህ የድክመት ምልክት አይደለም፡፡ ምናልባት እንግዲህ ሙክታርም የጅማ ልጅ ነው፤ እኔም የጅማ ልጅ ነኝ፤ ያው መላ ምት ነው፡፡

እንደ ዶ/ር ነጋሶ ያሉ በርካታ ሠዎች የሚጎነትሉህ ቦታ ቁጭ ብለህ የኢህአዴግ መልዕክተኛ ከምትሆን የኢህአዴግ ካድሬ አትሆንም? የአንድ ዞን አስተዳዳሪነት ቦታ ይሰጥሃል እኮ፡፡ አሁን ካሉት ሠዎች በአቅም ላልተናነስ እችላለሁ፡፡ ኦህዴድ ብሆን ደረጃዬን ጠብቄ መጥቼ ሙክታር ያለበት ደረጃ መድረስ እችል ነበር፡፡ በርግጠኝነት ዛሬ ሄጄ ብጠይቀው ኢህአዴግ ይሄን የሚነፍግ ንፉግ አይመስለኝም፡፡ እንደውም ጠላት መቀነስ ነው፡፡

ለህሊናቸው ሳይሆን ለሆዳቸው ያደሩ ጋዚጠኞችም አሉ፡፡ አንድ ሁለት ሶስት ጋዜጠኞች ደውለውልኝ አንድ ጥያቄ ጠይቀውኝ ነበር፡፡ በጣም የወረደ ጥያቄ ማለት ነው፡፡ እኔ ብዙ አልፈራም፤ ሠዎች ይመጡና አንድ ነገር እንስራ ይሉሃል፡፡ በሁለተኛው ቀን ሌላ ነገር ይጠይቁሃል፡፡ ይሄማ ትክክል አይደለም ስትላቸው እንደዚህ ነህ እንልሃለን ይሉሃል፡፡ ምንም ይበሉህ ምን ጊዜውን ጠብቆ እውነት ያወጣዋል፡፡ እኔ ከአንድነት ስራ አስፈፃሚ እንደወጣሁ ኢህአዴግ ሊሆን ነው ምናምን ይሉ ነበር፡፡ ኢህአዴግ እኔ የማስበውን የሚያስብ ከሆነ እንደኔ አንድነት የሚያጠናክር ከሆነ ልናግዘውና ልናጠናክረው ነው የሚገባው፡፡ እንደኔ ዓይነት ኢህአዴጎች ካሉ ለምንድነው የማንሠበስባቸውና የማናመጣቸው? ዘለቀ የኢህአዴግ አባል ሲሆን መታወቂያ ይኖረዋል አይደል፡፡ ኢህአዴግ አንድነትን ለመሠለል ከበቃ አድገናል ማለት ነው፡፡ ይቺ አሉ የሚባሉትን ሠዎች ከስር ሆኖ መቀንጠሻ ናት ዘዴ ናት፡፡

ስለ አንድ ሰው ልንገርህ፤ የባንክ ሠራተኛ ነው፤ ስሙን አልገልፅልህም፤ መሃንዲስ ነው፡፡ አንድ ቀን በራሴ ፅሁፍ በይፋ እገልጸዋለሁ፡፡ አንዱን ጋዜጠኛ ምን ብሎ ያሳስተዋል መሠለህ? አርሲ ነገሌ “መንገድ ስራ” ወስደነው ነበር፡፡ መንገዱ ፈርሶ ተበላሻሽቶ ከፍተኛ ብጥብጥ ተነስቷል ብሎ ይነግረዋል፡፡ ይሄን የሰማው ልጅ ይደውልልኝና “ኢ/ር ዘለቀ ነህ አዎ…አርሲ ነገሌ የምትሠሩት መንገድ ተበላሽቷል ወይ? ምናምን ብሎ ይጠይቀኛል፡፡ ማን ነገረህ? አልኩት፡፡ ጥቆማ ደርሶን ነው አለ፡፡ ዓይተህ ማውጣት ትችላለህ፤ ይህን ካላደረግክ እኛ ህጉን ጠብቀን እንከስሃለን ብዬ መለስኩለት፡፡ ከ15 ቀን በኋላ መንገዱ ይመረቅ ነበር፡፡ ከመመረቁ በፊት ተዟዙሮ የተመለከተው የከተማው አስተዳደር “የመጀመሪያ ኮንትራክተር ነው” ብሎናል፡፡ ሞያውን ተጠቅሞ ስራውን በአግባቡ ሰርቶልናል ተብሎ የከተማ አስተዳደሩ “ቡልኮ” ሸልሞኛል፡፡ በኦሮሞ ባህል ቡልኮ የተሸለሙት እነ አባዱላ ናቸው፡፡ ጋዜጠኛው እዛ ነበርና በጣም ነው የደነገጠው፡፡ ስለዚህ እዚህ መጥተው የተለየ ጥቅም የሚያገኙ ሠዎች ሄደው ስም ያጠፋሉ፡፡ ኢ/ር ግዛቸውን ብዙ ነገር ይሉታል፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በተፈጥሮው ጠንካራና እያጣራ ማለፍ የሚወድ ሠው ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ቢሆኑ በዚህ ፈተና ይወድቁ ነበር፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ጋር ቀድሞ ሄዶ የነገራቸው ሰው አሸናፊ ነው፡፡ እኔ አንተን ቀጥቅጬህ ቀድሜ ሄጄ ከነገርኳቸው ቁስልህን ብታሳይ አይሰሙህም፡፡ ኢ/ር ግዛቸው ግን ይህንን ሁሉ ነው የተቋቋመው፡፡ እነዚህ ሠዎች ካንተ ጥቅም ሲያጡ ፓርቲ ውስጥ ስትገባ የምትጠቀም ይመስላቸዋል፡፡ ለሃገርህ የሆነ አስተዋፅዖ ለማበርከት የሄድክ አይመስላቸውም፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ነገር ሊወራብህ ይችላል፡፡ በመረጃ “ኢህአዴግ ነው ብሎ” የሚሞግተኝ ካለ ምንም ችግር የለብኝም፡፡ አሉባልታ ግን አሉባልታ ነው፡፡ የኔ ማረጋጋጫ ስራዬ፡፡ ኢህአዴግ ብሆን ኖሮ አንዲት ሴትዮ 400 ሺህ ብር በልታኝ አትቀርም ነበር፡፡ ኢህአዴግ ሆኜ ይሄ ነው የኮንዶሚኒየም ግንባታ ላይ እንዳልሳተፍ (እንዳልሰራ) አልደረግም ነበር፡፡ ኢህአዴግ የሆኑ ሰዎችን እናውቃቸዋለን፡፡ ቢጠሯቸው አይሰሙም፡፡ ገንዘባቸው የት ነው ያለው? እኛ እኮ NGO እየለመንን ነው የምንሰራው፡፡ ያውም ደግሞ ጠንካራ ጠንካራ NGOዎች ናቸው እንጂ አነስ አነስ ያሉት ዝም በሉ ሲባሉ ዝም ይላሉ፡፡ በርካታ NGOዎች ናቸው ጨረታ ካለፍን በኋላ የሰረዙብን፤ ደህንነቶች እያስፈራሯቸው ማለት ነው፡፡ ዘለቀ ኢህአዴግ ነው የሚባለው ከአንድነት ከፓርቲ አገልግሎት ለማስወጣት ሲባል ነው፡፡ ኢህአዴግ መሆን ብፈልግ በአንድነት በኩል መዞር የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡ ለሰራተኞቼ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንሹራንስ የምገዛ ሰው ነኝ፡፡ አንድ ሚኒስትር የሚከፈለው ደመወዝ ስንት ነው? እኔ እኮ 38 ሺህ ብር ነው ለአንድ መሃንዲስ የምከፍለው፡፡ ምን አጥቼ ነው ኢህአዴግ ስር የምሸጎጠው? በህልሜም የኢህአዴግ አባል ሆኜ ማየት አልፈልግም፡፡ እስካሁን ባለኝ አቋም የኢህአዴግ አባል አይደለሁም፡፡ የአይዲዎሎጂ አስተሳሰብ ጊዜውን ጠብቆ የሚቀየር ነገር ነውና ወደፊት ምን እንደሚፈጠር አላውቅም፡፡ ምኒልክም “ሃገሬ ስትወረር ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ” እንዳሉት እኔም ኢህአዴግ ከምሆን ሞቴን ነው የምመርጠው፡፡ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነጻነት የሚለውን የአንድነት ዘመቻ ረዳህ ተባልኩ፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያ ጥቅም ሲሰራ እደግፋለሁ፡፡ ኢህአዴግ የፖለቲካ ቅስቀሳ ስለሚያደርግበት አንድም እርዳታ አድርጌበት አላውቅም፡፡ የአባይ ግድብ የኔ ገንዘብ የለበትም፡፡ ለምን? ለፖለቲካ ቅስቀሳ እያዋለው ስለሆነ፡፡ ለህዝብ አሳልፎ ስላልሠጠ፤ ለህዝብ ስጥ እያልኩ እየፃፍኩበት ነው፡፡ ለህዝብ ሲሰጥ ግን አንደኛ የምረዳው እኔ ነኝ፡፡ አሁን ግን ለአባይ ግድብ የአንድ ብር ቦንድ አልገዛሁም፡፡

ሎሚ፡- ከዚህ ቀደም የፓርቲያችሁ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነፃነትን “አዲስ ዘመን” ብለህ ዘልፈኸዋል፤ አዲሱ ካቢኔ ሲዋቀርም በአንተ መመረጥ ዙሪያ ከተነሱ ቅሬታዎች አንዱ ይሄነው፤ እንዲህ ልትል የቻልክበት ምክንያት ምንድነው?

ኢ/ር ዘለቀ፡- ምን መሰለህ? በወቅቱ አንድ ዜና ሰርተው ነበር፡፡ እኔን የሚመለከት ዜና ም/ቤቱ ሲሰጣቸው ሚዛናዊ ለማድረግ ሀሳቤን አላካተቱም ነበር፡፡ ስላልጠየቁኝ “ፍኖተ ነፃነት” ትልቅ የህዝብ ሚዲያ ናት፤ ግን ምንድነው ከአዲስ ዘመን የተለየ የሚያደርገው?…አዲስ ዘመን ዜና ሲሰራ የጉዳዩን ባለቤት አይጠቅም አይደል?…ፍኖተ ነጻነትም እንደዚያ ስላደረገ አዲስ ዘመን ብዬው ነበር፡፡ እኔን መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ በአንድነት ባህል አንድ ግለሰብ ከፕሬዚዳንቱ እኩል መብት አለው፡፡ ያንን መብቴን አልሰጣችሁኝም የሚል ቅሬታ ነው ያነሳሁት፡፡ ከጋዜጠኛው ጋርም ተነጋግረናል፡፡ ዜናውን ስትሰሩ ሚዛናዊ ማድረግ አለባችሁ በሚል ተወያይተናል፡፡ ችግሩም በሰላም ተፈትቷል፡፡

No comments: